ዓመቱ ሲታወስ፤ የአፍሪቃ አበይት ጉዳዮች በ2016
ከአሰቃቂ የሽብር ጥቃቶች እስከ ደፋር የአደባባይ ተቃውሞዎች፤ሥልጣን የሙጥኝ ብለው የቀሩ መሪዎች፤በምርጫ ተሸንፈው ተፎካካሪዎቻቸውን እንኳን ደስ አለዎ ለማለት የደፈሩ ፖለቲከኞች ከአፍሪቃ የ2016 ታሪኮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው
አይረሴው የተቃውሞ ምልክት
በሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጭ ፈይሳ ሊለሳ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ እጆቹን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ የኢትዮጵያ መንግሥትን እና በኦሮሞ ላይ የሚደርሰውን አፈና በመቃወም ነበር። በቢሾፍቱ ከተማ እንደ ፈይሳ ሁሉ እጆቻቸውን በማጣመር ተቃውሟቸውን በገለጡ ዜጎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ በመክፈታቸው በተፈጠረ ግፊያ እና መረጋገጥ ከ50 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የሽብር ጥቃቶች
እስላማዊ ተቃዋሚዎች ከባሕር ዳርቻ በምትገኘው የአይቮሪ ኮስት ግራንድ ባሳም ከተማ በሚያዝያ ወር በፈጸሙት ጥቃት 19 ሰዎች ገደሉ። ይኸ ግን የመጀመሪያው የሽብር ጥቃት አይደለም። በጥር ወር በማግሪብ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የአል-ቃዒዳ ክንፍ በኡጋዱጉ ከተማ በቡርኪናቤ ሆቴል ላይ ጥቃት ከፍቶ በርካቶችን ገድሏል። ከቡርኪናፋሶው ጥቃት ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ በማሊዋ የባማኮ ከተማ እገታ ነበር። ሰዎችም ተገድለዋል። ሽብር እንዲህ በምዕራብ አፍሪቃ ደረሰ
የቻድ የቀድሞ አምባገነን እድሜ ይፍታህ ፍርድ
ሒስዌኔ ሐብሬ በተከሰሱበት የጦር ወንጀል እድሜ ልክ ተፈርዶባቸዋል። ሰውየው ከጎርጎሮሳዊው 1982 ዓ.ም. ጀምሮ በሥልጣን በቆዩባቸው ስምንት ዓመታት 40,000 ሰዎች እንደተገደሉ ይገመታል። ብይኑ የተላለፈው በአፍሪቃ ኅብረት በሴኔጋል በተሰየመው አፍሪቃዊ ፍርድ ቤት ነበር። ሴኔጋል የቀድሞውን የቻድ አምባገነን ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት አሳልፋ ለመስጠት አልፈቀደችም።
ፍትኅ ለተደቆሱት የማሊ ቅርሶች
በቲምቡክቱ ከተማ የሚገኘው የሲዲ ያሃያ መስጂድ መስከረም 19 ቀን እንደገና ተከፍቷል። መስጂዱ ከስድስት ዓመታት በፊት በእስላማዊ ታጣቂዎች ድምጥማጡ ጠፍቶ ነበር። የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤የሳይንስ እና ባሕል ድርጅት በቅርስነት ለተመዘገቡት ቅርሶች ጥፋት ተጠያቂ ነው የተባለው አንሳር ዲን የተባለ የቱዓረግ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አባል የሆኑት አህመድ አል-ማሐዲ ላይ የዘጠኝ ዓመት እስራት በይኗል።
ያልተወደደው የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በአፍሪቃውያን ዘንድ በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ትችት ሲሰነዘርበት ነበር። ተቺዎቹ ፍርድ ቤቱ ሌሎች የዓለም ክፍሎት የሚፈጠሩ ኩነቶችን ችላ ብሎ ኢ-ፍትኃዊ በሆነ መንገድ አፍሪቃ ላይ አተኩሯል ሲሉ ወቅሰውታል። ቡሩንዲ፤ጋምቢያ እና ደቡብ አፍሪቃ ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት አባልነት ራሳቸውን አግልለዋል። ተቺዎች ግን አገራቱ የየራሳቸውን አወዛጋቢ መሪዎች ከተጠያቂነት ለማዳን ያደረጉት ነው ይላሉ።
ልጆቻችንን መልሱ
ለሁለት ዓመት ከግማሽ ከዘለቀ የማያባራ እርግጠኝነት ማጣት በኋላ ከቺቦክ ትምህርት ቤት ከተገቱ ልጃገረዶች መካከል 21ዱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በጥቅምት ወር ተገናኝተዋል። ልጃገረዶቹ የተለቀቁት ከቦኮ ሐራም ጋር በተደረገ ድርድር ነው። ከተለቀቁት በአስር እጥፍ የሚልቁ ልጃገረዶች አሁንም በእገታ ሥር ሲሆኑ የቦኮ ሐራም ታጣቂ ቡድን አሁም ሰሜናዊ ናይጄርያ እና አዋሳኝ አገሮችን ማሸበሩን ይዟል።
ይኸ ሰንደቅ አላማ-የዚምባብዌ ተቃውሞ
ፓስተር ኢቫንስ ማዋሪሬ የዚምባብዌ ዜጎችን ይኸ ሰንደቅ አላማ (#ThisFlag) በተሰኘ መፈክር ተቃውሞ ወደ ተግባር መሩት። «በሰንደቅ አላማችን ላይ የሚገኘው አረንጓዴ ምርታማነትን ይወክላል። ምንም አይነት ምርት ግን እያየሁ አይደለም» ይላሉ ፓስተሩ በማሕበራዊ ድረ-ገፆች በቪዲዮ ባሰራጩት መልዕክት። ኤኮኖሚያዊ ብልሹ አሰራር እና ብክነትን ለመቃወም የጀመሩትን ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተቀላቅለውታል። በሐምሌ ወር ተቃዋሚዎች ዋና ከተማ ሐራሬን ወጥረው ይዘዋት ነበር።
በኮንጎ ምርጫ የለም ተቃውሞ ግን አይሏል
ተቃዋሚዎች እና የሲቪክ ማሕበረሰብ አባላት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላን ተቃውመው በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አደባባዮች ወጥተዋል። ተቃዋሚዎቹ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. አዲስ ፕሬዝዳንት የመምረጥ እቅድ ነበራቸው። ነገር ግን ካቢላ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው በወርኃ ታኅሳስ ቢጠናቀቅም ፕሬዝዳንትነቱን ለማስረከብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ውረቱን ለመፍታት ድርድሮች እየተካሔዱ ነው።
የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት አበቃላቸው?
ዓመቱ ለደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በጎ አልነበረም። የአገሪቱ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኃላፊ ቱሊ ማዶንሴላ ይፋ ያደረጉት ዘገባ ኃብታሙ የጉፕታ ቤተሰብ በፕሬዝዳንቱ ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ እንዳላቸው አሳይቷል። የደቡብ አፍሪቃ ዜጎችም የታክስ ከፋዮች ገንዘብ ለዙማ የግል ቅንጡ መኖሪያ ቤት እድሳት ወጪ መደረጉን ሲሰሙ እጅጉን ተቆጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ በቀረበባቸው ተቃውሞ አልተነቃነቁም። የአገሪቱ ምክር ቤት የመተማመኛ ድምፅ ለመንፈግ ድምፅ ቢሰጥም ተርፈዋል።
የሞዛምቢክ ቀውስ
የነዳጅ ማጓጓዣ ተሽከርካሪ በሞዛምቢኳ ቴቴ ግዛት ፈንድቶ ከ70 በላይ ሰዎች ተገደሉ። ፍንዳታው የተከሰተው ከነዳጅ ማጓጓዣ ተሽከርካሪው በሕገ-ወጥ መንገድ ቤንዚን ሲቀዳ ነበር። አደጋው በአሳዛኝ ሁኔታ በሙስና የከሰረችው አገር ውድቀት መገለጫ ነበር። ሞዛምቢክ መፍትሔ ባልተገኘለት መንግሥታዊ ቀውስ ውስጥ ሆና በብሔራዊው ጦር እና ተቃዋሚ አማፅያን መካከል አነስተኛ ግጭቶችም ገጥሟት ነበር።
ጋምቢያ... ተዓምር ወይስ ቅዠት
በአስገራሚ ሁኔታ በተዓምራዊ የምርጫ ድል የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪው አዳማ ባሮው ለ22 ዓመታት ጋምቢያን የመሩት አምባገነን ያሕያ ጃሜሕን ተክተው ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ተመርጠዋል። ሁለተኛው አስደናቂ ነገር በምርጫ መሸነፋቸውን አምነው የተቀበሉት ጃሜሕ ቃላቸውን አጥፈው ሕጋዊው አሸናፊ እኔ ነኝ አሉ። የምርጫው ቀውስ ግን ገና አላባራም።
ምርጫ፤ ጋና ከፊት ትመራለች
ጋና የአፍሪቃ የዴሞክራሲ ተምሳሌት መሆኗን በድጋሚ አስመስክራለች። በሶስተኛ ሙከራቸው የተቃዋሚ እጩው ናና አኩፎ አዶ በታኅሳስ ወር የተካሔደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸንፈዋል። ተሸናፊው ጆን ማሓማ ተቀናቃኛቸውን እንኳን ደስ ያለዎ ብለው በምርጫው መሸነፋቸውን በጸጋ ተቀብለዋል። ድምፅ ሰጪዎች በደካማ ኤኮኖሚያዊ እድገት፤ የጸና የኃይል ቀውስ እና ሥራ አጥነት ምክንያት ድጋፋቸውን ነስተዋቸዋል።
የአፍሪቃዊዉ የሩምባ ንጉስ ስንብት
በቀደሙት ዓመታት በፓፓ ዌምባ ሞት ላይ በርካታ አሉባልታዎች ነበሩ። አሁን ግን ለጥርጣሬ ቦታ የለም። የ66 ዓመቱ ድምፃዊ እና የኮንጎ ሩምባ ሙዚቃ ዋርካ በአይቮሪ ኮስት አቢጃን መድረክ ላይ ወድቆ እስከ ወዲያኛው አሸልቧል። በዓለም የሙዚቃ መድረክ የኮንጎን ሥም ከፍ አድርጎ ያስጠራው ፓፓ ዌምባ ሞት በርካቶችን አሳዝኗል። እርሱ የሚጫወተው የኮንጎ አሊያም የአፍሪቃ ሙዚቃን እንደማይጫወት ተናግሮ ነበር- በቃ ሙዚቃን ብቻ እንጂ!