1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓመታዊ የስፖርት ክንውን

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2003

ለመጀመሪያ ግዜ አፍሪቃ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድርን በምድሯ ለማዘጋጀት በቃች። ቫንኮቨር ካናዳ ውስጥ የክረምት ኦሎምፒክ አስገራሚም አሳዛኝም ትዝታ ጥሎ አለፈ። ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ ዓለም ካዘቀጠችበት መቀመቅ ቀና እንድትል ያደረገ ክስተት ተፈጠረ። በዛው ልኩ ደግሞ እንደንጉስ የምታየውን የእግር ኳስ ኮከቧን በሞት ተነጠቀች። 2010 ዓ.ም

https://p.dw.com/p/QkVK
የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ስሜት
የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ስሜትምስል AP

በዛሬው የስፖርት ዝግጅታችን በ2010 ዓ.ም. ውስጥ የተከናወኑ አበይት ስፖርታዊ ክስተቶችን እንቃኛለን። ለዝግጅቱ ማንተጋፍቶት ስለሺ። የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ግዜ በተዘጋጀው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ደቡብ አፍሪቃ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ውድድሩን በማስተናገድ ብቃቷን አስመስክራለች።

በዚህ የአውሮፓውያኑ 2010 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪቃው የዓለም እግር ኳስ የዓለም የእግር ኳስ ፍልሚያ ሀምሌ አራት ቀን ሁለት ሺህ ሁለት ዓ.ም. ስፔን ኔዘርላንድን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ረታ የዋንጫው ባለቤት ሆነች። በወቅቱ የስፔን የቁርጥ ቀን ልጅ በመሆን መላ የስፔን ደጋፊዎችን ጮቤ ያስረገጠው አንድሬስ አኔስታ በደቡብ አፍሪቃ ከስታዲየም ሆኖ ደስታውን በዚህ መልኩ ነበር የገለጠው። «ሊታመን የማይችል ነው። እጅግ ከፍተኛ ጥረት የጠየቀንና ፈፅሞ ቀላል ያልነበረ ግጥሚያ ነው። ሆኖም የዓለም ዋንጫን በድል መጨበጥ ያ ልዩ ነው» በዚሁ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ታላቅ ውድድር በሶስተኝነት ያጠናቀቀው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንም ሃያልነቱን ለማስመስከር ችሏል።

የጀርመኑ አሰልጣኝ
የጀርመኑ አሰልጣኝምስል AP

በሩብ ፍፃሜው እንግሊዝን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ ልዩነት ሲረታ፤ ውጤቱ ያጋጣሚ እንዳልነበር በግማሽ ፍፃሜው አርጀንቲናን አራት ለምንም በሆነ ውጤት አንገት በማስደፋት አረጋግጧል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮአሂም ሎቭ በወቅቱ የቡድኑን ጥንካሬ በዚህ መልኩ ነበር የገለፀው። «በአጨዋወት ስልታችን፣ በቆራጥነት ባሳየነው የማጥቃት ድፍረት ልንደሰት ይገባል። መከላከል ብቻ ሳይሆን ወደፊት እየገፋንም ባሳየነው የአጨዋወት ስልታችን ደጋፊዎቻችንም የተደሰቱ ይመስለኛል» በደቡብ አፍሪቃው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ከአፍሪቃ እስከመጨረሻው ጥንካሬዋን ለማሳየት የቻለችው ጋና ብቻ ነበረች።

ጋና በግማሽ ፍፃሜው ውድድር በፍፁም ቅጣት ምት መለያ በኡራጋይ ሶስት ለሁለት እስከተሸነፈችበት ድረስ ለመዝለቅ ችላ ነበር። የዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ፤ እ.ጎ.አ. በ2018 ሩሲያ በ 2022 ዓ.ም. ደግሞ ቓታር የዓለም የእግር ኳስ ውድድርን እንዲያዘጋጁ ከሳምንታት በፊት መወሰኑም ይታወቃል። የአውሮፓውያኑ 2010 ዓ.ም. በስፖርቱ ዓለም ታላቅ የሆነ ሌላ ክስተትም አስተናግዷል። የቫንኮቨር ካናዳው የክረምት ኦሎምፒክ። በዚህ የመክፈቻ ውድድር ጆርጂያዊው አትሌት ኖዳር ኩማሪታሽቪሊ በልምምድ ወቅት ህይወቱ በማለፏ ውድድሩ ላይ ጥላ አጥልቶ ነበር። የክረምት ኦሎምፒክ ውድድሩ ሲጠናቀቅ አዘጋጇ ካናዳ በአስራ አራት የወርቅ ሜዳሊያ አንደኛ ስትወጣ ጀርመን በአስር ወርቅ ሁለተኛ ለመብቃት ችላ ነበር። አሁን ደግሞ ወደ አፍሪቃ መለስ ብለን ዋና ዋና ክስተቶችን እንቃኛለን።

የደርባኑ ስታዲየም
የደርባኑ ስታዲየምምስል AP

ታህሳስ ሰላሳሳ ሁለት ሺህ ሁለት ዓ.ም. በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ቀመር መሰረት ሊገባደድ የተቃረበው 2010 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት። አንጎላ ላይ ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር የቶጎ ብሔራዊ ቡድንን የጫነው አውቶቡስ የኮንጎንጎ ጠረፍን ተሻግሮ የአንጎላ ምድርን ረግጧል። የጠበቀው ግን እጅግ አስደንጋጭ አቀባበል ነበር። ቡድኑ በተሳፈረበት አውቶቡስ ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ድንገተኛ የተኩስ እሩምታ በርካቶች ሲቆስሉ የአውቶቡስ ሹፌሩ ህይወት ተቀጠፈ። ጥቃቱን የፈፀሙት በነዳጅ ሀብት ከበለፀገው የአንጎላ ሰሜናዊ ክፍል ለመገንጠል የሚፈልጉ አማፂያን መሆናቸው ተነገረ። በክስተቱ እጅግ በጣም የተደናገጠው የቶጎ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አንጎላን ጥሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ጥር ሁለት ቀን እዛው አንጎላ ላይ በተከፈተው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር አዘጋጇ ሀገር ማሊን እስከ ሰባ ስምንተኛው ደቂቃ ድረስ አራት ለዜሮ ስትመራ ቆየች። የማታ ማታ ግን ማሊዎች አንጎላ ላይ አከታትለው ባስቆጠሩት አራት ግብ ከአዘጋጇ ሀገር ጋር ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ቻሉ።

በዚሁ የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ፤ ጥር ሃያ ሶስት ቀን ሁለት ሺህ ሁለት ዓ.ም. ግብጽና ጋና ለፍፃሜ ደረሱ። እናም በግብፅ አንድ ለባዶ አሸናፊነት ውድድሩ ተጠናቀቀ። በውድድሩ ግብፅ ለሶስት ተከታታይ ግዜያት የአፍሪቃ ዋንጫን በመብላት በአፍሪቃ ዋንጫ ሀያልነቷን አስመሰከረች። ከዚሁ የአፍሪቃ ዋንጫ ታሪክ ሳንወጣ፤ በእግር ኳሱ ዓለም የአፍሪቃ ሀያል የሆነችው ግብፃን በሃያልነት ያርበደብድ የነበረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሃያል ቡድን አንድ ኮከብ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። እውቁ የእግር ኳስ ጠቢብ መንግስቱ ወርቁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ማህበረሰብ ማለትም በሴካፋ ውድድር በአራተኛነት ያጠናቀቀውም በዚሁ ዓመት ነበር። ቡድኑ በኡጋንዳ አራት ለሶስት ተሸንፎ አራተኛ ደረጃን ባገኘበት ውጤት ለዓመታት ካዘቀጠበት ቀና ቀና ለማለት ችሏል። በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ ሰላሳ ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝም በቅቷል። ኤርትራ አርባ አራተኛ፣ ሶማሊያ አርባ ዘጠነኛ፣ ጅቡቲ ሀምሳ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሱዳንና ኤንያ ደግሞ ሀያ አምስተኛና ሀያ ዘጠነኛ። በአፍሪቃ የእግር ኳስ ደረጃ ግብፅ አንደኛ፣ ጋና አይቮሪኮስትን አስከትላ ሁለተኛ ላይ ትገኛለች።

ወደ አትሌቲክሱ ስንመል ደግሞ በመላው ዓለም በስፖርቱ ዘርፍ ታላቅ ቦታ ያለው ኢትዮጲያዊው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ዓለምን ያነጋገረ ውሳኔ ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር። ሀይሌ በኒውዮርኩ ማራቶን ውድድር ወቅት እምባ እየተናነቀው ከሩጫው መሰናበቱን ገለፀ። ወዲያው ደግሞ ኒውዮርክ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ የሀይሌን አሰልጣኝ በማጣቀስ ሀይሌ ፖለቲካዊ ጫና ስላለበት ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ሲል ዘገበ። ብዙም ሳይቆይ አስልጣኙ ማስተባበያ ሰጡ።

ሀይሌም በህዝቡ ጥያቄ መሰረት በሚል ወደ አትሌቲኩሱ በድጋሚ መመለሱንና መደበኛ ልምምድ መጀመሩን ገለፀ። በዓለም ዙሪያ በተደረጉ የተለያዩ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተደጋጋሚ ድል ያስመዘገቡበት ወቅትም ነበር 2010 ዓ.ም. ሚያዝያ አስራ ሶስት ቀን ሁለት ሺህ ሁለት ዓ.ም. የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ፕሬዚዳንቱ ጁዋን አንቶኒዮ ሳማራንች በሰማንያ ዘጠኝ ዓመታቸው ነበር የሞቱት። ግንቦት አራት አትሌቲኮ ማድሪድ በተጨማሪ ሰዓት ፉልሀምን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት በመርታት የአውሮፓ ሊግ ዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቃ። ከእር ቀናት በኋላ ደግሞ ኢንተር ሚላን ባየር ሙኒክን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ የእሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሀያልነቱን አስመሰከረ።

ሰኔ አስራ ሰባት ደግሞ በዓለም የቴኒስ ውድድር ታሪክ ረዥም ሰዓት የፈጀው ውድድር ተመዘገበ። ከአስራ አንድ ሰዓታት በላይ በቆየው የዊንቤልደኑ ውድድር አሜሪካዊው ጆን ኢንሰር ፈረንሳዊው ኒኮላስ ማሁትን ሰባ ለስልሳ ስምንት በሆነ ጠባብ ልዩነት አሸነፈ። ይህ ረዥም ውድድር ለሶስስት ቀናት በተከታታይ የተደረገ ነበረ። በ2010 ዓ.ም. ውስጥ የተከናወኑ አበይት ስፖርታዊ ክስተቶችን ያስቃኘን ዝግጅታችን በዚህ ይጠናቀቃል። ለዝግጅቱ ማንተጋፍቶት ስለሺ ነኝ፤ ጤናይስጥልኝ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ