1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉጊያና ተኩስ ያናወጣት የሶማሊያ መዲና

ረቡዕ፣ መጋቢት 12 1999

በዛሬዉ ዕለት የሶማሊያ መዲና መቃዲሾ ዉስጥ በሽግግሩ መንግስቱና በረዳትነት እዚያ በሚገኙት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ከባድ ጥቃት መስንዘሩን የዜና አዉታሮች ዘግበዋል።

https://p.dw.com/p/E0Yd
የኢትዮጵያ ወታደሮች በመቃዲሾ
የኢትዮጵያ ወታደሮች በመቃዲሾምስል AP

የመዲናዋ ኗሪዎች ለዘጋቢዎቹ እንደገለፁት ጥቃት አድራሾቹ የኢትዮጵያ ታንክ ላይ ተኩስ ሲከፍቱ ምላሽ በመከተሉ ጠንከር ያለ የተኩስ ልዉውጥ ተካሂዷል። ሶማሊያን ለማረጋጋት ወደመቃዲሾ የገባዉ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር በመዲናይቱ የሚታየዉ ያልተጠበቀ ክስተት አይደለም ይላል። የዶቼ ቬለ የኪስዋሂሊ ወኪል ከመቃዲሾ በቅድሚያ ወደሶማሊያ ከገባዉ የህብረቱ ጦር መካከል የዑጋንዳዉን ሻምበል አነጋግሯል።

በአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ መሰረት ከእኩለ ቀን በፊት የሶማሊያና የኢትዮጵያ ወታደሮች የአደጋ ጣዮቹ የተጠናከረ ስፍራ ተብሎ በሚታመነዉ ማዕከላዊ መቃዲሾ በገቡበት ወቅት ነዉ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ህይወታቸዉን ያጡበት ዉጊያ የተቀሰቀሰዉ። በመቶዎች የሚቆጠሩት ጭንብል ያጠለቁ ጥቃት አድራሾችም በታንክና መሳሪያ በተጠመደባቸዉ ተሽከርካሪዎች የሚደገፉትን የመንግስት ወታደሮች እንደተጋፈጧቸዉ የአካባቢዉ ኗሪ ገልፀዋል። በርካታ ሰላማዊ ዜጎችም አደጋ ጣይዎቹ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሰፈር በሆነዉ የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ላይ ባደረሱት የመሳሪያ ድብደባ መዉሰላቸዉን የአካባቢዉ ኗሪዎች ይናገራሉ። ለጥቃቱም ጠንከራ አፀፋ ተሰንዝሯል። ደቡባዊ መቃዲሾ በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ወታደሮች መንደር ላይ ዛሬ የተከፈተዉ ጥቃት ቢያንስ የ14 ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል። የአይን ምስክሮች ለዘጋቢዎች እንደገለፁት ቤታቸዉ ላይ በወደቀ አዳፍኔ ሳቢያም ሰላማዊ ዜጎች ሞተዋል። ሀኪሞችና እማኞች እንደገለፁትም ከሟቾቹ ሌላ 10ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ የፎቶ ጋዜጠኛም በበኩሉ የዛሬ 17ዓመት የሶማሊያ ሚሊሺያዎች የዩናይትድ ስቴትስን ሄሊኮፕተር ተኩሰዉ በጣሉበት ስፍራ የሁለት ኢትዮጵያዊና የአንድ ሶማሊያ ዜጋ ሟች ወታደሮችን አስከሬን ሲጎትቱና በእሳትም ሲለኩሱ ማየቱን ገልጿል። በአጎራባቿ ባሩዋና የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተበሳጩ ሰልፈኞችም የሞቱት ወታደሮች አስከሬን በእሳት ሲጋይ ከማየታቸዉ በላይ አልፈዉም በሽግግር መንግስቱና በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ዛቻ ሰንዝረዋል።

የሽግግር መንግስቱ በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች እየተረዳ ተጠናክረዋል ሲባል የከረመዉን የእስላማዊ ሚሊሺያዎች ካባረረ ወዲህ መቃዲሾን ለማረጋጋት ጥረቱን ቢቀጥልም ተስፋ የሚሰጥ ነገር አልታየም። ሶማሊያን የማረጋጋቱን ሃላፊነት ከኢትዮጵያ ወታደሮች ሊረከብ ወደሶማሊያ ምድር የገባዉ የመጀመሪያዉ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ከዑጋንዳ መሆኑ ይታወቃል። በስፍራዉ ከሚገኙት መካከል ሻምበል ፓዲ እንኩንዳ በሶማሊያ የሚታየዉ የጥቃት እርምጃ ያልተጠበቀ አይደለም ባይናቸዉ።

«ይህን መሰሉን ጥቃት አስቀድመን አስበነዋል። በመቃዲሾ ይህ በጣም የተለመደ ነዉ። ሰላማዊ ቢሆን ኖሮ እኛም እዚህ ባልተገኘንም ነበር። ቢሆንም እንኳን አንፈራም፤ ሁሉም እንደታቀደዉ እየሄደ ነዉ ተልዕኳችንንም ይህ አያጎድለዉም።»

ህዝቡ በተደጋጋሚ ባካሄዳቸዉ የተቃዉሞ ሰልፎች በምድሪቱ የሚገኙ የዉጪ ወታደሮች እንዲወጡለት ሲጠይቅ፤ ከዚያም አልፎ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደስፍራዉ መንቀሳቀሱን ሲያወግዝ እንደሰነበተ የሚታወስ ነዉ። ሰላም ለማስከበር ከዑጋንዳ የተነሳዉ ጦርም መቃዲሾ አዉሮፕላን ማረፊያም ሆነ የባህር ወደብ ሲደርስ የተቀበለዉ የጥቃት እርምጃ ነበር። ሻምበሉ ህዝቡ በመምጣታችን ደስተኛ ነዉ ያለን ግንኙነትም ሰላማዊ ነዉ ይላሉ

«እኛ እዚህ በመሆናችን በጣም ተደስተዋል። በጎዳናዉ ቅኝት በምናደርግበት ወቅት ምን እንደተከሰተ ይነግሩናል ይጠቁሙናል። አሁን ራሱ ፈንጂ የተቀበረበትን አካባቢ አሳይተዉን አክሽፈነዋል። ይህም የሚያሳየዉ ተጨማሪ መረጃም እንደሚሰጡን ነዉ ያም እዚህ የሚኖረንን ተልዕኮ ለማሳካት ይረዳናል።»

ሶማሊያ ከኢራቅ የባሰች የጦር አዉድማ ልትሆን ትችላለች የሚለዉ የአካባቢዉ ፖለቲካ ተንታኞች ግምት አሁንም ስጋት ጨምሮ እንደቀጠለ ነዉ።