1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል በአዲስ አበባ

ሐሙስ፣ ኅዳር 6 2005

መዲና አዲስ አበባ "ከለርስ ኦፍ ዘ ናይል" በሚል ርዕስ ዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫልን አዘጋጅታ ከዓለም የተሰባሰቡ አፍሪቃዊ ፊልሞችን ለአፍሪቃዉያን ፊልም አፍቃሪዎች እና ፊልም ሰራተኞች አቅርባለች።

https://p.dw.com/p/16jcV
ምስል DW

በፊስቲቫሉ መድረክ አሸናፊ ለተባሉ አፍሪቃዉያን ፊልም ሰራተኞች እና ስራዎቻቸዉ ሽልማት  ተበርክቶአል። የፊስቲቫሉ አላማ በተለይ በአፍሪቃዉያን ፊልም ሰራተኞች መካከል መግባባትንን መማማርን እንዲሁም የልምድ ልዉዉጥን ለማጠናከር እንደሆነ ተነግሮአል። ለአምስት ቀናት በዘለቀዉ በዚህ አፍሪቃዉያን የፊልም ስራ ድግስ ላይ ፤ ምን ጉዳዮች ተከናወኑ፤ አሸናፊዎችስ እነማን ነበሩ፤ ኢትዮጵያዉያን የፊልም ስራ አዋቂዎች እና ፊልም አፍቃሪዎች  ከፊስቲቫሉ ምን ይማራሉ፤ በለቱ ዝግጅታችን እንቃኛለን!
የከለርስ ኦፍ ዘ ናይል" ዓለም አቀፉ የፊልም ፊስቲቫል ላይ ምርጥ ፊልም በመባል ለሽልማት የበቃዉ ሪስትለስ ሲቲ የተሰኘዉ በይጀሪያዊዉ የፊልም ስራ አዋቂ የተቀናበረዉ ፊልም ነዉ። ምርጥ የሴት የፊልም ተዋናይ ኢትዮጵያዊትዋ ባለሞያ ሽልማትን አግኝታለች። በአጭር የምስል ፊልም ቅንብርም እንዲሁ «ሂሳብ» የተሰኘዉ በኢትዮጵያዊዉ የፊልም ባለሞያ የተቀናበረዉ አጭር ፊልም ሽልማቱን ወስዶአል። አዲስ አበባ ላይ ከጥቅምት 28 እስከ ኅዳር 2 የዘለቀዉ "ከለርስ ኦፍ ዘ ናይል" የተሰኘዉ ዓለም አቀፉ የፊልም ፊስቲቫል በአጠቃላይ 28 አገራት የተሳተፉበት  እና 58 አፍቃዉያን ፊልሞች ለእይታ የቀረቡበት እንደሆነ ተነግሮአል። የፊስቲቫሉ ዋና ተጠሪ ሲኒማቶግራፈር አቶ አብርሃም ሃይሌ በሀገራችን ይህን አይነት የፊለም መድረክ ለማዘጋጀት የበቁት ያዘጋጁት ከረጅም ግዜ ዉጥን በኋላ እንደሆን ይገልጻሉ።  በፊልም ስራ ጉዳይ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን በኔዘርላንድ እንዳጠናቀቁ የነገሩን ሲኒማቶግራፈር አቶ አብርሃም ሃይሌን ሲኒማቶግራፈር የሚለዉ ቃል እስከ ዛሪ አቻ አማርኛ አልተገኘለትምን ስንል ጠይቀናቸዉም  ነበር። መልስ ሰጥተዉናል! በፊስቲቫሉ የቀረቡት ፊልሞች የሚያሳዩት መልዕክት  በአፍሪቃ የፊልም ስራ ተወዳጅ መሆኑን እና እየዳበረ መምጣቱን  አመላካች ነዉ ያሉት አቶ አብርሃም፤ አፍሪቃዉያኑ ፊልም ሰራተኞች የአህጉሪቱን ገጽታ ባህል በማስተዋወቁ ረገድ ጥበባዊ ስራቸዉን ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ መሆኑንም  ሳይገልፁ አላለፉም። በዚሁ የፊልም ፊስቲቫል ላይ ከደቡብ አፍሪቃ፣ ከሴኔጋል ከናይጄሪያ ከሆላንድ እና ከፈረንሳይ ዳኞች ጋር ኢትዮጵያን ወክለዉ ለዉድድር የቀረቡትን ፊልሞች፤ ደረጃ የሰጡት የአስቴር ፊልም ዳሪክተር አቶ ሰለሞን በቀለ፤ አፍሪቃዉያን የፊልም ስራ አዋቂዎች፣ ስራዎቻቸዉ ገንዘብን ብቻ ያላለሙ ሳይሆን፤  ፊልሞቻቸዉ እያዝናኑ የአህጉሪቱን ገጽታ ብሩህ ገጽታ እንዲሁም ችግሮች፤ ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል ባይ ናቸዉ።  የዛሪ ሃያ አመት ግድም በኢትዮጵያ ከአራት ወራት በላይ ለህዝብ እይታ የቀረበዉ እና ከኢትዮጵያ የመጀመርያ ፊልሞች መካከል አንዱ የሆነዉ የ«አስቴር» ፊልም ባለቤት አቶ ሰለሞን በቀለ ወያ ፤ «ከለርስ ኦፍ ዘ ናይል» የፊልም ፊስቲቫል ልዩ የሚያደርገዉ በርካታ የአፍሪቃ የፊልም ሰራተኞች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ባለሞያዎች በፊስቲቫሉ በመገኘታቸዉ ነዉ ይላሉ።  የአንድ ሀገር ብልሹ ሁኔታ በፊልም እንደሚሰራጭ  ሁሉ የአንድን አገር መልከዓ ምድር፤ የህብረተሰቡን አኗኗር እና ባህል፤ እንዲሁም የህብረተሰቡን ፍላጎት በፊልም ጥበብ ለዓለም ማሳወቅ ይቻላል የሚሉት የፊስቲቫሉ ፕሪዝደንት አቶ አብርሃም ሃይሌ፤ ከፊስቲቫሉ ፊልም ሰራተኛዉ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ሀገር ብሎም አህጉሪቱ ተጠቃሚ መሆኗን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሚሰሩ ፊልሞች አብዛኞቹ ሃገራዊ ያልሆኑ ባህልን የማያንጸባርቁ ናቸዉ ፤ የሚል ነቀፊታ ይሰማል ለሚለዉ ሲኒማቶግራፈር  አብርሃምሃ ሃይሌ ወጣቱ ፊልም ሰሪ ሊበረታታ፤ ሊደገፍ እንዲሁም ትምህርትን ሊያገኝ ይገባዋል ሲሉ አስረድተዋል።
የሀገርን ገጽታ እና  እድገት የህዝቦችዋን ባህል፤ በሲኒማ ጥበብ ይበልጥ ለማስተዋወቅ፣ የፊልም ስራ ሞያ ድጋፍ እንደሚያስፈልገዉ መዘንጋት የለበትም ያሉንንን የፊልም ባለሞያዎች ለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን። የኢትዮጵያ ሲኒማ ጎልብቶ ጥበባዊ ይዞታዉ የጎላና፤ ዓለማቀፋዊ ተደራሽነት እንዲኖረዉ፤ የዓለም አቀፍ መድረኮችን በመዘርጋት፤ ባለሞያዎችን እና ስራዎቻቸዉን መተዋወቅ የጀመረበት ጥረት ሊበረታታ የሚገባዉ ይመስለናል፤ በማለት  የለቱን ቅንብሪን አጠናቀኩ አዜብ ታደሰ ነኝ፤ ሙሉዉን ቅንብር ያድምጡ!
       
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Colours of the Nile International Film Festival
ምስል DW
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ