1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ከጉም እና ጤዛ ውሃ መሰብስቢያ በዶርዜ ተተክሏል

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2009

ደቡብ ኢትዮጵያ፡፡ ጋሞ ጎፋ ዞን፡፡ የአማራና ቦዶ ቀበሌ ነዋሪዎች  ጭፈራ ላይ ናቸው፡፡ ሲያሻቸው በቀዬያቸው ቋንቋ፣ ሲላቸው ደግሞ በእግር ኳስ ጨዋታ ድል ወቅት በተለመደ ባህላዊ ዜማ “የእርግብ አሞራ እያሉ”፡፡ የቀበሌውን ነዋሪዎች እንዲህ ያስጨፈራቸው በአካባቢያቸው “ዋርካ” መተከሉ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2dXSJ
Äthiopien Warka Water Projekt
ምስል Warka Water

ደቡብ ኢትዮጵያ የተሞከረዉ የዉኃ መሠብሰቢያ ቋት

“ለአንድ ዋርካ መተከል ፈንጠዝያ ምነው?” ለምትሉ ነገሩን በቅጡ ለመረዳት የአርቱሮ ቪቶሪዮን ታሪክ ማድመጥ አለባችሁ፡፡ አርቱሮ ቪቶሪዮ በሙያው የተመሰገነ እና ሽልማቶች የተበረከቱለት ጣሊያናዊው አርክቴክት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ያስተሳሰረው ታሪክ መነሾ የቀድሞ መስሪያ ቤቱ ኤርባስ የአውሮፕላን አምራች ድርጅት ነው፡፡ መቀመጫውን ቱሉዝ ፈረንሳይ ያደረገው ኤርባስ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሆኑ አውሮፕላኖች ለማምረት ሲስማማ የአውሮፕላኖቹን ውስጠኛ አካል ንድፍ ለሚያቀርቡለት ባለሙያዎች ጥሪ ያደርጋል፡፡ ቀድሞም እንዲህ ዓይነት የስራ ልምድ የነበረው አርቱሮ ለስራው ይረዳው ዘንድ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ይወስናል፡፡ ጊዜው በጎርጎሮሳዊው 2012 ነበር፡፡ 

በዚህ ጉዞው እንደ እርሱው አርክቴክት ከሆኑ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ታደሰ ግርማይ ጋር ይገናኛል፡፡ ታደሰ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አካል በሆነው ቀድሞ ህንጻ ኮሌጅ ተብሎ በሚታወቀው የአርክቴክቸር፣ ህንጻ ግንባታ እና ልማት ተቋም መምህር ናቸው፡፡ ሁለቱ ባለሙያዎች ሀገር ለመጎብኘት በዞሩባቸው ቦታዎች ጣሊያናዊው በየቦታው ያለ አንድ ብርቱ ችግር ያስተውላል፡፡

“የሰሜኑን ክፍል ስንጎበኝ ሴቶች፣ ህጻናት፣ እናቶች ልጅ አዝለው ውሃ ለመቅዳት ሲጓዙ ብዙ ነገር አየን እና ጥያቄዎች ሲጠይቀኝ ያለውን ነገር ነገርኩት፡፡ እኔም ሳድግ ውሃ መቅዳት አይነት ተመሳሳይ ነገሮች እንደነበሩ እና ልጆች ለቤተሰቦቻቸው እንዴት እንደሚያግዙ የሚያሳየን ነገር ስለነበር በእሱ ዙሪያ ስናወራ ፕሮጀክት ለምን አንቀርጽም እና ውሃ ላይ ለምን አንሰራም የሚል ነገር መጣ” ይላሉ አቶ ታደሰ፡፡  

Äthiopien Warka Water Projekt
ምስል Warka Water

በኢትዮጵያ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዓይን የተመለከተው አርቱሮ የችግሩን ግዝፈት ለመረዳት ጥናቶችን ተመልክቷል፡፡  በሀገሪቱ ያሉ ዋነኛ የጤና ችግሮች በንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የንጽህና እጦት ምክንያት የሚሰራጩ በሽታዎች እንደሆኑ ከጥናቶቹ ተገነዘበ፡፡ በዚያው ዓመት የወጣውን የተባበሩት መንግስታት ህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዘገባ ሲያገላብጥ ደግሞ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በንጹህ ውሃ እጥረት ምክንያት በሚከሰቱ የተቅማጥ በሽታዎች 54‚000 ህጻናት እንደሚሞቱ ተረዳ፡፡

“ቁጥሮች እንደሚነግሩን ከኢትዮጵያ ህዝብ 60 ከመቶው የእዚህ ችግር ተጠቂ ነው፡፡ ለአንድ ሰው ለመጠጥ እና ንጽህናውን ለመጠበቅ በቀን 15 ሊትር በቂ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ይህን ያህል አነስተኛ መጠን ያለው ውሃ እንኳ የላቸውም” ሲል አርቱሮ ይናገራል፡፡

ጣሊያናዊው አርክቴክት ለዚህ ችግር መፍትሄ ለማግኘት ዲዛይን የማድረግ ችሎታውን ተግባር ላይ አውሏል፡፡ መፍትሄው በቀን ከ50 እስከ 100 ሊትር ውሃን ከዝናብ፣ ከጉም፣ እና ጤዛ ሰብስቦ ማጠራቀም የሚችል ቋት መፍጠር ነው፡፡ ለንድፉ የፈጠራ ሀሳብ ለማመንጨት ተፈጥሮን መነሻ አድርጓል፡፡ ከጢንዛዛ በውሃ አጥር ቦታዎች ውሃን የማሰባሰብ ብልሃትን፣ ከሸረሪት ድርን፣ ከቁልቋል- ጭጋግን ወደ ውሃ እንዴት እንደሚቀይር እና ከ“ሎተስ” አበባ - በቅጠሎች ውሃ መቋጠርን ለመኮረጅ ሞክሯል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮጵያ የተመለከታቸውን ነገሮችንም በግብዓትነት ተጠቅሟል፡፡ የውሃ መሰብሰቢያው ቋት ስያሜ እንኳ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የሀገሬው ሰዎች ለክፉም ለደጉም ከዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበው እንደሚመክሩ ልብ ያለው አርቱሮ ቋቱን “ዋርካ” ሲል ሰይሞታል፡፡ ቅርጹን ደግሞ ከሙዳይ እና መሶብ ተበድሯል፡፡ ኢትዮጵያዊ እና አፍሪካዊ የሽመና ጥበብን ደግሞ ቋቱን ለሚያለብሰው ዳንቴል መሳይ መረብ ተጠቅሟል፡፡ የዶርዜ ቤት አሰራር ዘዴም አልቀረ፡፡

Äthiopien Warka Water Projekt
ምስል Warka Water

“ያለነው አፍሪካ ውስጥ እንደመሆኑ በአካባቢው ያለውን የማምረት ዘዴ ተመልክተናል፡፡ በአፍሪካ ቤቶችን እንዴት እንደሚገነቡ ተመልከታችኋል? በጣም በቀላሉ ነው፡፡ ከአካባቢያቸው ያገኙትን ጥሬ ዕቃ ይጠቀማሉ፡፡ ሲሰሩም በጋራ ሆነው በማህብረሰብ ስራ መልክ ነው፡፡ ቤት ሲሰራ የሚቆምበት መወጣጫም አይጠቀሙም፡፡ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክ ስራዎች የሉም፡፡ ሁሉንም ነገር በእጅ ቢሰራም ውብ ቤቶች ነው የሚገነቡት፡፡ በዚያ ላይ ቤቶች ረጅም ጊዜ የሚቆዩ ናቸው” ሲል አርቱሮ “TEDx” በተሰኘው ሰዎች ለየት ያለ ሀሳባቸውን በሚያጋሩበት መድረክ ተናግሮ ነበር፡፡   

ተፈጥሮ እና የአካባቢ ዕውቀትን ያቀናጀው “የዋርካ የውሃ ቋት” ከወረቀት እና ኮምፒውተር ተሻግሮ በሙከራ መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው በቀድሞው ህንጻ ኮሌጅ ግቢ ነው፡፡ አንድ ሜትር በማይሞላ ርዝመት ከቀርከሃ ከተሰራው ከዚህ የውሃ ቋት በኋላ በተሻሻለ ንድፍ ሁለተኛው ሙከራ የተካሄደው በቬኒስ ጣሊያን ነበር፡፡ በእንደዚህ አይነት ቋት ውሃ ከአየር ላይ መሰብሰብ ይቻል እንደው ለመሞከር ግን ወደ ገጠራማው ኢትዮጵያ ክፍል መሄድ ግድ አለ፡፡ ለሙከራው ተስማሚ የሚሆነው ጭጋግ እና ጤዛ በቀላሉ የሚገኝበት ተራራማ ቦታ በመሆኑ ቦታ ይመረጥ ጀመር፡፡ በስተመጨረሻ ዶርዜ የእነአርቱሮን ቀልብ ገዛ፡፡ 

አቶ ጸሀይ ቦጋለ በዶርዜ ወረዳ የአማራ እና ቦዶ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ እነ አርቱሮ ወደ አካባቢያቸው ሲመጡ በመጀመሪያ ካነጋገሯቸው ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በጨንቻ ተራራ ላይ በተሰቀለው ደጋማ መንደራቸው “ዶርዜ ሎጅ” የተሰኘ የራሳቸውን እንግዳ ማስተናገጃ ገንብተው ያስተዳድራሉ፡፡ በዚያው በደቡብ ክልል ከ10 ዓመት በላይ በገጠር ውሃ ልማት ዘርፍ ለሰሩት ለአቶ ጸሀይ የእነ አርቱሮን ለየት ያለ እና በንድፍ ደረጃ ያለን ሀሳብ መረዳት አልከበዳቸውም፡፡ እነአርቱሮ “የዋርካ የውሃ ቋት”ን በአማራ እና ቦዶ ለመትከል ሲነሱ አቶ ጸሀይ በመንደራቸው ያለውን የውሃ ችግር በመጥቀስ ማህብረሰቡን የማሳመን እገዛ አድርገዋል፡፡  

“ህብረተሰቡ የውሃ ችግር ስለነበረበት እዚያው መንደራቸው ላይ ይህን ነገር ብተክል ብሎ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ጠየቃቸው፡፡ ህዝቡም ደግሞ በጥሩ አዎንታዊ መልኩ መለሱለት፡፡ የእኛ መንደር አማራና ቦዶ በአብዛኛው ተራራማ ሆኖ ድንጋያማ አካባቢ ላይ ነው ያለው፡፡ ያው ከመንደራችው ተነስተው ትንሽ ሸለቆ ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ ምንጮች ለማግኘት በትንሹ ሁለት ሰዓት ያስኬዳቸዋል” ይላሉ አቶ ጸሀይ፡፡

Äthiopien Warka Water Projekt
ምስል Warka Water

ከአንድ ወር ዝግጅት በኋላ ህብረተሰቡ በመረጠው ቦታ የዋርካ የውሃ ቋት ተተከለ፡፡ ቋቱን በመትከል ሂደት ሲሳተፍ የነበረው የአካባቢው ነዋሪ በስተመጨረሻ ሁሉም ነገር ተጠናቆ ሲያይ ደስታውን በጭፈራ ገልጿል፡፡ በዚህ ዝግጅት መግቢያ የሰማችሁት የጭፈራ ድምጽ እንግዲህ ከዚያ የተቀነጨበ ነበር፡፡ ቋቱ እንደታሰበው 350 አባወራዎች ለሚኖሩበት መንደር “የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅራቢ ሆነ ወይስ በጅምር ቀረ?” ስል አቶ ጸሀይን ጠይቄያቸው ነበር፡፡ 

“ህብረተሰቡ ያው እናቶች ሁሉ ውሃ ከዚያ ይጠቀሙ ነበር፡፡ በአብዛኛው ግን የተጠቀሙት በዝናባማ ወቅት ደመና ሲኖር ነው፡፡ ምክንያቱም ከደመና ላይ ትንንሽ ጠብታ አይነት ነገር ይሰባሰብና ያ ነው ወደ ማጠራቀሚያው ውስጥ የሚገባው፡፡ ከዚያ ከማጠራቀሚያው በቧንቧ መልኩ ወጥቶ የሚጠቀሙት፡፡ ጸሀይ በሚሆንበት ሰዓት ምንም ነገር አይገኝም” ሲሉ አቶ ጸሀይ ይመልሳሉ፡፡   

የውሃው መጠራቀሚያ እስካለፈው ወር ድረስ አግልግሎት ይሰጥ እንደነበር አቶ ጸሀይ ይናገራሉ፡፡ ከአንድ ወር ወዲህ ግን የቋቱ ምሶሶ በቀርከሃ በመሰራቱ እና ስሩ በምስጦች በመበላቱ የመፍረስ አዝማሚያ ላይ በመሆኑ አገልግሎት ማቋረጡን ያስረዳሉ፡፡ እንዲህ አይነት በሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እና ከየአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆኑ ቋቶችን ለመስራት በየጊዜው የተሻሻለ ንድፍ እንደሚዘጋጅ አርክቴክቱ አቶ ታደሰ ይገልጻሉ፡፡ ከ“ዋርካ ውሃ” ይፋዊ ድረ-ገጽ  በተገኘ መረጃ መሰረት እስካሁን 12 ዓይነት የውሃ ቋቶች በተለያየ ቦታ ተተክለው ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡ 

በዶርዜ የተጀመረው የ“ዋርካ” የሙከራ ጉዞ ወደ ጣሊያን፣ ሊባኖስ፣ ብራዚል እና ቻይና ተሻግሯል፡፡ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር በታይዋን ቴይፒ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የዲዛይን ውድድር ላይም አሸናፊ ሆኖ ተመርጧል፡፡ “ዋናው እና የመጀመሪያው ነገር ከአካባቢ ያለን ችግር በአካበቢ መፍታት መሞከር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዘላቂ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተፈጥሮ ጋር ምንም ዓይነት ግጭት ሳይፈጥሩ፣ ተፈጥሮን መነሻ በማድረግ አንድን መፍትሄ ማምጣት ነው” ሲሉ አቶ ታደሰ “ዋርካ ውሃ” የተመረጠበትን ምክንያት ያብራራሉ፡፡  

Äthiopien Warka Water Projekt
ምስል Warka Water

አሁን ባለውም ሆነ እየተሻሻሉ በመጡት ንድፎች የተሰሩ የዋርካ የውሃ ቋቶችን ራቅ ባሉ እና ገጠራማ ቦታዎች በመትከል የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ ከ500 እስከ አንድ ሺህ ዶላር ይጠይቃል፡፡ “አንድ ሺህ ዶላር ለገጠር አካባቢዎች ወድ ነው?” ለሚሉ አቶ ታደሰ ምላሽ አላቸው፡፡

“አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ብር ነው የሚያስወጣን ግን በብዛት ሲመረት ከ500 እስከ አንድ ሺህ ዶላር ባለው ሰርተን መጨረስ ይቻላል ነው፡፡ አንድ ጫማ ሲሰራ እና መቶ ጫማ ሲመረት ወጪው ይለያያል፡፡ ወጪው እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው፡፡

ትልቁ ነጥብ ግን ውሃ እጥረት ላለባቸው ቦታዎች ለሁሉም የሚሰራ ቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ብንደርስ 500 ዶላርም አይደለ አንድ ሺህ ዶላርም ውድ አይሆንም፡፡ ለምን? የዓለምን የውሃ አጠቃቀም ስንመለከት እነ ዱባይ ናቸው ብዙ ውሃ የሚጠቀሙት፡፡ [በነፍስ ወከፍ] እስከ 500 ሊትር በቀን ይጠቀማሉ፡፡ ሌላ አሜሪካም እነ አውሮፓም ከመቶ ሊትር በላይ የሚጠቀም የለም፡፡ እኛ ሀገር ከ40 ሊትር በላይ አንጠቀምም፡፡ እርሱንም ስለምናባክን ነው፡፡ እና የውሃ ችግር ላለበት አካባቢ በአንድ ሺህ ዶላር ያን ያህል ውሃ በቀን የሚያመነጭ ከሆነ በብዛት ሲመረት በ500 ዶላር ከዚያም በታች ከሰራነው ስኬታማ ነው” ሲሉ አቶ ታደሰ የዋርካን አዋጪነት ይመሰክራሉ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ