1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝክረ-ዓጼ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት

እሑድ፣ ግንቦት 5 2010

በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውውይይት እና የትብብር መድረክ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር ሲሉ ከወራሪው የእንግሊዝ ጦር ጋር ሲፋለሙ የተሰዉትን ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓጼ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ለመዘከር ፍራንክፈርት ከተማ ላይ ያዘጋጀው ልዩ ጉባኤ ትላንት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/2xeX2
Deutschland 150th anniversary of Emperor Tewodros celebration in Frankfurt
ምስል E. Fekade

በዝግጅቱ አቶ አንዱዓለም አራጌ የዕለቱ የክብር እንግዳ ነበሩ

ከቀትር በኋላ ዝግጅቱ በይፋ ከሚጀምርበት ሰዓት ቀደም ብለው ነበር አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የወጣቶች የመዝናኛ እና የስብሰባ ማዕከል " ሃውስ ዴር ዩጉንድ " ተብሎ በሚጠራው የስብሰባ አዳራሽ በሃገር ባሕል ልብስ ተሸልመው ሰንደቅ ዓላማና ልዩ ልዩ መፈክሮችን በመያዝ በደስታ እና በልዩ ስሜት ተውጠው በመኪናዎች በባቡሮች እና በአውቶቡሶች ተጓጉዘው መታደም የጀመሩት ።  ከታዳሚዎቹም መካከል የዓጼ ቴዎድሮስን ጨምሮ በቅርቡ ከእስር የተፈቱ የታዋቂ ፖለቲከኞች እና ሙያተኞች ምስል የሚታዩባቸውን በልዩ ልዩ ዲዛይኖች የተሰሩ ቲ- ሸርቶችን እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳትን በመልበስ የዝግጅቱን ድባብ ይበልጥ አድምቀውት ታይተዋል።

የጉባኤው ዋና ተጋባዥ እንግዳ እና ብዙዎች በጉጉት ይጠብቋቸው የነበሩት የቀድሞ የአንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትሕ ፓርቲ - አንድነት አመራር የነበሩት አቶ አንዱ ዓለም አራጌ በስፍራው መድረሳቸው ሲበሰር በማዕከሉ የታደመው ሕዝብ ደስታ ወሰን አጣ። አዳራሹ ድብልቅልቅ አለ።  የክብር እንግዳውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማልበስ እና የእንኳን ደህና መጡ ደስታ መግለጫ እቅፍ አበባ ሥጦታ በማበርከት እልልታው እና ጭፈራውን ሕዝቡ ማቅለጡን ቀጠለ ። " የዘመናችን የቋራው መይሳው ካሳ " በሚል አድናቆትም በመድረኩ ታዳሚዎች ተወድሰዋል ።በጥቅሉ እሳቸውን ጨምሮ ለሌሎችም ከእስር የተፈቱ እና አሁንም በማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ለሕዝብ ነጻነት የሚታገሉ የፖለቲካ እስረኞች ያለውን አድናቆት ድጋፍ እና ከፍተኛ ክብር ሕዝቡ ገልጿል።

Deutschland 150th anniversary of Emperor Tewodros celebration in Frankfurt
ምስል E. Fekade

"ሕይወት ማለት ነጻነት ነው። ነጻነት የሌለበት ሕይወት ብዙም ትርጉም አይሰጥም" የሚሉት አቶ አንዱዓለም ለነጻነት የሚደረግ እንቅስቃሴ መስዋዕትነትን እና ዋጋን እንደሚያስከፍል አስቀድሞ እያወቁ ለመሞትም ጭምር ተዘጋጅተው ወደ ሰላማዊ ትግሉ መግባታቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል. አሁን የሚታየው የአገሪቱ ታሪክ መቀየር እንዳለበት እና ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን እውነተኛ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንደሚኖርበትም ነው ያስገነዘቡት። የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በሃገር ውስጥም በውጭም የሚደረገውንም ከፍተኛ ጥረት አመስግነዋል።

አቶ አንዱዓለም ገዥው መንግሥት እስካሁን በስልጣን የተጓዘበት መንገድ ከበቂ በላይ እንደሆነና አሁን በኢትዮጵያ ጥገናዊ ሳይሆን የሥርዓት ለውጥ እንደሚያስፈልግ እግረ መንገድ ጠቁመዋል። በትጥቅ ትግልም ይሁን በሰላማዊ የትግል ሥልት የሚንቀሳቀሱ ኃይላትን የሚያሳትፍ ሃገራዊ ጉባኤ እንዲጠራም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ አንዱዓለም ከጥናታዊ ጽሁፍ ባሻገር በቅርቡ ያሳተሙትን "የሃገር ፍቅር ዕዳ " የተሰኘ መጽሐፋቸውንም ለታዳሚው በማስተዋወቅ አቅርበዋል። በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ እና የጉባኤው አስተባባሪ ከአሁን ቀደምም ተመሳሳይ ሃገራዊ መግባባትን እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶችን ማኅበሩ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች ማቅረቡን ገልጸውልናል።

በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውውይይት እና የትብብር መድረክ በአገር ቤትም በኦሮምያ እና አማራ ክልሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውውይይት እና የትብብር መድረክ ባዘጋጀው በዚህ ልዩ ጉባኤ ላይ የቀረቡት አገራዊ አንድነት የሚያጥናክሩ እና የቴዎድሮሥን ራዕይ የሚያመላክቱ  "የቴዎድሮስ አደራ " የተሰኘ አጭር ሙዚቃዊ ተውኔት እና ሃገራዊ ሥነ ግጥሞች ለዝግጅቱ ልዩ ድምቀትን ሰተውታል።

በአቶ አንዱ ዓለም አራጌ "ታሪክ የወረሰ ትውልድ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የግንባታ ሂደት ያጋጠሙት ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሃሳቦች " በሚል ርዕስ የተመረጠው የቀድሞውና የዘመኑ የፖለቲካ ሥርዓት አወቃቀር እና የዲሞክራሲ ትግል የተነጻጸረበት የተነጻጸረበት ጥናትም የፖለቲካ የግንዛቤ አድማስን የሚያሰፋ እንደነበር የጉባኤው ታዳሚዎ ገልጸዋል። የአጼ ቴዎድሮስ የቤተሰብ አባል እና አራተኛ ትውልድ የሆኑት አቶ አብዩ በለው ንጉሰ ነገሥቱ በቤተሰብ ዙሪያ ምን ዓይነት ሰብዕና እንደነበራቸው የገለጹበት ማብራሪያም ለጉባዔተኞቹ ግንዛቤን የሰጠ ነበር ።

ከዚህ ሌላ የቀድሞ የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ፕሮግራም ባልደረባ አንጋፋው ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ " የኢትዮጵያ አንድነት እና የዳግማዊ ዓጼ ቴዎድሮስ ራዕይ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን ጥናት በማቅረብ ለጉባኤው ታዳሚ አጋርቷል። 

Deutschland 150th anniversary of Emperor Tewodros celebration in Frankfurt
ምስል E. Fekade

ዳግማዊ ዓጼ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን የግዛት ሉዓላዊነት ለማስከበር እና ሃገሪቱን የዘመናዊ ሥልጣኔ ባለቤት ለማድረግ በነበራቸው ታላቅ ራዕይ ምክንያት ከወራሪው የእንግሊዝ ጦር ጋር ተፋልመው በጀግነነት ራሳቸውን ሰውተዋል። በወቅቱ የእንግሊዝ ጦር የ 7 ዓመት ልጃቸውን ልዑል ደጃዝማች አለማየሁን ጨምሮ ከ1.5 ቢልዮን የሚልቅ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና የከበሩ ቅርሶች ዘርፎ ወደሃገሩ ተመልሷል። የዓጼ ቴዎድሮሥ የመጀመሪያ ልጅ የራስ መሸሻ ካሳ የልጅ ልጅ አቶ አያሌው ካሳ መሸሻ የጉባኤው ተሳታፊ ነበሩ ። ለመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የአያታቸውን የታሪክ ገድል በማስታወስ እንዲህ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ::

 በርካታ ኢትዮጵያውያን የታደሙበት እና በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውውይይት እና የትብብር መድረክ በፍራንክፈርት ከተማ በትናንትናው ዕለት ያዘጋጀው ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ወራሪ ጦር ጋር ሲፋለሙ የተሰዉበት 150ኛው ዓመት የተጋድሎ ታሪክ ልዩ ዝክረ-ጉባኤ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዶ ምሽት ላይ ተጠናቋል። የጉባኤው አስተባባሪዎች እንደገለጹት በሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን መስዋዕትነት የሚከፍሉ የፖለቲካ እስረኞችን ሞራል ለማነቃቃት እንዲረዳ በማሰብ ልዩ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር የተካሄደ ሲሆን በዕውቅ ሰዓሊ የተዘጋጀ የዳግማዊ ዓጼ ቴዎድሮስ ምስልም በጨረታ ቀርቧል። አቶ አንዱዓለም አራጌ በኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ እና መስዋዕትነት ምሥጋና በማቅረብ የዳግማዊ ዓጼ ቴዎድሮስን ምስል በሥጦታ ተበርክቶላቸዋል። 

እንዳልካቸው ፈቃደ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ