1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስና አፍሪቃ

ረቡዕ፣ መስከረም 28 2001

በአሜሪካ ባንኮች ክስረት የተፈጠረው የፊናንስ ቀውስ አውሮፓን ቀስ በቀስ እያዳረሰና በእሢያ ክፍለ-ዓለምም የኤኮኖሚ ዕድገት ዝግመት ስጋትን እያጠናከረ በመሄድ ላይ ነው። በአፍሪቃስ ተጽዕኖው እስከምን ይሆን?

https://p.dw.com/p/FWHW
ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ድርጅት IMF
ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ድርጅት IMFምስል DW

ቀውሱ በመሠረቱ ድንገት የወረደ ዱብ-ዕዳ አይደለም። ቀስ በቀስ ሥር እየየደደ የመጣና የተወሳሰበ እንደመሆኑም መጠን የተባበረ ጥረትን የሚጠይቅ ነው የሚመስለው። ለነገሩ የአሜሪካ ብሄራዊ ሸንጎ የባንኮቹን የብድር አቅርቦት ብቃት መልሶ ለማስፈን የ 700 ሚሊያርድ ዶላር ዕቅድ ቢያጸድቅም የፊናንሱ ገበያ አሁንም የማቆልቆል እንጂ የማገገም አዝማሚያ አይታየትም። በዚህ በአውሮፓም የፊናንሱን ገበያ የገንዘብ ፍሰት ለማረጋገጥ መዓት ገንዘብ ይውታ እንጂ በገንዘብ አስቀማጮች ዘንድ የባንኮችን ታማኝነት መልሶ ማረጋገጡ ቀላል ነገር አልሆነም።
በፊናንሱ ገበዮች ዝቤት ሳቢያ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የተደቀነው የቀውስ አደጋ ማንዣበቡን እንደቀጠለ ነው። የወቅቱ ሁኔታ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፤ ከአውሮፓ እስከ እሢያ የአኮኖሚ ቀውስ እንዳይከተል ወይም ቢቀር ዕድገቱ ተጎታች እንዳይሆን ፍርሃቻን መፍጠሩ አልቀረም። በዚህ በጀርመን የአገሪቱ ቻንስለር ወሮ አንጌላ ሜርክል በባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ዜጎች ንብረታቸውን እንደማያጡ በአንድ ሣምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ በማረጋገጥ ለማረጋጋት ሞክራዋል። አዋቂዎች የሚናገሩት በአገሪቱ ላይ ከባድ የብድር እንቅስቃሴ መሰናከል እያሰጋ እንደሆነ ነው።

በብሪታኒያ ደግሞ የፊናንሱ ገበያ አለመረጋጋት ያሳሰበው መንግሥት ባንኮችን በከፊል በይዞታው ሥር ለማዋል ማቅማማት ይዟል። በጃፓን ማዕከላዊው ባንክ የገንዘብ ገበያውን ነውጽ ለማረጋጋት እስከ ዛሬ ድረስ 10.8 ሚሊያርድ ኤውሮ አፍሷል። በዓለምአቀፉ የባንኮች ቀውስ እስካሁን 1.400 ሚሊያርድ ዶላር መውደሙ ነው የሚነገረው። በዓለምአቀፍ ደረጃ በፊናንሱ ገበዮች ላይ የነበረው ዓመኔታ ክፉኛ ሲያቆለቁል ሁኔታው ስጋት ያሳደረው በገንዘብ አስቀማጮች ዘንድ ብቻ አይደለም። ባንኮችም ብድር በሚሰጡበት ወይም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አይገኙም።

እንግዲህ ድርቅ የተጣባውን የፊናንስ ገበያ መልሶ ሕይወት ለመስጠት በዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቁዋም በ IMF ስሌት መሠረት በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት የ 675 ሚሊያርድ ዶላር ካፒታልን የሚጠይቅ ይሆናል። የፊናንስ ቀውሱ በወቅቱ ባንኮችን ብቻ ሣይሆን የተቀሩትን የኤኮኖሚ ዘርፎችና ባለንብረቶችን ጭምር ማለቂያው ከማይታወቅ መዘዝ ላይ እየጣለ የሚሄድ ጉዳይ ነው። እንደ IMF ከሆነ ፈተናውን ለመወጣት በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉትና በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኙት ተራማጅ መንግሥታት ትብብር ላይ የተመሠረተ የተጣጣመ ዕርምጃ ግድ ነው የሚሆነው።
በዛሬው የተሳሰረ ዓለም በተናጠል በሚወሰዱ ዕርምጃዎች መፍትሄ ሊገኝ አይችልም። እርግጥ ጥያቄው ይህን መሰሉ ትብብር ገሃድ ይሆናል ወይ ነው። የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆርጅ-ደብይሉ-ቡሽ የችግሩን ክብደት በማስገንዘብ ለአውሮፓ መንግሥታት የትብብር ጥሪ አድርገዋል። በሌላ በኩል ይሁንና ባለፈው ሣምንት ፓሪስ ላይ የተሰበሰቡት የአራቱ ቀደምት የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት የጀርመን፣ የፈረንሣይ፣ የብሪታኒያና የኢጣሊያ መሪዎች በጋራ ለመሥራት ከመስማማት ባሻገር ከብሄራዊ ደረጃ ያለፈ አንድ-ወጥ የማዳን ተግባር ለማስፈን አልፈለጉም።

ከዚህ አንጻር ሁኔታው ለወራትና ምናልባትም ለዓመታት ፈታኝ ሆኖ የሚቆይ ነው የሚመስለው። የፊናንሱ ገበዮች ቀውስና የበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በታዳጊ አገሮች፤ በተለይም በአፍሪቃ ልማት ላይም ተጽዕኖ የሚኖረው ጉዳይ ነው። ተጽዕኖው እስከ ምንና እንዴት? በወቅቱ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙትን የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ መምሕር ዶር/በፈቃዱ ደገፌ በጉዳዩ የሚሉት አላቸው።