1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንሶ በሰገን ዞን ሥር እንዲሆን መደረጉ ያስከተለዉ ቅሬታ ተባብሶ መቀጠሉ፤

ሐሙስ፣ መስከረም 26 2009

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በልዩ ወረዳነት የቆየዉ ኮንሶ በሰገን ዞን ሥር እንዲጠቃለል መደረጉ ያስከተለዉ ቅሬታ ተባብሶ አካባቢዉ ዉጥረት ግጭትን ሲያስተናግድ ቆየ።

https://p.dw.com/p/2Qz1Y
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

Konso Tenstion - MP3-Stereo

ከስፍራዉ የተላከልን አንድ መልዕክት እንደሚያመለክተዉ ኗሪዎች ለስብሰባ ዉጡ የሚለዉን የመንግሥት ባለስልጣናት ትዕዛዝ አለመቀበላቸዉ በኮንሶ ዉጥረቱን አባብሶታል።

የኮንሶ አለመረጋጋት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን በዋትስአፕ ጥቆማ የላኩልን አድማጭ የመንግሥት ወታደሮች ከተማዋን ተቆጣጥረዉ ደስ ያላቸዉን ያስራሉ ይገርፋሉ፤ ከፈለጉም ይገድላሉ፤ ይላሉ። ባለስልጣናቱ ኗሪዎችን ለስብሰባ ዉጡ እያሉ መለፈፍ ከጀመሩ 7 ቀን ቢሞላም የሚፈለገዉን ያህል ህዝብ ባለመዉጣቱም ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ማስገደድ እና በየቤቱም መግባት ጀምረዋል ሲሉም ይዘረዝራሉ። ሁኔታዉን እንዲያስረዱን በስልክ ያገኘናቸዉ የኮንሶ ኗሪ፤ እንደኗሪዉ ገለፃ በየቤቱ አሁን የሚገኙት ሕፃናት፤ ሴቶች እና አዛዉንት ናቸዉ። ወጣቶችም ሆኑ አዋቂ ወንዶች በአካባቢዉ አይገኙም፤ ጫካ ገብተዋል። እሳቸዉ ያሉትን እዚያዉ ደዉለን ያነጋገርናቸዉ ጫካ ዉስጥ ነን ያሉን አንድ ኗሪ ያረጋግጣሉ። ዋናዉ ግፊትም ይላሉ ያነሳችሁትን ጥያቄ ተዉት የሚል ነዉ፤ ያ ካልሆነ በሚል ተከትሏል ያሉት ዛቻም አለ።

Omo Dam Projekt in Äthiopien
ምስል Survival International

የኮንሶ ሕዝብ ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ገመቹ ገንፋም ይህኑ ነዉ ያጠናከሩት። እሳቸዉም እንደሌሎች ወገኖቻቸዉ ጫካ ዉስጥ ለመኖር መገደዳቸዉ የገለፁት አቶ ገመቹ የባለስልጣናት እና የሕዝቡ ፍጥጫ ስብሰባ ዉጡ አንወጣም የሚለዉ መሆኑን ገልጸዋል። የሰዉ ቤት ንብረቱን ጥሎ ወደጫካ መሄድም ያስከተለዉ ሌላ ችግር መኖሩንም ይናገራሉ።

አቶ ገመቹ እና የኮንሶን ሁኔታ እንድንከታተል ጥቆማ ከላኩልን አድማጭ እንደተረዳነዉ አሁን በከተማዋ ሥራ የሚሠራዉ የኮንሶ ሃኪም ቤት ብቻ ነዉ። እዚያም ቢሆን ሃላፊዎቹ ሰሞኑን ታስረዉ ነዉ የተለቀቁት። ይህናን ሌሎች ያነጋገርናቸዉ ወገኖች የገለጹልንን ዝርዝር ችግሮች በመያዝ የአካባቢዉን ባለስልጣናት ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደርግናቸዉ የስልክ ጥሪዎች ባለመመለሳቸዉ፤ ሃሳባቸዉን ማካተት አልቻልንም።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ