1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘመናዊ የጤና መረጃ አያያዝ

ማክሰኞ፣ መስከረም 25 2008

በበለፀጉት ሃገራት የመረጃ/ ኢንፎርሜሽን አደረጃጀት ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል። ወደሃኪም ቤት የሚሄዱ ህሙማን ስማቸዉን ገልፀዉ በዕለቱ የተሰማቸዉን የህመም ስሜት ከመግለፅ ባለፈዉ በየጊዜዉ ዝርዝር የጤና ይዞታቸዉን መግለጽ አይጠበቅባቸዉም።

https://p.dw.com/p/1GjaX
Symbolbild Technologie und Mensch
ምስል Fotolia/freshidea

ዘመናዊ የጤና መረጃ አያያዝ

የጤና ይዞታ ታሪካቸዉ በየጊዜዉ ይመዘገባልና ስማቸዉን ሰጥቶ መረጃዉን ማገላበጥ ብቻ ነዉ። ይህን አሠራር በዩናይትድ ስቴትስ ቱሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ዉልታ ለማ ወደኢትዮጵያ ለማሻገር መስመር ዘርግተዋል።

ዶክተር ዉልታ ለማ በ1980ዎቹ ከኢትዮጵያ ለትምህርት ከወጡ ወገኖች አንዷ መሆናቸዉን ይናገራሉ። መጀመሪያ በልጅነታቸዉ ሰዎች በወባ ሲሞቱ መስማታቸዉ ለዚህ በሽታ መከላከያ የሚሆን ክትባት የመፈልሰፍ ምኞት ነበራቸዉ። እናም በህክምናዉ ዘርፍ ትምህርት ጥናታቸዉን ገፉበት። እንደፈለጉት ክትባት መፍጠሩ ለጊዜዉ ባይሳካም በአዳጊ ሃገራት ዉስጥ መከላከልና መዳን ሲቻል ብዙዎችን በሚጎዱ የበሽታ ዓይነቶች ላይ ጥናታቸዉን ገፍተዉ PHD ዲግሪያቸዉን ሠሩ። እሳቸዉ ስለክትባት መፍጠር እያሰቡ ወደናሚቢያ በሄዱበት አጋጣሚ በዓለም ላይ የተገኙት የተለያዩ ክትባቶች እንደዚያች ባሉ ሃገራት ገና አለመድረሳቸዉን ይገነዘባሉ። ለዚህ ምክንያቶቹ በርከት ሊሉ ቢችሉም ዋነኛዉ ግን የስልት እና መንገድ ጉዳይ መሆኑን አስተዋሉ።

Diskussion um Vorratsdatenspeicherung
ምስል picture-alliance/dpa

በጤናዉም ሆነ በሌላዉ ዘርፍ ብዙዉን ጊዜ የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት ችግር በአዳጊ ሃገራት ዉስጥ መኖሩን በመገንዘብ ዶክተር ዉልታ ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህን ለማሻሻል ወጥነዉ ተንቀሳቅሰዋል። እሳቸዉ እንደገለፁልን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በጤናዉ ዘርፍ ያለዉ የመረጃ አያያዝ ማስተካከል እና በዘመናዊ ቴክኒዎሎጂ ታግዞ መሥራት የሚችል የሰዉ ኃይል ማፍራትን ግንባር ቀደም ተግባር ለማድረግ ወሰኑ። ብዙ ጊዜ አሉ ዶክተር ዉልታ ሰዎች ወደዉጪ ሄደዉ እንዲማሩ ይደረጋል፤ ቁጥራቸዉ ግን ከሁለት ከሶስት ላይበልጥ ይችላል። ለዚህ መፍትሄ የሚሆነዉ ለተፈለገዉ ዘርፍ የሚሆኑ መምህራንን ከዉጭ እያስመጡ በርካቶች ትምህርት እንዲቀስሙ ማድረግ ነዉ በሚለዉ ተግባቡ። በቁጥጥርና ምዘና ወይም ሞኒተሪንግ ኤንድ ኢቫሉዌሽን የድህረ ምረቃ ማለትም ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርትም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ። ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃም የመጀመሪያዉ ነዉ። በዩኒቨርሲቲዉም ከሀገሪቱ ዜጎች በተጨማሪ ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ አስተምሯል፤ አሁንም ያስተምራልም።

በአንድ ሀገር ለተለያየ ዘርፍ የሚዉል ገንዘብ መኖሩ ብቻዉን ዋጋ እንደሌለዉ የሚናገሩት ዶክተር ዉልታ ባለፉት ወራት በምዕራብ አፍሪቃ ተከስቶ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈዉ የኤቦላ ወረርሽኝ ያን ያህል ጉዳት ያደረሰዉ በመረጃ እጥረት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዉታል። ለዚህም ነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በጤናዉ ዘርፍ ተገቢ የመረጃ አያያዝና ፍሰት እንዲኖር ትኩረት የተሰጠዉ ሲሉም አስረድተዋል።

Mobiltelefon - PDA Blackberry
ምስል picture-alliance/dpa

ዶክተር ዉልታ የተሠራዉን ራሱ ሥራዉ ይግለፀዉ እንጂ መዘርዘሩ አያስፈልግም ባይ ናቸዉ። በእሳቸዉ እምነትም ለሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም ትምህርት ሊሆን የሚችል ተግባር ተከናዉኗል። በየሃኪም ቤቱ የጤና መረጃ የሚያደራጅ የሰለጠ የሰዉ ኃይል ለማፍራት በተደረገዉ ጥረትም ጤና ጥበቃ እና የትምህርት ሚኒስቴር የተቀናጀ ሥራ እንደሰሩ ነዉ ከዶክተር ዉልታ የተረዳነዉ። የተማሩትን ሥራ ላይ ለማሰማራትም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፈቃደኛነቱን ገልጿል።

በቴክኒዎሎጂ የታገዘ የተሻለ የጤና መረጃ ክምችትና አያያዝ ከተደራጀም ኅብረተሰቡ የሚፈልገዉን በቀላሉ ማግኘት እንደሚችልም ነዉ ዶክተር ዉልታ በእርግጠኝነት የሚናገሩት። ኢንተርኔትና ኮምፕዩተር በሌለባቸዉ አካባቢዎችም በተንቀሳቃሽ ስልኮች አስፈላጊዉን የጤና መረጃ ማግኘት የሚቻልበት ስልትም እንደሚቀየስ ነዉ እምነታቸዉ። ይህ ሁሉ ግን አሁን መጠናከር እንዳለበት ነዉ የሚያሳስቡት። ከምንም በላይ ደግሞ በዘርፉ የተማረ እና ከ10 ሺህ በላይ የሠለጠነ ኃይል መኖር እንዳለበትም ገልጸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ