1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ

ሐሙስ፣ የካቲት 18 2002

ዓለምአቀፉን የልማት ዕርዳታ አከራካሪ የሚያደርገው የፍቱንነቱ ጥያቄ ብቻ አይደለም። ዕርዳታው በተገባው ቃል መጠን ገቢር የመሆኑም ጉዳይ በየጊዜው ብዙ የሚያነጋግር ነው።

https://p.dw.com/p/MA71
ምስል dpa/DW

በአሕጽሮት ኦ.ኢ.ሲ.ዲ. በመባል የሚታወቀው የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ዕርዳታው በያዝነው 2010 ዓ.ም.ም. በተባለው መጠን እንደማይቀርብ ዛሬ ፓሪስ ላይ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። ቃልን በሟጋደሉ ረገድ በርከት ያሉ አገሮች ሲጠቀሱ በድርጅቱ ይበልጡን የተወቀሰችው ደግሞ ጀርመን ናት። በዘገባው እንደተጠቀሰው በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉ አገሮች ከአምሥት ዓመታት በፊት ተጨማሪ ሃምሣ ሚሊያርድ ዶላር ለማቅረብ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉ አገሮች ተገብቶ ከነበረው ቃል ዘንድሮ እንዲያውም ዕርዳታው በ 21 ሚሊያርድ ያነሰ ነው የሚሆነው።

ከ 49 ዓመታት በፊት ፓሪስ ላይ የተቋቋመውና በዚያው ተቀማጭ የሆነው የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት፤ በአሕጽሮት ኦ.ኢ.ሲ.ዲ. በምጣኔ-ሐብት ፖሊሲ ላይ ውይይት የሚያካሂድ ዓለምአቀፍ መድረክ ነው። ድርጅቱ ሰላሣ ዓባል ሃገራት ሲኖሩት በርካታ የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታትን፣ አሜሪካን፣ ጃፓንን፣ ደቡብ ኮሪያን፣ አውስትራሊያን፣ ስዊትዘርላንድንና ቱርክን የመሳሰሉ ሃገራት ይጠቀልላል። የኢንዱስትሪው ዓለም የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ዛሬ ባቀረበው ዘገባ እንዳመለከተው ከጀርመን ሌላ ፈረንሣይ፣ ኢጣሊያ፣ አውስትሪያ፣ ጃፓን፣ ፖልቱጋልና ግርክ የገቡትን ቃል አላከበሩም። የተቀሩት ዓባል ሃገራቱ ግን ቃላቸውን ጠብቀዋል።
ዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም የተገባው ቃል አመከበሩን የሞራል ድህነት ማረጋገጫ ነው ብሎታል። ዕርዳታው እንደተባለው እስከፊታችን 2015 ከ 0.7 ከመቶ ግቡ ማድረሱ ዕውን መሆኑንም አጠራጣሪ ነው ያደረገው። የድርጅቱ የበርሊን ቢሮ ባልደረባ ቶቢያስ ሃውሺልድ እንዳሉት አሁን በጎደለው 21 ሚሊያርድ ዶላር መቶ ሚሊዮን ሕጻናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ በተቻለ ነበር። በነገራችን ላይ የበለጸጉት መንግሥታት ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው 0.7 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ለማዋል የተስማሙት ከሶሥት ዓሠርተ-ዓመታት በፊት ነበር። ይሁንና ቃሉን ገቢር ሲያደርጉ የታዩት ጥቂት አገሮች ብቻ ናቸው። በ 2005 ዓ.ም. ታሪካዊ በተባለው የግሌንኢግልስ የቡድን-ስምንት መሪዎች ጉባዔ እስከዚህ ዓመት የተቀመጠው የ 0.51 ከመቶ ግብም አሁን የኦ.ኢ.ሲ.ዲ. ዘገባ እንደሚያሳየው ገና በተሟላ ሁኔታ አልተደረሰበትም።

ለነገሩ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱ ባወጣው ዘገባ መሠረት የልማት ዕርዳታው ከስድሥት ዓመታት ወዲህ 35 በመቶ ከፍ ብሏል። 15 የአውሮፓ ሕብረት ሃገራትና የድርጅቱ የልማት ዕርዳታ ኮሚቴ ዓባላት በያዝነው ዓመት ከብሄራዊ ገቢያቸው 0.5 ከመቶ የሚሆነውን ለልማት ዕርዳታ ለማዋል ቃል ገብተዋል። ግን ይህ የጀርመንን ይዞታ አይጠቀልልም። አዳዲስ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የጀርመን የልማት ዕርዳታ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አንጻር 0.4 ከመቶውን ድርሻ ቢይዝ ነው። ሆኖም የጀርመን መንግሥት ቃሉን አላከበረም ሲል የተሰነዘረበትን ትችት አይቀበለውም።
የአገሪቱ የልማት ሚኒስትር ዲርክ ኔብል በርሊን ላይ እንዳስረዱት በአውሮፓ ሕብረት ደረጃ በደረጃ የልማት ዕርዳታን የማስተካከል ዕቅድ መሠረት የተቀመጠው የ 0.51 ከመቶ መጠን በዚህ ዓመት ሊሟላ የማይችል መሆኑ ገና ባለፈው ሕዳር ወር ግልጽ ነበር። ሚኒስትሩ ይሁንና ዓለምአቀፍ ግዴታችንን እስከፊታችን 2015 ለማሟላት የልማት ዕርዳታውን እናሳድጋለን ብለዋል። በተጨባጭ በአዲሱ የመንግሥት በጀት ውስጥ የልማቱን ወጪ ካለፈው 2009 ዓ.ም. አንጻር በ 187 ሚሊዮን ኤውሮ ከፍ ለማድረግ ነው የሚታሰበው። የሆነው ሆኖ Welthungerhilfe የተሰኘው የጀርመን የረሃብ ዕርዳታ ድርጅትና የሕጻናት ተንከባካቢው ድርጅት ቴር-ዴስ-ሆምስ የበርሊን መንግሥት ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቱ 0.51 ከመቶውን ድርሻ አለሟሟላቱ ቃልን ማጠፍ ሲሉ ነው የወቀሱት። በዘንድሮው በጀት ላይ ይጨመራል የተባለውን 187 ሚሊዮን ኤውሮም ዝቅተኛ ነው ብለውታል።
ወደ ኦ.ኢሲዲ. እንመለስና በጀርመን መንግሥት አቅጣጫ የሰነዘረው ወቀሣ ለድሆች አገሮች የአካባቢ አየር ጥበቃ የሚሰጠውን ገንዘብ በልማት ዕርዳታ ኮታ ውስጥ መጠቅለልንም ይመለከታል። የጀርመን መንግሥት በበኩሉ ይህ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተለመደ አሠራር ነው ባይ ነው። በበርሊን መንግሥት አመለካከት የአካባቢ አየር ጥበቃም ለልማት አስተዋጽኦ አለው። ስለዚህም ድህነትን በመታገሉ ረገድ የሚጓደል ነገር አይኖርም። ይሁን እንጂ የተለያዩ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች አባባሉን አይቀበሉትም።

ለነገሩ በዓለም ላይ የድሃ-ድሃ የሚባሉት አገሮች በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ ይበልጥ ዕርዳታ ፈላጊ እየሆኑ ነው የሄዱት። የውጭ ንግዳቸው ተዳክሟል፣ በውጭው ዓለም በሚኖሩ ተወላጆቻቸው ዘንድ ሥራ አጥነት መስፋፋቱ የሚላከው ገንዘብ እንዲያቆለቁል ሲያደርግ የውጭ መዋዕለ-ነዋይና ብድርም መጠኑን ቀንሷል። እንግዲህ የልማት ዕርዳታው ቃል አለመከበር በብዛት የሚጎዳው በተለይ እነዚሁኑ አገሮች ነው። አውሮፓ ውስጥ 1.600 የልማት ድርጅቶችን የሚወክለው ማሕበር ኮንኮርድ የአውሮፓን ሕብረት ብዙ ዓባል ሃገራቱ የፊናንሱን ቀውስ ከለላ በማድረግ የልማት በጀታቸውን በመቀነስ በተለይም የድሃ-ድሃ የሆኑትን አገሮች ጎድተዋል ሲል ነው አጥብቆ የተቸው።

በሌላ በኩል በኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅቱ ዘገባ መሠረት በርከት ያሉ ሌሎች አባላቱ የገቡትን ቃል አያከበሩ ነው። አሜሪካ ለምሳሌ ከሣሃራ በስተደቡብ ለሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የምትሰጠውን ዕርዳታ ከ 2004 አንጻር እስከዚህ ዓመት በእጥፍ ለመጨመር ግዴታ ገብታለች። እርግጥ የገቡትን ቃል ገቢር በማድረጉ ረገድ ቀደምቶቹ ትናንሾቹ የአውሮፓ አገሮች ስዊድን፣ ሉክሰምቡርግ፣ ዴንማርክና ኔዘርላንድ ናቸው። እነዚህ ሃገራት ከብሄራዊ ገቢያቸው ለልማት ዕርዳታ የሚያውሉት ገንዘብ ድርሻ ከአንድ በመቶ በላይ፤ ማለት በአውሮፓ ሕብረቱ በወቅቱ ከተቀመጠው መስፈርት እጥፍና ከዚያም የሚበልጥ ነው። የፓሪሱ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በፊታችን ሰኔ ወር ካናዳ ውስጥ በሚካሄደው የቡድን-ስምንት መሪዎች ጉባዔ ላይ የዕርዳታ ቃላቸውን ባላከበሩት አገሮች ላይ ተጨማሪ ግፊት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

የልማት ዕርዳታው ፖሊሲ በዚህ በአውሮፓ በወቅቱ ባለሙያዎችንም በሰፊው እያነጋገረ ነው። አዲሱ የአውሮፓ ኮሚሢዮን በብራስልስ ሥራውን በጀመረበት በዚህ ወቅት የጀርመን የልማት ፖሊሲና የባሕር ማዶ ልማት ኢንስቲቲዩቶች ወይም የአውሮፓን የልማት ፖሊሲ ማዕከል የመሳሰሉት ተቋማት ባለሙያዎች በአውሮፓ የልማት ትብብር ረገድ ቀጣዩን እርምጃ ለመጠቆም ሞክረዋል። እነዚሁ ባቀረቡት የአውሮፓ ሕብረት ሜሞራንደም፤ የሃሣብ ሰነድ መሠረት አውሮፓ ከቀደምቶቹ ከአሜሪካና ከቻይና በስተጀርባ በመቆም መወሰን ሣይሆን ሚናዋን ማጠናከር ይኖርባታል። በሌላ አነጋገር አውሮፓ ራሷን ዓለምአቀፍ ሃይል አድርጋ መመልከቷ ግድ ነው። ለግንዛቤ ያህል የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት በዓለምአቀፍ ልማትና የልማት ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ምርምር ከሚያካሂዱት ቀደምት ተቋማት አንዱ ነው። ገለልተኛ ምርምርን በማካሄድ በጀርመንና በዓለምአቀፍ ደረጃ በበለጸገውና በታዳጊው ዓለም ወቅታዊ ጥያቄዎች ላይ ያማክራል፤ ሥልጠናም ይሰጣል። ልምዱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሆኖ ነው የሚገኘው።

ይሄው የጀርመኑ ተቋምና መሰሎቹ እንደሚሉት የልማት መርህ በአውሮፓ የውጭ ፖሊሲ አቀራረጽ ረገድ ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው ነገር ነው። የልማት ፖሊሲ በመጀመሪያ ደረጃ ዓለምአቀፍ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አካል ሊሆን ይገባዋል። አውሮፓ በዚህ ረገድ አመራሩን መያዝ አለባት ማለት ነው። ለዚህም ዘንድሮ ብዙ አጋጣሚዎች አይታጡም። የያዝነው ዓመት የጀኔቫው የዓለም ንግድ ንግግር የሚቀጥልበት ነው። በመስከረም ወር ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየሙን ግቦች ዕውን በማድረጉ ረገድ እስካሁን የተገኘውን ውጤት በመሪዎች ደረጃ ተሰብስበው ይገመግማሉ። በመሃሉ ሰኔ ወርም የቡድን-ስምንትና የቡድን-ሃያ መሪዎች ካናዳ ውስጥ ተሰብስበው ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የተገኘውን ትምሕርት የሚያጤኑበት ነው። አውሮፓ በነዚህ አጋጣሚዎች ድምጿን ለማጉላት መቻል ይጠበቅባታል።

ሁለተኛው ነጥብ በዓለምአቀፍ ደረጃ የልማት ዕርዳታ መጠንንና ፍቱንነትን በሚገባ ማስቀመጥ ነው። ለምሳሌ የአውሮፓ ሕብረት አገሮች አፍሪቃ ውስጥ የሚያካሂዱት የልማት ተግባር የተቀናበረ ባለመሆኑ አንዱ በሌላው ላይ ሲሰናከል ማየቱ መቀጠል የለበትም። በሌላ በኩል ለአካባቢ አየር ጥበቃ የሚፈሰው ዕርዳታ በሌሎች ዘርፎች ትከሻ የሚካሄድ መሆኑ ከግራ ኪስ አውጥቶ ወደ ቀኝ ኪስ የመክተትን ያህል ነው የሚሆነው። የልማት ዕርዳታ ዘላቂነት ያለው አቀነባበርን እንደሚጠይቅ፤ በዓለምአቀፍ የልማት ሽርክና ላይ ያተኮረ መዋዕለ-ነዋይ አስፈላጊ መሆኑንም ባለሚያዎቹ አያይዘው አስገንዝበዋል።

MM/DW/AFP/dpa