1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘረኝነትን የሚቃወም ሠልፍ በጀርመን

እሑድ፣ ሰኔ 12 2008

ደቡባዊ ጀርመን ሙኒክ ዉስጥ «ለፀረ-ዘረኝነት ትግል እጅ ለእጅ እንያያዝ» በሚል መሪ መፈክር ዛሬ በከተማይቱ ሰብአዊ ሰንሰለት ሰርቶ ዘረኝነትን ያወገዘዉ ሕዝብ ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ ተገምቷል

https://p.dw.com/p/1J9c4
ምስል Imago/M. Westermann

ጀርመን ዉስጥ ዘረኝነትን በመቃወም እና ለስደተኞች ድጋፍ ለመስጠት በተለያዩ ከተሞች የሚደረገዉ የአደባባይ ሠልፍ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ነዉ የዋለዉ።በየከተማዉ አደባባይ እና ታሪካዊ ሥፍራዎች የተሰለፈዉ ሕዝብ እጅ ለእጅ እየተያያዘ፤ ረጅም «ሰብአዊ ሠንሠለት» ሰርቶ ዘረኝነትን ተቃዉሟል።ሠልፉን ያደራጁት በጀርመን የእስራኤል የባሕል ማሕበረሰብ፤ የእስላም መድረክ፤ የካቶሊክ፤ የአንገሊካን እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በጋራ ነዉ።ደቡባዊ ጀርመን ሙኒክ ዉስጥ «ለፀረ-ዘረኝነት ትግል እጅ ለእጅ እንያያዝ» በሚል መሪ መፈክር ዛሬ በከተማይቱ አደባባይ ሰብአዊ ሰንሰለት ሰርቶ ዘረኝነትን ያወገዘዉ ሕዝብ ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ ተገምቷል።የጀርመን ሕግ መምሪያ ምክር ቤት ቡድንስታግ ምክትል ፕሬዝደንት የአረንጓዴዉ ፓርቲ እንደራሴ ክላዉዲያ ሩት ለሙኒኩ ሰልፈኛ « ሙስሊም፤ ጂብሲ፤ ሮማ ወይም ስደተኛ እያሉ አንዱን ከሌላዉ አሳንሶ ማየትን ጨርሶ እንቀበልም» ብለዋል።ምሥራቅ ጀርመን ላይፕሲክ ከተማ ደግሞ ከሁለት ሺሕ በላይ ሕዝብ አደባባይ ወጥቷል።ርዕሠ ከተማ በርሊን ዉስጥ ለተመሳሳይ ሠልፍ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ነበር ተዘግቧል።ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሕዝብ የተሠለፈዉ ትናንት፤ ቦኹም-ምዕራብ ጀርመን ዉስጥ ነበር።8500 ሕዝብ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ