1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም በ2016 ከጥር እስከ ሰኔ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2009

የአፍቃኒስታን የአስራ-ስድት ዓመት፤ የኢራቅ የ13 ዓመት፤የሊቢያና የሶሪያ የአምስት ዓመት፤የየመን፤ የዩክሬን-ሩሲያ፤የሩሲያ-ምዕራባዉያን የሁለት ዓመት የጦርነት፤የእልቂት፤ዉዝግብ ታሪክ  እንደደመቀ-ዘንድሮ አምና ሊሆን የአስር ቀን ዕድሜ ቀረዉ

https://p.dw.com/p/2UYdB
Kombobild Khamenei, Putin, Assad
ምስል picture-alliance/dpa/Y. Badawi/dpa

ዓለም በ2016 ከጥር እስከ ሰኔ

ለፍልስጤም-ዓረብ እስራኤሎች 1948ን «ድሮ» ፤ 2016ን «ዘንድሮ» አልነዉ አላልነዉ  ከጠብ፤ ግጭት ጦርነት ሌላ ሌላ ብዙ ታሪክ የለም።ኮሪያ ልሳነ ምድርም 1950 ሆነ፤ 2016 ያዉ ነዉ።የአፍቃኒስታን የአስራ-ስድት ዓመት፤ የኢራቅ የ13 ዓመት፤የሊቢያና የሶሪያ የአምስት ዓመት፤የየመን፤ የዩክሬን-ሩሲያ፤የሩሲያ-ምዕራባዉያን የሁለት ዓመት የጦርነት፤የእልቂት፤ዉዝግብ ታሪክ  እንደደመቀ-ዘንድሮ አምና ሊሆን የአስር ቀን ዕድሜ ቀረዉ።የሠላም ተስፋ በጦርነት ዑደት፤ የመግባባት ምኞት በጠብ ንረት፤ የዕድገት ሕልም በስደት ማዕበል በተጨናጎለበት በ2016 ከአፍሪቃና ከአዉሮጳ በመለስ የተከናወኑ አበይት ጉዳዮችን በሁለት ክፍል እንቃኛለን። የመጀመሪያዉን እነሆ።
                        
የዘመን ሒደት፤ ሰዉ የመሆን ተፈጥሮ ግድ ብሎ መካከለኛዉ ምሥራቅ ከሚያዉቃቸዉ ብዙ ትላልቅ ሰዎች አንዱን ዘንድሮ አሰናበተ።ሺሞን ፔሬስን።መስከረም።ለዉጊያ፤ ግጭት ዉዝግቡ ግን ያ ምድር ድሮም-ዘንድሮ-ዘንድሮም ድሮ ነዉ።

የኮሪያ ልሳነ ምድር ሕዝብ  ከ1950 ጀምሮ እንደነበሩበት 57 ዘመናት ሁሉ 2007ን በጦርነት፤ ግጭት፤ ፍጥጫ እንደተሸማቀቀ ትልቅ ዲፕሎማቱን ፓን ጊሙንን ለትልቁ ድርጅት ዋና ፀሐፊነት አሹሞ፤ በጦርነት፤ ግጭት ፍጥጫዉ ዑደት ኖሮ ፓንን ከትልቁ ሹመት አሰናበተ። 2016ንም ሊሸኝ ነዉ።
 አሜሪካኖች ባራክ ኦባማን ሲመርጡ ከደቡብ እስያ እስከ መካከለኛዉ ምስራቅ፤ ከምሥራቅ አፍሪቃ ፤ እስከ ደቡብ እስያ ከጦርነት ከሞጀሯቸዉ፤ ታማኞቻቸዉን ከየጦርነቱ እየዘፈቁ፤ ዓለምን ሽብር-ፀረ ሽብር ካዘመሩት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ይሻላሉ የሚል ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።

USA Außenminister John Kerry USA und Javad Zarif Iran
ምስል picture alliance/dpa/AP Photo/F. Franklin

ኦባማ አምና ሐገራቸዉን ከኢራንና ከኩባ ጋር ማስታረቃቸዉ ለሰላም በርግጥ ጥሩ ጅምር ነዉ።ኦባማ ከ2016 ጋር ከስልጣናቸዉ የሚሰናበቱት ግን በወረሱት ጦርነት ላይ የሊቢያን፤ የየመንን፤ የሶሪያን፤የዩክሬንን እልቂት፤ ትርምስ፤ሽብር ጥፋት-ዉዝግብን አጋግመዉ፦ ሐገር ተከታዮችዋን ከሩሲያዎች ጋር አቃቅረዉ የመሆኑ ሐቅ እንጂ የጥሩዉ ጅምር ቅጭት።
ዓለም ስለ ሰላም ሲጮሕ፤ ስለ እኩልነት ሲማፀን የዓለም መሪዋ ሐገር ሕዝብ፤ ጠብ ናፋቂ፤ ዘረኝነትን ሰባኪ፤ ሕዝብን ከፋፋይ ቱጃር ፖለቲከኛን መምረጡ ሂያጁ ዘንድሮ  ለመጪዉ ዘመን የሚያወርሰዉ ተቸማሪ እዳ ነዉ።

አምና ዩቱይብ ላይ የተለጠፈች የነጭ-ጥቁር ቀለም የቪዲዮ ክሊፕ የሳዑዲ አረቢያ ባሕላዊ ጨፈራን ታሳያለች።ከጨፋሪዎቹ ሁሉ አንዱ ጎላ፤ ደመቅ፤ ደገምገም ብሎ ይታያል።ከቪዲዮዉ ስር የተለጠፈዉ ፅሁፍ «የኢራኑ ንጉስ መሐመድ ሬዛ ፓሕሌቪ ሳዑዲ አረቢያን በጎበኙበት ወቅት ንጉስ ሳልማን በጭፈራ ሲቀበሏቸዉ» ይላል።
ዘመኑ አልተጠቀሰም።ሻሕ መሐመድ ሬዛ ፓሕሌቪ በ1955 እና በ1966 ሪያድን መጎብኘታቸዉ ግን እዉነት ነዉ።በ1955 ንጉስ ሳዑድ ቢን አብዱል አዚዝ፤ በ1966 ደግሞ ንጉስ  ፈይሰል ኢቢን አብዱል አዚዝ አል ሳዑድ በቴሕራን አፀፋ ጉብኝት ማድረጋቸዉም ሐቅ ነዉ። ወጣቱ ልዑል በመጀመሪያዉ ጉብኝት ወቅት የሪያድ ምክትል አገረ-ገዢ፤ በሁለተኛዉ ዋና አገረ-ገዢ ስለነበሩ የኢራኑን መሪ በክብር ካስተናገዱት የሳዑዲ አረቢያ ልዑላን አንዱ እንደሚሆኑ መገመት አያዳግትም።
ሁለቱ ሐገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲመሰርቱ ሳልማን አልተወለዱም ነበር።1929።ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ  የተደረገዉ የሁለቱ ሐገራት ነገስታት ጉብኝት አፀፋ-ጉብኝት፤ ጭፈራ ዉይይቱ በሁለቱ ሙስሊም፤ የነዳጅ ዘይት ሐብታም፤ ሰፋፊ ጎረቤት ሐገራት መካከል የነበረዉን ጥብቅ ወዳጅነትን ማረጋገጡም ሐቅ ነዉ።

Saudi-Arabien General Qamar Javed Bajwa, Chief of Army staff (COAS)
ምስል ISPR

እርግጥ ነዉ የኢራኑ ሻሕ ለእስራኤል እዉቅና መስጠታቸዉ የሪያድ ነገስታትን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም።ቅሬታዉ ግን ጥብቅ ወዳጅነቱን አልሸረሸረዉም።
ከ1950ዎቹ ጀምሮ የካይሮ፤የደማስቆና የባግዳድን አብያተ መንግሥታት የተቆጣጠሩት ወጣት የጦር መኮንኖች ዋሽንግተን-ለንደኞችን ለቴል አቪቭ በሚሰጡት ድጋፍ ምክንያት ገሸሽ-ገለል ራቅ ፤ ሞስኮዎችን ጠጋ፤ጠበቅ ማድረጋቸዉ ያሰጋቸዉ የዋሽግተን፤ ለንደን ፓሪስ ተሻራኪዎች የሪያድና ቴሕራንን መወዳጀት ለማጠናከር በቀጥታም፤ በተዘዋዋሪም ግፊት ያደርጉም ነበር።
በ1979 የመሐመድ ሬዛ ፓሕሌቭን አገዛዝ አስወግደዉ ስልጣን የያዙት የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች ልክ እንደ ሳዑዲዎች ለእስራኤል እዉቅና ነፈጉ።ሻሁ ለእስራኤል እዉቅና በመስጠታቸዉ ቅር ተሰኝተዉ የነበሩት የሪያድ ነገስታት ግን በቴሕራን አብዮተኞች ርምጃ  አልተደሰቱም።እንዲያዉም አኮረፉ።

ምክንያት፤አንድ- እስላማዊ አብዮተኞቹ ከሪያዶች በላይ የእስራኤል ጠላት፤ ከአረቦች ይበልጥ የፍልስጤም ነፃነት ተዋጊዎች ደጋፊ ሆኑ።ሁለት፤ አሜሪካን ትልቋ፤ ሌሎቹን ምዕራባዊ መንግሥታትን ትናንሾቹ «ሰይጣኖች» እያሉ አወገዙ፤ ተጋፈጡም።

ዋሽግተን፤ ለንደን ቴል አቪቮች ከመሰጠሩት ብዙ «ሴራ» አንዱ ሪያድ ላይ እንዲሕ ተተረጎመ። «እኒሕ የኢራን አብዮተኞች የሺዖ እስልምናን ለማስፋፋት፤ ሱኒዉን ለማዳከም የሚታገሉ መሰሪ ናቸዉ።እኛ ደግሞ የመካና መዲና ካዲሞች (አገልጋዮች) የሱኒ ጠባቂዎች፤ የአረብ አለኝታዎች በመሆናችን «ሴራዉን በሁሉም መስክ ማክሸፍ አለብን።» 
በሻሁ ዘመን የወዳጅነታቸዉ ዋልታ፤ የመደጋገፋቸዉ ማገር፤የመተባበራቸዉ መሠረት የነበረዉ እስልምና እሁለት ተገምሶ የጠባቸዉ ማጋጋሚያ፤ የመሻኮቺያቸዉ ማጦዢያ፤ የተዘዋዋሪ ጦርነታቸዉ መፋለሚያ ሆነ።ሱኒና ሺዓ።ዘንድሮ ለሁለተኛ ዓመት የመንን የሚያነፍረዉ ጦርነት የዚሕ ዉጤት ነዉ።ዓመቱ ሲጀመር ሳዑዲ አረቢያ እግረኛ ጦር አዘመተች ተብሎም ነበር።ያስተባበሉት ሪያዶች አይደሉም።ዋሽንግተኖች እንጂ
                    
«ቀላሉ መልስ፤ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች ሳዑዲ አረቢያም እርስ በርስም ሆነ ከሌላ ጋር እግረኛ ጦር ወደየመን ሥለማዝመት አልተናገሩም።»
ሁለቱ መንግሥታት ከግብፁ ፕሬዝደንት አንዋር አሳዳት ግድያ፤ እስከ ፍልስጤም እስራኤሎች ዉጊያ፤ ከኢራቅ-ኢራን ጦርነት፤ ከሊባኖሶች ዉጊያ፤ እስከ ኢራን-ባሕሬን ጠብ፤ ከሶሪያ እስከ የመን ጦርነት ሕዝብ እንዳፋጁ አሉ።

Syrien Busse bei Aleppo in der Idlib Provinz
ምስል picture-alliance/dpa/Sana

2016 በባተ በሁለተኛዉ ቀን ሳዑዲ አረቢያ እዉቁን የሺዓ መንፈሳዊ መሪ ኒምር አል ኒምርን ከሌሎች 46 ሰዎች ጋር በሞት ቀጣች።ሺዓ ወገኑ በመገደላቸዉ  የተቆጣዉ ኢራናዊ  በኢራን የሳዑዲ አረቢያን ኤምባሲና ቆስላ ፅሕፈት ቤቶችን ሰባበረ።ሪያዶች በተራቸዉ ተቆጡ።የፖለቲካ አዋቂ ጀማል ኻሽጂም ይሕን መሰረከሩ።
በ1955 ወይም 66 የሺዓዉን ንጉስ በፍቅር፤ በጭፍራ፤ ፈንጠዝያ የተቀበሉት የዛሬዉ ሽማግሌ የንጉስ ሰልማን  ቢን አብዱል አዚዝ አል ሳዑድ ቁጣ ልክ አልነበረዉም።
«ንሳ» አሉ አገልጋዮቻቸዉን «በአባት፤ አያት፤ ቅድመ አያቶቼ የተከበረች ሐገር በማንም ሺዓ አትደፈረም።ዲፕሎማቶቻችንን ከኢራን አስወጡ።ኤምባሲዉን ዝጉ።አያት ቅድመ አያቶቻቸዉ ከኢራን ጋር በ1929 የመሰረቱትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በጠሱት።ጥር 3 2016።
ጠቡም መረረ።የፖለቲካ ተንታኝ ፋዑዝ ዤዤ ከሰበቡ ጀርባ ያለዉን ምክንያት እንዲሕ ይገልፁታል።
                         
ጃኪዩም ጉዝማን ለተራዉ ሜክሲኩዊ እንደ ሰይጣን-ጭካኝ፤ ምሕረት የለሽ።እንደ ጀግና ደፋር፤ እንደ ብልሕ አሳሳች፤ ደግሞ ነጋዴ ቱጃር ናቸዉ።ዓለም የተስማማበት ግን ሰዉዬዉ ወደር የለሽ አደንዛዥ ነጋዴ በመሆናቸዉ ነዉ።በጥብቅ ከሚጠበቁበት እስር ቤት ማምለጣቸዉ አስደንቆ፤ አነጋግሮ ሳያበቃ እንደገና ተያዙ።ጥር ስምንት።
ደቡብ አሜሪካኖች በጉዝማን ድል፤ ገድል፤ ሽንፈት-ምርኮ የአሜሪካኖችን ሚና እያነሱ ሲጥሉ፤ ኢራን ከሐያላኑ መግስታት ጋር በተፈራረመችዉ ዉል መሰረት የኑክሌር መሳሪያዎችዋን መነቃቀሏን ዓለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት (IAEA) አረጋገጠ።
                        
የድርጅቱ ሐላፊ አኩዮ አማኖ።ጥር 16።የቪየናዉ ድርጅት ማረጋገጪያ ለኢራኖች ፌስታ፤ ለአሜሪካዎች እፎይታ፤ የጠብ፤ ጦርነት የእልቂት-ስደት ለታከተዉ ዓለም የሰላም ሽዉታ ነበር።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ፌዴሪካ ሞጌሪኒ እንዳሉት ደግሞ ጥሩ ዜና በሌለበት ዓለም ጥሩ ዜና ነዉ።
                        
ሁለት መንግስታት ግን ቆሽታቸዉ ነዉ ያረረዉ።እስኤልና ሳዑዲ አረቢያ።አረሩ-ተከኑ።አሜሪካ መንግሥት ላይ አልጎመጎሙም። ኢራን ግን ማዕቀቡ ተነሳላት።ግን ምን ያደርጋል ሰላም ወዳዱ ዓለም የሰላም ሽዉታዉን ከሳምንታት በላይ ማጣጣም አልቻለም።የካቲት ሰባት። ሰሜን ኮሪያ አዲስ የሰራችዉን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል ሞከረች።
                         
 
መጋቢት፤ ለቤልጂጎች ገደ-ቢስ ወር ነበር።ምክንያቱን መዘከር የኛ ድርሻ አይደለም።አዉሮጳና ጀርመን ያስታዉሰን ይሆናል።መጋቢት ለፓኪስታኖችም  የዘግናኝ ጥፋት ወር ነበር።ለነገሩ ዩንይትድ ስቴትስ መራሹ ጦር አፍቃኒስታንን ከወረረበት ከ2001 ጀምሮ ፓኪስታን ሸብር እልቂት ዘግናኝ ጥፋት ተለይቷት ያዉቃል።ተደገመ እንበል።
መጋቢት ሃያ ሰባት።ላሆር ከተማ፤ ጉልሻን ኢቅባል ፓርክ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳዉ ቦምብ 75 እራሱን ገደለ።340 አቆሰለ።አጥፍቶ ጠፊዉን ያዘመተዉ የሱኒ ሙስሊም አሸባሪ ድርጅት ነዉ ተብሏል።መጋቢት ተሰናበት።ሕይወትም፤ ሕይወትም ደሞ እስከ ሌላ ጥፋት ቀጠለች።አርመን ጥንታዊ ግን ትንሽ፤ደሐ ሐገር ናት።የአንድ መቶ ዓመት ርቀት የቀበረዉን ዶሴ አዋራ-አራግፋ  የቀድሞ ቅኝ ገዢ ትልቅ «ጠላትዋን» ቱርክን ለመክሰስ ማስወንጀል ግን ትንሽነቷ፤ ድሕነቷም አላገዳትም።
ይሁንና ከ101 ዓመት በፊት በዜጎችዋ ላይ ተፈፀመ ላለችዉ ግፍ ቱርክ እንድትወነጀል ከዋሽግተን-ለንደን፤ ከፓሪስ-ኦታዋ፤ከበርሊን ካምቤራ ስትባትል ባሁን ዜጎችዋን ላይ የተጋረጠዉን የጦርነት ስጋት ምናልባት ለመጪዉ መቶ ዓመት ቀብራ፤ ከአጎራባችዋ አዝርበጃን ጋር የገጠመችዉን ጠብ ዘንግታ ወይም ደብቃ ነበር።
አርመንን ከመርዳት፤ከጠበኞችዋ ከማስታረቅ ይልቅ ቱርክን ለማሳጣት የሚባትለዉ ምዕራቡ ዓለም የቱርክ ጦር በ19አስራዎቹ አርመን ላይ የወሰደዉን እርምጃ  ዘር ማጥፋት እያለ ሲወነጅል አርመንና አዘርበጃን አዲስ ጦርነት ገጠሙ።ሚያዚያ ሁለት።ናጎርኖ ካራባሕ በሚባለዉ ግዛት ሰበብ የሚወዛገቡት ሁለቱ ሐገራት ከ1994 ወዲሕ ጦርነትም የለም፤ ሰላምም የለም መርሐቸዉን አፍርሰዉ በገጠሙት ዉጊያ 193 ሰዉ ተገደለ።
ሚያዚያ 3 ዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ማሕበርና ሱድ ዶቸ ሳይቱግ የተሰኘዉ የጀርመን ጋዜጣ አንድ ጉድ አጋለጡ።ከኢትዮጵያ እስከ ብሪታንያ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ቻይና የቀረ የለም---የመንግሥታት መሪዎች፤ ፖለቲከኞች፤ የኩባንያ ሐላፊዎች ከየሐገራቸዉ የሚዘርፉትን ገንዘብ የሚያሸሹበትን ሰነድ አጋለጡ።የፓናማ ወረቀት የተባለዉ ሰነድ 11,5 ሚሊዮን ነዉ።214 ሺሕ ኩባንዮች አሉበት።ዓለም ጉድ አለ።የትንሺቱ ሐገር የአይስላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ሥልጣን ከመልቀቃቸዉ ባለፍ ጉድ ባሰኘዉ ቅሌት እስካሁን የተከሰሰ፤የተቀጣም የለም።
ሜድትራኒያን ባሕር።ሌላ ወር።ሌላ መርዶ።ግንቦት 19ኝ። 56 መንገደኞችን፤ ሰባት ሰራተኞችንና ሰወስት ወታደሮችን አሳፍሮ ከፓሪስ ወደ ካይሮ ይበር የነበረ የግብፅ የመንገደኞች አዉሮፕላን ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ ወድቆ ሰመጠ።ያሳፈራቸዉ ሰዎች በሙሉ አለቁ።የአደጋዉ ትክክለኛ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።ሽብር-ፀረ ሽብር ማለት የለመደዉ የዓለም መገናኛ ዘዴ አዉሮፕላኑ በአሸባሪዎች ቦምብ ሳይመታ አይቀርም የሚል መላምቱን እያነሳ ከመጣል አልታቀበም።
አደጋዉ ለአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ፖለቲከኞች የምረጡኝ  ዘመቻ መቀስቀሻ ሆኖም ነበር።ቀኝ ፅንፈኛዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራም ቀዳሚዉ ነበሩ።
                                
«አዉሮፕላኑ ድንገት መሐል ሰማይ ላይ ጋየ።ዝም ብሎ ሰማይ ላይ ጋየ ብሎ የሚያስብ ሰዉ ካለ እሱ መቶ በመቶ ስሕተተኛ ነዉ።ከዚሕም የባሰ አለ።ዛሬ አንድ ማሰራጪያ ጣቢያ እያየሁ ነበር።አንድ ጎበዝ የኤፍ ቢ አይ ባለሙያ ቀርቦ ነበር።በአዉሮፕላኑ ላይ ሥለደረሰዉ ይናገር ነበር።የሚገርም ነዉ እኔ አላዉቀዉም፤ በቴሌቪዥን አይቼዉም አላዉቅም።»
የሜድትራኒያን ባሕር አሳ እያመረተ-ሰዉ መብላት አዲሱ አይደለም።ዘንድሮ ብቻ ወደ አስምት ሺሕ ስደተኞች አልቀዋል።ዓለም ዘመናይ ታሪኳን መፃፍ ከጀመረች ብዙ ሕዝብ በማሰደድ ማፈናቀል ከ110 ቀን በኋላ አምና የምንለዉ ዘንድሮ አንደኛ ነዉ።65,3 ሚሊዮን ሕዝብ ስደተኛ ነዉ።

Egypt Air Trauer Mensch mit Kerzen Kairo Ägypten
ምስል picture-alliance/dpa/M. El Raai
Videostill Ägypten Shiff sucht Egyptair-Flugzeug
ምስል picture-alliance/AP Photo/Egyptian Armed Forces
Jemen Aden Selbstmordanschlag auf Soldaten
ምስል Getty Images/AFP/S. Al-Obeidi

ሟች ቁስለኛ፤ ስደተኛ ሲሰላ ዓመቱ ተጋመሰ።ስደተኛ ወር።ሰኔ።አፍሪቃ የቀድሞዉ የቻድ ፕሬዝደንት ከስ፤ወንጀል፤ፍርድ፤ ስትል፤ አዉሮጳ ደግሞ፤ ብሪታንያ ወሰነች።ከአዉሮጳ ሕብረት ወጣች ትል ነበር።በመሐሉ በሌላ ቦምብ ፍንዳታ ተሸበረች።ኢስታንቡል-አታ ቱርክ አዉሮፕላን ማረፈያ።አስከሬን ተቆጠረ።45።ቁስለኛ ተሰላ።230።ሐምሌ 28። የቀሪዉን ስድት ወር የጎላ እዉነት ሳምንት ከሌላ አዘጋጅ ጋር ይጠብቃችኋ።

 

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ