1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፦ «አዲስ አበባ ጠብቁን» - ኦዴግ

ነጋሽ መሐመድ
እሑድ፣ ግንቦት 12 2010

ለተጨማሪ «ድርድር እና ለሰላማዊ ትግል» ኢትዮጵያ ለመግባት መወሰኑን አስታዉቋልም።ኦዴግ በዉሳኔዉ ከፀና ከ1983 ወዲሕ እንደ ፓርቲ ከዉጪ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የመጀመሪያዉ የፖለቲካ ማሕበር ይሆናል።

https://p.dw.com/p/2xy4u
Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

ዉይይት፤ «አዲስ አበባ ጠብቁን» ኦዴግ

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ እና የሚመራዉ መንግሥት መሪ ከቀየሩ ወዲሕ የሐገሪቱ የ26 ዓመት የአገዛዝ መርሕ መጠነኛም ቢሆን የለዉጥ ፍንጭ እያሳየ ይመስላል።

እርግጥ ነዉ ለዉጡ በሚፈለገዉ ፍጥነት ገቢር አልሆነም ባዮች አሉ። ለተከታታይ ሰዎስት ዓመታት  አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ላነሳቸዉ የዴሞክራሲ፤የሰብአዊ መብት እና የፍትሕ ጥያቄዎች  ቀጥተኛ እና ተጨባጭ መልስ አላገኘም በማለት የሚተቹም አሉ።

ይሁንና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ የሚመሩት መንግሥት የሕሊና እስረኞችን መልቀቁ፤ የካቢኔ ሹም ሽር ማድረጉ፤ ለረዥም ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩ ሹማምንታትን በጡረታ መሸኘቱ ከሁሉም በላይ አዳዲስ አሰራሮችን ገቢር ለማድረግ ቃል መግባቱ ብዙዎችን አማልሏል።

ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሐል ግን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)ን ያክል በጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ጅምር ሥራ፤ ቃል እና ተስፋ እስካሁን የተማረከ፤ መንግሥትን አምኖ የተቀበለም ያለ አይመስልም።

Oromo Democratic front (ODF) Logo
ምስል Oromo Democratic front

መንግሥት፤ አዳዲስ ባለሥልጣናቱ በገቡት ቃል መሠረት ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በድብቅ ተነጋግሮ፤ እየተነጋገረ፤ ምናልባት ተስማምቶም ሊሆን ይችላል። እስካሁን መደራደሩን፤ መስማማቱንም በይፋ ያረጋገጠዉ ግን ከኦዴግ ጋር ብቻ ያደረገዉን ነዉ። የሁለቱ ወገኞች ተወካዮች ግንቦት 3 እና 4 መደራደራቸዉን ኦዴግም አረጋግጧል።

ለተጨማሪ «ድርድር እና ለሰላማዊ ትግል» ኢትዮጵያ ለመግባት መወሰኑን አስታዉቋልም። ኦዴግ በዉሳኔዉ ከፀና ከ1983 ወዲሕ እንደ ፓርቲ ከዉጪ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የመጀመሪያዉ የፖለቲካ ማሕበር ይሆናል። የኦዴግን ዉሳኔ የሚደግፉ እና የሚያደንቁ እንዳሉ ሁሉ የተቃወሙትም አሉ።የድጋፍ ተቃዉሞዉ ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ እዉነት፤ተስፋ እና ቀቢፀ ተስፋዉ ያፍታ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ