1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቢያፍራ የርስበርስ ጦርነት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1 2009

በደቡብ ምሥራቃዊ ናይጀሪያ የሚገኘው የቢያፍራ ግዛት ከሀገሪቱ መገንጠሉን ይፋ ካደረገ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በጎርጎሪዮሳዊው ሀምሌ ስድስት፣ 1967 ዓም በሀገሪቱ የርስበርስ ጦርነት የተጀመረበት 50ኛ ዓመት ከሶስት ቀናት በፊት ታሰበ።  

https://p.dw.com/p/2g5nl
Karte Biafra Nigeria
ምስል DW

Fokus Afrika A (08.07.2017) - MP3-Stereo

ግዙፏ አፍሪቃዊት ሀገር ናይጀሪያ ትከፋፈል የሚል ክርክር በአሁኑ ጊዜ በጋዜጦች እና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠናክሮ እየተካሄደ ነው። ቢያፍራ ከናይጀሪያ ተገንጥላ ነፃ መንግሥት ታቋቁም የሚለውን ሀሳብ ብዙዎች እንደገና በአዕምሯቸው ማሰላሰል ይዘዋል። ለሀሳቡ ደጋፊ ለማግኘት ከሚደረገው ክርክር ጎን ዘረኝነትን የሚያስፋፋ ጥላቻ አዘል ፕሮፓጋንዳም መካሄዱ አልቀረም። 
የርስበርሱ ጦርነት የተጀመረው የደቡብ ምሥራቃዊ ናይጀሪያ ግዛት፣ ቢያፍራ ራሱን በጎርጎሪዮሳዊው ግንቦት 30፣ 1967 ዓም ነፃ መንግሥት ብሎ ካወጀ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነበር። ከናይጀሪያ ተገንጥላ ለሶስት ዓመታት ነፃ ሬፓብሊክ ከማቋቁሟ እና ከርስበርሱ ጦርነት በፊት በሀገሪቱ ሁለት መፈንቅለ መንግሥት፣ ጭፍጨፋ መካሄዱ እና በደቡብ ምሥራቅ ናይጀሪያ የሚኖረው በብዛት የኢግቦ ጎሳ አባላትም በማዕከላዊው መንግሥት የተገለሉ ያህል እንደተሰማቸው ይነገራል።   
ሀምሌ ስድስት፣ 1967 ዓም የተጀመረው የርስበርስ ጦርነት እስከ ጎርጎሪዮሳዊው ጥር፣ 1970 ዓም የቀጠለ ሲሆን፣ የ2,5 ሚልዮን ሰው ሕይወት አጥፍቷል።  ይሁን እንጂ፣ በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሰው ስለዚሁ ሶስት ዓመት የዘለቀ እና የቢያፍራውያኑን ዓላማ ከግብ ያላደረሰ ጦርነት ታሪክ በሀገሪቱ ለብዙ አሰርተ ዓመታት በሀገሪቱ በፍጹም አልተነሳም ነበር፣ በትምህርት ቤቶችም ሆነ በሌሎች የኑሮ ዘርፎችም በይፋ አንዳችም መረጃ አልቀረበም ነበር።  የ23 ዓመቱ ሮይ ኡዴህ ኡባካም ስለዚሁ ታሪክ ያን ያህል የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ይናገራል። ኡዴህ ኡባካ ለመገንጠል የሞከረው ግዛት ርዕሰ ከተማ ከየሆነችው የኤኑጉ ተወላጅ ነው። የቢያፍራ ጦርነት በናይጀሪያ የትምህርት ስርዕት ውስጥ ያን ያህል ቦታ እንዳልተሰጠው ነው የሚያስታውሰው።
« የለም፣ በትምህርት ቤት ስለ ቢያፍራ ተነስቶ አያውቅም። ግን ፣ ባንድ ወቅት ማህበራዊ ሳይንስ ስማር ፣ በማስተማሪያው መጽሀፍ ላይ አንድ ምዕራፍ ነበር ስለ ቢያፍራ የሚያወሳ። ይህ ምዕራፍ ግን ቢያፍራን በአጭሩ ብቻ ነበር ያነሳው ። በሁለት ወይም በሶስት ገጾች ብቻ  ነበር ጠቀስ አድርጎ ያለፈው። » ኡዴህ ኡባካ ስለ ቢያፍራ ያለውን ዕውቀት ያገኘው ከትምህርት ቤት ሳይሆን   በህፃንነታቸው በወታደርነት ካገለገሉት አባቱ ሲሆን፣ ስለ የርስበርስ ጦርነቱ ያዩትን የራሳቸውን የግል ተሞክሮ አጫውተውታል። ሮይ ኡዴህ ኡባካም  ስለ የርስበርስ ጦርነቱ መረጃውን  በጽሁፍ ከተያዜ ተጨባጭ ማስረጃዎች ሳይሆን፣ ከግል ተሞክሮ በመነሳት ግለሰቦች ካቀረቧቸው ትረካዎች  ያገኘው ትውልድ አካል ነው። የናይጀሪያ ብሔራዊ ፈተና ምክር ቤት፣ በምህፃሩ  «ኔኮ»  ተብሎ የሚጠራው የሀገሪቱ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፈተና ተቆጣጣሪ ተቋም  የቀድሞ  ሊቀ መንበር ፓዲ ኬምዲ ንጆኩ እንደሚሉት፣ ይኸው ገሀድ ናይጀሪያ ስላለፈው የርስበርስ ጦርነት ታሪኳ በግልጽ እንዳትወያይ እና ተጨባጭ መረጃ እንዳታቀርብ  አከላክሏታል ። 
« እያንዳንዱ ናይጀሪያዊ ህፃን ከነፃነት እስከ አሁን ስላለው የሀገሩ ታሪክ ሊማር ይገባል። ትምህርቱ ስለ ቢያፍራ ብቻ መሆን የለበትም። ነፃነታችንን እንዴት እንዳገኘን ማስተማር አለብን። ስለመፈንቅለ መንግሥቱ፣ ስለ የርስበርሱ ጦርነት እና በርስበርሱ ጦርነት ስለተሳተፉትም በግልጽ መንገር ይኖርብናል። ታሪክን በትክክል አስተምረን ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ላይ ባልተገኘን ነበር። »
የራስን ታሪክ አለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ ላለማንሳት የተደረገው ሙከራ የናይጀሪያ መንግሥት ለሶስት ዓመታት ነፃ መንግሥት ካቋቋመችው ቢያፍራ ጋር ያካሄደው የርስበርስ ጦርነት ጥር ፣ 1970 ዓም ካበቃ በኋላ ስራዬ ብሎ የተከተለው ፖሊሲ ነው። በዚያን ጊዜ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ እንደሌለ ነው የተገለጸው። ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ ከጦርነቱ ጋር  በተያያዘ ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበር የታሰሩት፣ ለፍርድ የቀረቡም አልነበሩም ማለት ይቻላል። ስለጦርነቱም ሆነ በዚያን ወቅት ተፈፀመ ስለሚባል የጦር ወንጀል  በአንድም ቃል አልተነሳም ነበር። በዚህ ፈንታ ተገንጥላ የነበረችው ቢያፍራ እና የኢግቦ ጎሳ የሆነው ሕዝቧ እንደገና ከናይጀሪያ ጋር እንዲዋኃድ ተደርጓል።  የናይጀሪያ መንግሥት በጦርነቱ የወደመውን አካባቢ መልሶ የመገንባቱ እና የዕለት ተዕለቱ ኑሮ ናይጀሪያውያንን ያቀራርባል የሚል እሳቤን ነበር ያራመደው። በደቡብ ምሥራቃዊ ናይጀሪያ የሚኖረው ሕዝብ ይህንኑ የናይጀሪያ መንግሥት ዘዴን እስከዛሬ ድረስ አጥብቆ ይተቻል።   የናይጀሪያ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ  ሀኬም ባባ አህመድ ግን ይኸው የመንግሥቱ ዘዴ የተሳካ ነበር ይላሉ። ባባ አህመድ የናይጀሪያ መንግሥት ከ50 ዓመት በፊት የተከተለው ፖሊስ ትክክለኛ ነው በማለት፣ ያለፈውን ታሪክ ማንሳት እንደማያስፈልግ አመልክተዋል።
« በኔ አስተሳሰብ ናይጀሪያውያን እርቀ ሰላም አውርደዋል። ይህንንም ያደረጉት የርስበርሱ ይሁን እንጂ፣ የሀገሪቱን አንድነት ስጋት ላይ የጣሉ እና ናይጀሪያውያንን እርስበርስ ሊያጋጩ የሚችሉ ሌሎች ብዙ ጉዳዮች አሉ። ይሁንና፣ እርቀ ሰላም እንዴት ማውረድ እንዳለብን ተምረናል። በጣም ጥቂት ሀገራት ብቻ እኛ ያሳለፍነውን ዓይነት ችግር መቋቋም በቻሉ ነበር። »
የአንድ ወንጀለኛ ድርጅት አባል ናቸው በሚል ክስ ወህኒ ቤት ወርደው የነበሩት በምህፃሩ «ኢ ፒ ኦ ቢ» የተባለው የቢያፍራ ጥንታውያን ተወላጆች ንቅናቄ መሪ  ንናሚዲ ካኑ  እጎአ ከ2015 ዓም ወዲህ ባደረጉት ትግላቸው የቢያፍራ ጉዳይ  ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድረገዋል።አሁን እንደገና ቢያፍራ ነፃ መንግሥት ታቋቁም የሚለው ጥያቄ እየጎላ የመጣበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ባባ አህመድ ገልጸው፣ ከዚሁ ጥያቄ በስተጀርባ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ አስረድተዋል። 
«  ቢያፍራ ለናይጀሪያ ችግር መፍትሔ አይሆንም። ግን፣ የቢያፍራ ጉዳይ ናይጀሪያውያን መሰረታዊ በሆኑ ፣ ለምሳሌ፣ ድህነት፣ ምግባረ ብልሹ አስተዳደር እና የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ይዞታ በተሰኙት ጉዳዮች ላይ በግልጽ መወያየት እንዳለባቸው ያሳያል። ወጣት ናይጀሪያውያን የስራ ቦታ ያስፈልጋቸዋል። ስራ እስካላቸው ድረስ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ፣ በምሥራቅ፣ ሰሜን ወይም በምዕራብ  ቢኖሩ ግድ የላቸውም። ይመቻቸዋል። »
ይሁንና፣ ሁሉም ናይጀሪያውያን እንደ ባባ አህመድ ብሩህ አመለካከት የላቸውም። ፓዲ ኬምዲ  እርግጥ፣  ይህንኑ የባባ አህመድ አመለካከት በከፊል ይጋራሉ፣ ግን፣ ቀደም ሲል በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ብቻ መወያያቱ ብቻውን በቂ ሆኖ አላገኙትም። ከዚሁ ጎን በርስበርሱ ጦርነት ታሪክም ላይ ውይይት መደረግ አለበት ባይ ናቸው። ይህ ዓይነቱ ውይይት አንዱ ሌላውን ጥፋተኛ ለማድረግ ሳይሆን፣ እንደ ፓዲ ኬምዲ አስተሳሰብ፣ ታሪክን ለማስታወስ እና ካለፈው ታሪክ ትምህርት ለመቅሰም ይረዳል።
«ይህ አስፈላጊ ነው። በያመቱ የናጀሪያ ጦር ቀን የሚባል ለሀገር ሕይወታቸውን የሰው ወታደሮችን የምናስብበት ቀን አለ። ሀምሌ ስድስት ቀን።  እንደኔ አስተሳሰብ ፣ ከዚህ አንድ ርምጃ ወደፊት በመሄድ፣ ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ አለመግባባቶች በሚያሳዝን ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡትን ሁሉ ማስታወስ እንችላለን። »
ፓዲ ኬምዲ በጎርጎሪዮሳዊው  1960ኛዎቹ ዓመታት በናይጀሪያ የታዩ ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች መልስ ሳይሰጣቸው እንደታለፉ ነው የሚሰማቸው።  

NIGERIA Biafra Aba Demonstration
ምስል Getty Images/AFP/P. U. Ekpei
Nigeria Biafra | Stadtansicht
ቢያፍራምስል DW/K. Gänsler
Nigeria Enugu Erinnerungen Biafra
ምስል DW/Katrin Gänsler
Soldaten im Biafra-Krieg 1967 - 1970
ምስል AFP/Getty Images

አርያም ተክሌ/ካትሪን ጌንስለር

ልደት አበበ