ዘመናዊ የሕክምና መረጃ አያያዝ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:59 ደቂቃ
05.12.2018

የተቀናጀ ዲጂታል የሕክምና አገልግሎት ሥርዓትን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አሠራር ይሰጣል

ቴክኒዎሎጂው የታካሚዎችን የምርመራ ሒደት፣ የሕክምና ክትትል ሥርዓት መዝግቦ የሚይዝ ሲሆን፣ የታካሚዎችን የሕክምና ታሪክ ጊዜ ሳይፈጅ ያለ ውጣ ውረድ ለማግኘት ያስችላል።

በየጤና ተቋማቱ የሚታየውን የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ ዋነኛ መፍትሄ እንደሆነ ይነገርለታል፤ ዲጅታል ሥርዓትን ያካተተው የሕክምና አገልግሎት። ይህ ዘመናዊ የሕክምና መረጃ አያያዝ የማኅበረሰቡን የተቀላጠፈ የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ችግር መቅረፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሲሆን የሕክምና መሠረተ ልማታቸው በተስፋፋው ሃገራት ሥራ ላይ ከዋለ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ቴክኒዎሎጂው የታካሚዎችን የምርመራ ሒደት፣ የሕክምና ክትትል ሥርዓት መዝግቦ የሚይዝ ሲሆን፣ የታካሚዎችን የሕክምና ታሪክ ጊዜ ሳይፈጅ ያለ ውጣ ውረድ ለማግኘት ያስችላል። 
እንዲህ ያለው ዘመናዊ የሕክምና መረጃ አያያዝ የታካሚዎችን እንግልት ከማስቀረቱም በላይ፣ የሐኪሞችን ድካምም እንደሚቀንስ ይታመናል። በዚህም የሕክምና ሒደቱን የሚያቀልል ቀልጣፋ አሰራር ነው።
ዲጅታል ሥርዓትን ስላካተተው የሕክምና አገልግሎት የመረጃ ቴክኖሎጂ ማለትም (የIT ባለሙያ) የሆኑት አቶ አንድነት ሀብታሙን አነጋግሬያለሁ። 
ይህን ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት መጠቀም ከጀመሩ የሕክምና ተቋማት አንዱ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከአንድ ዓመት በፊት ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለሆስፒታሉ ዲጅታል የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ዘርግቷል። በአሁኑ ሰአት 70 በመቶው የተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት በኤሌክትሮ ሜዲካል ሪከርዲንግ እንደሚሠራ ዶ/ር ዳዊት ወንድምአገኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ገልጸውልናል።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቀደም ሲል የነበረውን  የተለመደው በካርድ ላይ የተመሠረተ አሠራርን ቀይሮ የታካሚዎችን የሕክምና መረጃ እና ሙሉ የአገልግሎት መረጃ የያዘ የተቀናጀ ዲጂታል የሕክምና አገልግሎት ሥርዓትን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አሠራር ዘርግቷል። ሐኪሞች የታካሚዎችን ሙሉ መረጃ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ያስገባሉ፤ ይቀባበላሉ። አጠቃላይ የሕክምና ሒደቱን ከሌሎች ክፍሎች ጋር በማገኛኘትም የተቀላጠፈ ሥራን መሥራት ተችሏል። ይህ አሠራርም ታካሚው ካርድ አውጥቶ ከአንዱ የሕክምና ክፍል ወደ ሌላው ሲል ይገጥመው የነበረውን እንግልት አስቀርቷል። በካርድ አያያዙም ቢሆን መረጃ የመጥፋት እና የመበላሽት ችግሮችን እንዳስቀረ ነው የሚነገረው። 
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በዓመት ለ500,000 ታካሚዎች ህክምና ይሰጣል። በየቀኑ ከ2,600 እስከ 3,000 ተመላላሽ ታካሚዎችን ሲያስተናግድ፤ 600ዎቹ ደግሞ ተኝተው ይታከማሉ። እንዲህ ታማሚዎች በሚበዙበት የሕክምና ተቋም ዘመናዊውን ዲጂታል የህክምና መረጃ አያያዝ ሥርዓት መጠቀም አንዱን ታካሚ ከ10 እስከ 12 ደቂቃ በሚፈጅ ጊዜ ውስጥ ለመስተናገድ በቂ መሆኑ ነው የተገለጸው። ይህም የሥራ መዘግየትን አስቀርቶ በአጭር ጊዜ ታካሚዎችን ለማስተናገድ አግዟል ይላሉ የሆስፒታሉ ዳይሬክተር።
የተሻለ አሰራር ዘርግቶ መስራት አላማቸው እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ዳዊት በቴክኖሎጂው በመታገዝም የአግልግሎቱን ሽፋን ከ70 በመቶ ወደ 100 በመቶ በማሳደግ በየመሀሉ የሚፈጠሩ መጓተቶችን ለመቅረፍ ሆስፒታሉ እንደሚሠራም አመልክተዋል።
ዶ/ር ዳዊት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ቀጣይነት ባለው መልኩ በሌሎች የሕክምና ተቋማትም ሥራ ላይ እንዲውል እና ለኅብረተሰቡ የተቀላጠፈ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል። 


ነጃት ኢብራሂም

ሸዋዬ ለገሰ

ተከታተሉን