1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስና አይ.ኤም.ኤፍ.

ሐሙስ፣ ጥቅምት 6 2001

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ኤኮኖሚያቸውን ሊያናጋ ያሰጋውን ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ለማለዘብ የሚያደርጉት የተባበረ ጥረት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/FaEL
ፕሬዚደንት ቡሽ በዋይትሐውስ
ፕሬዚደንት ቡሽ በዋይትሐውስምስል AP

ከዩ.ኤስ.አሜሪካ እስከ አውሮፓ፤ ከአውሮፓ እስከ እሢያ-ጃፓን የባንኮችን ክስረት ለመግታትና የተሰናከለውን የገንዘብ ፍሰት ወይም የብድር እንቅስቃሴ መልሶ ለማስፈን ባለፉት ጥቂት ሣምንታት መዓት ሚሊያርድ ዶላር ነው የፈሰሰው። ይሄው በፊናንሱ ገበያ ላይ ዓመኔታን ለማስፈንና በባንኮች መካከል ያለውን የብድር ፍሰት ሕያው ለማድረግ ከያቅጣጫው የተወሰደው ዕርምጃም ካለፈው ሰኞ ወዲህ ተሥፋ ሰጭ አዝማሚያን እያመለከተ ነው። በፊናንሱ ገበዮች ላይ እንደገና የማገገም ሂደት መታየት ይዟል። ይሁንና ቀውሱ በኤኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በደፈናው ገሸሽ ብሏል ለማለት አይቻልም። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም በቅርቡ ያመለከተው የፊናንሱ ቀውስ ምታት በበለጸጉትም ሆነ በታዳጊዎቹ አገሮች የረጅም ጊዜ ጫና እንደሚኖረው ነው።

ከአሜሪካ ተነስቶ ዓለምን ባዳረሰው የፊናንስ ቀውስ የተነሣ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት አገሮች ከባድ ፈተና ላይ ቢወድቁም የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ጨርሶ ሂደቱን አላቆመም። ዕድገቱ ቻይናን፣ ሕንድንና ሩሢያን በመሳሰሉት በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ በሚገኙት አገሮችና በተወሰኑ የአፍሪቃ አገሮች ቀጥሏል። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም “የዓለም ኤኮኖሚ ዕይታ” በ 2009 በሚል ለሚቀጥለው ዓመት ባቀረበው ግምት ዕድገቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ በሶሥት ከመቶ ገደማ እንደሚወሰን ነው የተነበየው። እርግጥ በዘገባው እንደተጠቀሰው ባለፉት ሣምንታት የተፈራው የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ የተወሰኑ ቅድመ-ግዴታዎች ከተሟሉ ይደርሳል ተብሎ አይፈራም።

ቻይናን በመሳሰሉት አገሮች በወቅቱ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ የኤኮኖሚው ዕድገት እስካሁን ከተለመደው ጋብ ማለቱ ባይቀርም የዓለም ኤኮኖሚ ጨርሶ ተንኮታኩቶ እንዳይወድቅ ደጋፊነት አለው። በ IMF ግምት መሠረት ያለፈው ዓመት የቻይና የ 11,9 ከመቶ ዕድገት ወደ 9,3 በመቶ ወረድ ይላል። በሕንድ ከ 9,3 ወደ 6,9 በመቶ፤ በሩሢያ ደግሞ ከ 8,1 ወደ 5,5 ከመቶ! ይሁንና ዕድገቱ ጥቂት ቢዳከምም በታላላቆቹ ባለ ኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥ ከሚኖረው የላቀ ነው። ሌላው ቀርቶ አፍሪቃ እንኳ ከዓለምአቀፉ የፊናንሰ ቀውስ ያለ ብዙ ጉዳት ልታመልጥ እንደምትችል ነው ተቁዋሙ የሚገምተው።

የምንዛሪው ተቁዋም ጠበብት በቀደምቶቹ የበለጸጉ አገሮች በአንጻሩ ዕድገቱ እንደሚገታ ወይም የለየለት የኤኮኖሚ ቀውስ ሊከተል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። በሚቀጥለው ዓመት በነዚህ አገሮች እዚህ ግባ የሚባል የረባ ዕድገት አይጠበቅም። ተቁዋሙ በአጠቃላይ በብሪታኒያ፣ በፈረንሣይና በኢጣሊያ ማቆልቆል እንደሚኖር ሲተነብይ በአሜሪካም ጥቂት ዕድገት ብቻ ነው የሚጠብቀው። የ IMF ባልደረባ ዮርግ ዴክሬሢን እንደሚሉት በጀርመን እንዲያውም ዕድገትን ማሰቡ ከንቱ ነው።

“ጀርመን ውስጥ የኤኮኖሚው ዕድገት በማቆልቆል ወደ ዜሮ ነጥብ እንደሚጠጋ ወይም በዚያ ዙሪያ እንደሚሆን ነው የሚታየን። የጀርመን የዕድገት መንኮራኩር የውጭ ንግዷ ነው። እና አሁን የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ቀስተኛ ሆኖ ሲያዘግም የውጭ ንግድ ሞተሯ በሚገባ ለመንቀሰስ በቂ ነዳጅ የሚጎለው ይሆናል። ይህ ነው ዕድገቱ ተወስኖ ይቀራል ለማለት ያነሳሳን”

እንግዲህ የጀርመን የውጭ ንግድ መንገዳገድ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትም በድን እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። የሕዝቡ የግል ፍጆት ደግሞ ለዓመታት ተገትቶ መቆየቱ ሲታሰብ በዕውነትም የኤኮኖሚ ዕድገት መጠበቁ የሚያዳግት ነው። ለጀርመን የውጭ ንግድ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ምናልባት መድህን ወይም የተሥፋ ምንጭ ሊሆን የሚችለው በሶሥተኛው ዓለምና በሩሢያ ያለው ፍላጎት ይሆናል። በተፈጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙትን አገሮች ፍላጎት ለማሟላት የጀርመን ኤኮኖሚ በእርግጥም ተስማሚው ብቃት አለው።
በታዳጊው የዓለም ክፍል የአዳዲሶቹን ሃብታሞች ፍላጎት ለማሟላት የሚበጀው መዋቅር፣ የተሟላ የኢንዱስትሪ መሣሪያ፣ መድሃኒቶች፣ የቅንጦት አውቶሞቢሎችና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የምግብ ምርቶች ወዘተ. በሌላ አነጋገር የጀርመን የውጭ ንግድ በአውሮፓ ሕብረትና ሌሎች የበለጸጉ አገሮች በሰፊው ቢያቆለቁልም በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሰፊ የገንዘብ ክምችት ያላቸው አገሮች ከለየለት የኤኮኖሚ ክስረት ሊያተርፉት ይችላሉ። ለማንኛውም በወቅቱ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ የበለጸጉት መንግሥታት የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ አደገኛ ነው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም የፊናንሱ ቀውስ በዘርፉ ዓመኔታ እንዲጠፋ ከማድረጉ ባሻገር መዘዙ ወደተቀረው የኤኮኖሚ ዘርፍ እንዳይሻገር የሚያሰጋ መሆኑን ነው ያመለከተው።
ታላላቆቹ የኢንዱስትሪ መንግሥታት በአንድ ላይ ቀውስ ውስጥ ወድቀዋል። ከዚህ መላቀቅ የሚችሉትም በሕብረት ብቻ ነው። በመሆኑም በዓለምአቀፍ ደረጃ የተጣጣመ ዕርምጃ የግድ ይፈልጋል። ለዚህም ነበር የምንዛሪው ተቁዋም ቡድን-ሰባት መንግሥታት ባለፈው አርብ ዋሺንግተን ላይ ተሰብስበው በጋራ ቀውሱን ለመታገል ያወጡትን የተግባር ዕቅድ የደገፈው። አስተዳዳሪው ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን በማግሥቱ እንደገለጹት ይህ ዕርምጃ ተቁዋማቸው ሲጠይቀው የቆየ ነገር ነበር።

“የምንዛሪው ተቁዋም ለወራት እንኳ ባይሆን ለሣምንታት በዓለምአቀፍ ደረጃ የተቀናበረ ዕርምጃ ሲጠይቅ ነው የቆየው። በዓለምአቀፍ ደረጃ መግባባት ሣይኖር በተናጠል የሚወሰዱ ብሄራዊ ዕርምጃዎች እንደማይረዱና እንዲያውም ጎጂ እንደሆኑ አስገንዝቧል። ስለዚህም አሁን የመጀመሪያው ቅንብር ዕውን ሊሆን መብቃቱ እጅግ ጠቃሚ ነው”

185 የሚሆኑት የምንዛሪው ተቁዋም ዓባል ሃገራት ባለፈው ቅዳሜ ስብሰባቸው አንድም ታላቅ ባንክ ወይም ጠቃሚ የፊናንስ ኢንስቲቲቱት ከእንግዲህ ኪሣራ ላይ እንዳይወድቅ ለመግታት በአንድ ድምጽ ተስማምተዋል። የደገፉት የቡድን-ሰባት የተግባር ዕቅድ የብድር ዋስትናን የሚሰጥ ነው። የቆጣቢዎችና የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ንብረት ፍቱን በሆነ መንገድ እንዲጠበቁ ያደርጋል። በአጠቃላይ መንግሥታቱ የፊናንሱን ስርዓት ሕልውና ለማረጋገጥ ዋስትና ገብተዋል ማለት ነው።

የበለጸጉት መንግሥታት ባለፉት ሣምንታት በገፍ ያፈሰሱት ገንዘብና ዓመኔታን መልሶ ለማስፈን የወሰዱት ዕርምጃ የፊናንስ ገበያው በዚህ ሣምንት መልሶ ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ ጀምሯል። በዕድገት አዝሚያው ጸንቶ ለመቀጠሉ ግን አንዳች ዋስትና የለም። የተፈራው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ ላለመድረሱም እንዲሁ! በሌላ በኩል የምዕራቡ ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት መጎተት ውሎ አድሮ በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ስጋት መኖሩም አልቀረም።
አንዳንድ የኤኮኖሚ ጠበብት ሁኔታውን አሳሳቢ አድርገው ይመለከቱታል። የፊናንሱ ቀውስ በታዳጊ አገሮች ላይ ግልጽ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል ከሚሉት ከነዚሁ ጥበብት መካከል አንዱ በአሕጽሮት ዊድ፤ ማለት የዓለም የኤኮኖሚ፣ የተፈጥሮና የልማት መረብ የተሰኘ በርሊን ላይ ተቀማጭ የሆነ የሰሜን-ደቡብ የምጣኔ-ሐብት አዋቂዎችን ያስተሳሰረ ድርጅት ባልደረባ ፔተር ቫል ናቸው።

“የፊናንሱ ቀውስና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከዚሁ የተሳሰሩት የአምራቹ ኤኮኖሚ ዘርፍ ችግሮች የደቡቡ ዓለም መንግሥታት በጀቶች እጅግ እንዲጨምሩ የሚያደርጉ ናቸው። የመንግሥታቱ ዕዳ ከመጠን በላይ በማደግ ገና ከአሁኑ ከባድ ሆኖ ከሚገኘው የሚሌኔየም ዕቅድ ግቦች ለመድረስ የተያዘውን የልማት ትብብር ማራመዱን ይብስ አዳጋች ያደርገዋል”

የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታቸውን ከፍ ለማድረግ የገቡት ቃል አሁን በፊናንሱ ቀውስና ይሄው ባሳደረው የበጀት ጥበት የተነሣ የሚቻል ነገር መሆኑ ሲበዛ የሚያጠያይቅ ነው። ይህ ደግሞ ለታዳጊው ዓለም ድህነት መጨመር እንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የልማት ችግሮችንም እንዲሁ የሚያከብድ ነው። እርግጥ እንደ ዊድ የፊናንስ ባለሙያ እንደ ፔተር ቫል ቀውሱ ሁሉንም ታዳጊ አገሮች እኩል የሚጎዳ አይመስልም።

“በአንድ በኩል ተጽዕኖው በተለይ የሚሰማቸው ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ይሆናሉ። እንበል በአሜሪካ የነጻ ገበያ ክልል ውስጥ ያሉት፤ ሜክሢኮን የመሳሰሉ የማዕከላዊ አሜሪካ አካባቢ አገሮች! እነዚህ አገሮች አሁን ወደ አሜሪካ የሚያደርጉት የውጭ ንግድ በመነካቱ ተጽዕኖው በተለይ የሚሰማቸው ነው። በሌላ በኩል ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ አገሮችም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚጠብቃቸው። ማለት በዚህ በእውሮፓ ቀውሱ ሥር ሲሰድ የ ACP- የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ ስብስብ አገሮችም በከባዱ የሚጎዱ ይሆናሉ”

ሌሎቹ ተጎጂዎች በጥሬ ዕቃና በምግብ ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆኑ ድሆች አገሮች ናቸው። እነዚህ አገሮች በምግብና በነዳጅ ዋጋ መናር የተነሣ ከአሁኑ ከባድ ከሆነ የኤኮኖሚ ችግር ላይ ወድቀዋል። እንግዲህ የፊናንሱ ቀውስ ለነዚህ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያህል መሆኑ ነው። የተፈራው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ ከደረሰ ደግሞ የውጭ ንግድ ዕድላቸው ይብስ የመነመነ ይሆናል። ስለዚህም ከበለጸጉት መንግሥታት በኩል የተገባው የልማት ዕርዳታ ቃል ዕውን መሆኑ ግድ ነው። ለዚህ ከሚከራከሩት ፖለቲከኞች መካከል የጀርመኗ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይልም ይገኙበታል። ባለሥልጣኗ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በታዳጊዎቹ ላይ ፊታቸውን እንዳያዞሩ ነበር በሰሞኑ የዓለም ባንክ ስብሰባ ላይ የጠየቁት። የስጋታቸውን ያህል ተሥፋ መጣላቸውም አልቀረም።

“ይህ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ማስታወስ ያለብን ታዳጊዎቹ አገሮች በሶሥት ቀውሶች ተጠምደው እንደሚገኙ ነው። በምግብና በነዳጅ ዋጋ መናር፤ አሁን ደግሞ በባንኮች ቀውስ! የአካባቢ አየር ለውጥ ተጽዕኖም ሊዘነጋ አይገባውም። እና ከታዳጊዎቹ አገሮች ጎን የማንቆም ከሆነ ዓለምን በድሃና በሃብታም የመከፋፈሉ ሁኔታ ተባብሶ አዲስ የዓለም ስርዓተ-ቢስነት እንዳናይ ነው የምፈራው። ውጤቱ ለዓመጽና ለውዝግብ መንገድ ከፋች ነው የሚሆነው”

ከዚህ የበለጠ የከፋ ሁኔታ ሊታሰብ አይችልም። በቪቾሬክ-ሶይል ዕምነት ለበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታውን ማቅረቡ የሚከተለውን የከፋ ውጤት ከማከሙ የረከሰ ነው የሚሆነው። ለማንኛውም የፊናንሱ ቀውስ ዓለምን ወደ ኤኮኖሚ አዘቅት እንዳይከት አቅምን የማስተባበሩ ግንዛቤ ተጠናክሯል፤ ውጣ-ውረዱም ቀጥሏል። ግን የተያዘው ጥረት በቂ ይሆን? ከወዲሁ ከመተንበዩ ከርሞ መታዘቡ ይመረጣል።