1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ትንበያ ለምን ዘለለ?

ረቡዕ፣ ጥቅምት 17 2014

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት በሚቀጥለው አመት የሚኖራቸውን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ሲተነብይ የኢትዮጵያን ሳያካትት ቀርቷል። የተቋሙ እርምጃ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደሩ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ቢስማሙም ፖለቲካዊ ገፊ ምክንያት ይኖረው ይሆን? በሚለው ጉዳይ ይለያያሉ።

https://p.dw.com/p/42GId
USA Weltbank-Zentrale in Washington
ምስል Reuters/Y. Gripas

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ትንበያ ለምን ዘለለ?

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት በሚቀጥለው አመት የሚኖራቸውን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ሲተነብይ የኢትዮጵያን ሳያካትት ቀርቷል። ባለፈው ሣምንት ይፋ የሆነው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰነድ የ45 የአፍሪካ አገራትን የምጣኔ ሐብት ይዞታ የሚያሳዩ መረጃዎች እና ሊገባደድ ሁለት ወራት በቀሩት የጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም የሚጠበቀውን እንዲሁም በመጪው ዓመት የሚኖራቸውን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ትንበያ ያካተተ ነው።

በአይ.ኤም.ኤፍ ትንበያ መሠረት በየጎርጎሮሳውያኑ 2021 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በ2.0 በመቶ ያድጋል። ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ምጣኔ ሐብት በሚቀጥለው አመት 3.8 በመቶ እንደሚያድግ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል። በ2022 ዓ.ም ኤርትራ 4.8 በመቶ፤ ደቡብ ሱዳን 6.5 በመቶ ሊያድጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የኢትዮጵያን ግን --አድርጎታል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ አበበ አዕምሮ ስላሴ "በወደፊት ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ረገድ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የእርግጠኝነት ማጣት አለ። ሁለተኛው ምክንያት [የኢትዮጵያ] መንግሥት በአዲስ መርሐ-ግብር ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ድጋፍ ጠይቋል። በድጋፉ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ገና አልተጀመሩም" ሲሉ ተቋሙ የኤኮኖሚ ትንበያውን ያላቀረበባቸውን ሁለት ምክንያቶች አስረድተዋል። ኃላፊው "ይኸ ከዚህ ቀደም ያልተደረገ አይደለም። አርጀንቲና እና ሊባኖስን በመሳሰሉ አገሮች በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች የዕድገት ትንበያ ሳናቀርብ ቀርተን እናውቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዓመት ሁለት ጊዜ በሚያዝያ እና በጥቅም ወራት እንዲህ የአገራትን የኤኮኖሚ ትንበያ ይፋ ያደርጋል። ከሳምንት በፊት ይፋ የሆነው የተቋሙ ሰነድ የአራት አመታት የምጣኔ ሐብት ትንበያን የያዘ እንደሆነ የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ "በውስጡ `በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ እርግጠኛ አይደለሁም፤ እንደ አገርም ላትኖር ትችላለች አይነት የሚል መልዕክት አለው።´ መተንበይ አልችልም ማለት፤ የአገሪቱን እጣ ፋንታ አላውቀውም" የሚል መልዕክት ጭምር እንዳስተላለፈ ገልጸዋል።

"ማንኛውም ዓለም አቀፍ ኢንቨስተር፤ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ እጣ ፈንታ ማወቅ ይፈልጋል። መረጃ የሚያገኘው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ነው። በኢትዮጵያ ትልቅ መዋዕለ-ንዋይ የሚሰማራ ኢንቨስተር የአገሪቱን የሚቀጥሉት አመታት የኤኮኖሚ ሁኔታ ምን ይሆናል የሚለውን ከእነ አይ.ኤም.ኤፍ. ከሚያገኘው መረጃ ተመርኩዞ የመነሻ ሐሳብ ወስዶ ከዚያ ዝርዝር ጥናቶችን ያካሒዳል ማለት ነው" የሚሉት አቶ አብዱልመናን "ይኸ መረጃ በሌለበት ማንኛውም ኢንቨስተር በኢትዮጵያ  ኢንቨስት የማድረግ ፤ አበዳሪም የማበደር ፍላጎት አይኖረውም" በማለት የሚያስከትለውን ጉዳት ገልጸውታል።

የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት የተመለከቱ መረጃዎች ሲፈልጉ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰነዶች ከሚያገላብጡ ባለሙያዎች መካከል በጀርመኑ ሔለባ ባንክ የኤኮኖሚ ትንተና ባለሙያው ፓትሪክ ሐይኒሽ አንዱ ናቸው። በግጭት ውስጥ ለሚገኙ እንደ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ያሉ አገሮች ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አጠቃላይ አገራዊ ምርት፣ የዋጋ ግሽበት እና የወለድ ምጣኔን የመሳሰሉ ኤኮኖሚያዊ መረጃዎች እንደሚያቀርብ የሚናገሩት ፓትሪክ ሐይኒሽ ተቋሙ ኢትዮጵያን ሲዘል "ያልተለመደ ውሳኔ" ሆኖባቸዋል።

ፓትሪክ ሐይኒሽ "አንድ የጀርመን ነጋዴ ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ መላክ ከፈለገ በኢትዮጵያ ባንክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት ይኖርብናል። የእኔ ሥራ የአንድን አገር የሥጋት ትንተና የማቅረብ ነው። ስለዚህ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ተቋማት የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች እመለከታለሁ። ነገር ግን ኢትዮጵያን የተመለከተ መረጃ ማግኘት ካልቻልኩ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚያዊ ክንዋኔ ለመተንበይ ወይም የኢትዮጵያን ዕዳ የመክፈል አቅም ለመገመት አልችልም።  ከመንግሥት ጋር ሳይሆን በኢትዮጵያ ከሚገኝ ኩባንያ ጋር የምትሰራ ቢሆን እንኳ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት መቻሉን መገምገም ይኖርብሃል። ምክንያቱም በአሜሪካ ዶላር እንጂ በብር እንዲከፈለን አንፈልግም። የአንድ አገር የሥጋት ትንተና አስፈላጊ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው። እነዚህን መረጃዎች ማግኘት ካልቻልክ እጅግ ፈታኝ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ባለሙያው እንደሚሉት አይ.ኤም.ኤፍ. የኢትዮጵያን የምጣኔ ሐብት ትንበያ ይፋ አለማድረግ  "ለባለወረቶች እና የውጭ ባንኮች ትልቅ ችግር ይሆናል።"

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የብድር ማዕቀፍ "እንዲቀጥል" ኢትዮጵያ ጠየቀች

 

ልክ የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ሙሉ አንድ አመት የሚደፍነው እና በትግራይ ተቀስቅሶ እስከ አፋር እና አማራ ክልሎች የዘለቀው ውጊያ ከፈጠረው ብርቱ ሰብዓዊ ቀውስ፣ ካወደመው መሠረተ-ልማት እና የአገሪቱ ጥሪት ባሻገር የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት ቅርቃር ውስጥ ከቶቷል።

የኤኮኖሚ ትንተና ባለሙያው ፓትሪክ ሐይኒሽ በኢትዮጵያ ግጭት እና ተግዳሮቶች ቢኖሩም እያደገ በሚሔደው የአገሪቱ ገበያ እና በረዥም ጊዜ ባለው አቅም ምክንያት የተወሰኑ ግዙፍ ኩባንያዎች እና ባለወረቶች አሁንም ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ። ለዚህም በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለሚገባ የቴሌኮም ኩባንያ ፈቃድ ለመስጠት የተካሔደው ጨረታ የተሳታፊዎቹ ቁጥር ሁለት ብቻ ቢሆንም የሚጠቀስ ነው።

የኢትዮጵያ ግዙፍ ገበያ እና እያደገ የሚሔድ የሕዝብ ቁጥር የውጭ ባለወረቶች ቀልብ ቢስብም የዛኑ ያክል አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታ በተለይም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለራሳቸው መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሞክሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ ፓትሪክ ሐይኒሽ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ "ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ በየአመቱ እየቀነሰ ነው። ነገር ግን ካለፈው ከ2020 ሶስተኛ ሩብ ዓመት ጀምሮ ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ቀስ በቀስ እየጨመረ ነው። ወቅቱ የትግራይ ጦርነት የተጀመረበት፤ የኮቪድ ወረርሽኝ የበረታበት በመሆኑ ይኸ አስገራሚ ነው" የሚሉት ፓትሪክ ሐይኒሽ  "የኢትዮጵያን ጥሪቶች በዝቅተኛ ዋጋ ለመግዛት የሚሞክሩ ባለወረቶች እንዳሉ አስባለሁ። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በማዛወሩ ሒደት ገፍተውበታል። ምክንያቱም የተሻለ ጊዜ እስኪመጣ መጠበቅ አይችሉም። ገንዘቡ አሁን ያስፈልጋቸዋል። የትግራይ ጦርነት ውድ ነው፤ ወረርሽኙ ገንዘብ ያስወጣል። ተግዳሮቶች ፤ ቀውስ እንዲሁም የተሟላ መረጃ ባይኖርም ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ቀስ በቀስ የበለጠ አይጨምርም ማለት አልችልም" ሲሉ አስረድተዋል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ኃላፊ አበበ አዕምሮ ስላሴ ተቋማቸው በመጪው አመት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ሊኖረው የሚችለውን ዕድገት በተመለከተ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ምክንያትም ኃላፊው እንዳሉት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንዲገለጽ የፈለጉትን ብቻ ነው።

Portugal Troika
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ አበበ አዕምሮ ስላሴ "በወደፊት ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ረገድ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የእርግጠኝነት ማጣት" ተቋማቸው ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሐብት ትንበያ ሳያቀርብ ከቀረባቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። ምስል picture-alliance/dpa

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ተቋሙ ደቡብ ሱዳንን የመሳሰሉ አገሮችን ትንበያ እና ምጣኔ ሐብታዊ መረጃዎች አቅርቦ የኢትዮጵያን ባለማካተቱ "ህልውናዋን እጠራጠራለሁ ነው እያለ ያለው" ሲሉ ይናገራሉ። የተቋሙን ውሳኔ "የሚያሳምን ሆኖ አላገኘሁምት" የሚሉት አብዱልመናን "[ውሳኔው] ይበልጥ ፖለቲካዊ ይመስላል። ማንም ቢመዝን የአይ.ኤም.ኤፍ አይነት ድምዳሜ ላይ ይደርሳል የሚል ግምት የለኝም። የአፍሪካ ልማት ባንክ የሰራው [የኤኮኖሚ ትንበያ] አለ። ይኼ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደሪያም ይመስላል። ምክንያቱም ኢንቨስተሮች እንዳይመጡ ማሸሽ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) የተባለው እና መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም ያበቃው የዓለም የገንዘብ ድርጅት ማዕቀፍ እንዲቀጥል ለተቋሙ ጥያቄ አቅርባለች። ከዚህ በተጨማሪ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያ ባለባት የውጭ ዕዳ የአከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ በሒደት ላይ ይገኛል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለሁለቱ ሒደቶች ምላሽ ለመስጠት ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ አንዳች ትንበያ መሥራቱ ስለማይቀር ተቋሙ አሁን የደረሰበትን ውሳኔ እንደሚያብራራ ፓትሪክ ሐይኒሽ ይጠብቃሉ።

"ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር የሚወያዩት፣ ወደ ቦታው ተጉዘው ከማዕከላዊ ባንኩ ገዢ የሚገናኙት፤ ከፖለቲካ መሪዎች ጋር የሚነጋገሩት ባለሙያዎች በንድፈ ሐሳብ ወገንተኛ ሊሆኑ አይገባም። የሚሰሩት ሪፖርት ገለልተኛ በሆነ መንገድ መቅረብ አለበት" የሚሉት ፓትሪክ ሐይኒሽ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ገፊ ምክንያት አለው የሚለውን ክርክር ለመቀበል ይቸግራቸዋል።

"ፖለቲካዊ የሚሆነው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ነው። ምክንያቱም የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ አብላጫ ድምጽ አላቸው። የድርጅቱን ፕሮግራሞች እና ክፍያዎች ማገድ ይችላሉ። የየአገራቱን ጉዳይ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ትንበያ ሲሰሩ ፖለቲካዊ መነሾ ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ወዴት እያመራ እንደሆነ እርግጠኞች አይደሉም። ከባለሥልጣናቱ ጋር እየተወያዩ ነው። የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ሒደቱን ከተመለከትክ ብዙ ነገሮች አሁንም ግልጽ አይደሉም። እንዲህ አይነት ትንበያ እርግጠኝነት የጎደለው የሚያደርጉ በርካታ ተለዋዋጮች አሉ" ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት ሐይኒሽ "ባለፈው ሳምንት አይ.ኤም.ኤፍ የገለጻቸው ጉዳዮች ትክክለኛ ምክንያቶች ናቸው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ