1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀንስ ዲትሪሽ ጌንሸር ማንነት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 27 2008

እንደ ፖለቲከኛ የዛሬዋን ጀርመን የቀረፁ ፣ እንደ ምክትል መራሄ መንግሥት ለጀርመን ውህደት ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዓለም ዙሪያ ክብር የተቸራቸው ዲፕሎማት ነበሩ ፤ ባለፈው ሳምንት አርብ በሞት የተለዩት የቀድሞ የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ዲትሪሽ ጌንሸር ።

https://p.dw.com/p/1IPqn
Bildergalerie Der frühere Bundesaußenminister Hans-Dietrich Genscher
ምስል picture-alliance/dpa/J. Woitas

በምክትል መራሄ መንግሥትነትም ሆነ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለረዥም ጊዜ በማገልገል የመጀመሪያው የጀርመን ፖለቲከኛም ናቸው ። በሥልጣን ዘመናቸውም ለአውሮጳ ህብረት እና ለጀርመን ውህደት ባደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል ፤ የአውሮጳ ህብረት ምሥረታን እውን ያደረገው የማስትሪቹን ውል በመፈረም እንዲሁም የቀዝቃዛው ጦርነት እንዲያበቃ ከሶቭየት ህብረት እና ከምስራቅ ጀርመን ጋር በተካሄደው ድርድር ታሪክ ከሚያስታውሳቸው ዓለምም ከሚያከብራቸው ታላቅ ጀርመናውያን አንዱ ነበሩ ።ለ25 ዓመታት ጀርመን የኖሩት የፓለቲካ ሳይንስ ምሁርና የህግ ባለሞያ ዶክተር ለማይፍራሸዋ ጌንሸርን አስተዋይ ፖለቲከኛ ይሉዋቸዋል ጌንሸር በተለይ በጎርጎሮሳዊው መስከረም 30፣1989 በያኔዋ ቼኮዝሎቫክያ ዋና ከተማ ፕራግ በሚገኘው የምዕራብ ጀርመን ኤምባሲ ሰገነት ላይ ሆነው በኤምባሲው ለተጠለሉና ወደ ምዕራብ ጀርመን መሄድ ለሚፈልጉ የምሥራቅ ጀርመን ዜጎች ያበሰሩት የምሥራች ዛሬም ህይው ሆኖ ስማቸውን ያስጠራል ።«ዛሬ እዚህ እናንተ ጋ የመጣነው የእናንተ ጉዞ መጽደቁን .ልንነግራችሁ.ነው»ጌንሸር አረፍተ ነገሩን ሳይጨርሱ ህዝቡ በደስታ ገነፈሎ መጮህ ጀመረ ። ያኔ ምሥራቅ በርሊን ውስጥ ተማሪ የነበሩት እና ጀርመን ሲኖሩ ከ31 ዓመት በላይ ያስቆጠሩት አቶ መስፍን አማረ ፣ጌንሸር በወቅቱ የህዝብን ፍቅር ያተረፉ ዲፕሎማት እንደነበሩ ያስታውሳሉ ።

Genscher Botschaft in Prag 30.09.2014
ምስል picture-alliance/dpa/Filip Singer

ሃንስ ዲትሪሽ ጌንሸር የተወለዱት በዛክሰን አንሃልት ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ በምትገኘው በምሥራቅ ጀርመንዋ በሃለ ከተማ ራይደቡርግ በጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 21፣ 1927 ነው ። የህግ ባለሞያ የነበሩት አባታቸው ጌንሸር በ9 ዓመታቸው ነው በሞት የተለዩዋቸው ። በ16 ዓመታቸው በናዚ ጀርመን አየር ኃይል ድጋፍ ሰጭ ክፍል ውስጥ መሥራት የጀመሩት ጌንሸር በርሊንን ለማስለቀቅ በተካሄደው የሞት ሽረት ውጊያ ተሳትፈዋል ። ጀርመን ስትሸነፍ ለሁለት ወራት የጦር እስረኛ ነበሩ ።የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ሲቃረብ ርሳቸውና ሌሎች ወታደሮች በመከላከያ ክፍላቸው አማካይነት የናዚ ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ተደረገ ። ርሳቸው ግን ይህን እንደማያውቁ ነው ኋላ ላይ የተናገሩት ።ወጣቱ ጌንሸር ከጦርነቱ በኋላ ፊቱንን ወደ ትምህርቱ ነበር ያዞረው ።በምሥራቅ ጀርመኖቹ በሃለ እና በላይፕዚሽ ዩኒቨርስቲዎች በጎርጎሮሳውያኑ ከ1946 እስከ 1949 ህግና ኤኮኖሚክስ አጠኑ ። በ1946 የምሥራቅ ጀርመኑ ለዘብተኛ ዲሞክራት ፓርቲ LDPD አባል ሆኑ ።እዚያም አልቆዩም ። በ1952 ወደ ምዕራብ ጀርመን በመሄድ ለዘብተኛውን የነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲ ተቀላቀሉ ። ከሁለት ዓመት በኋላ በሰሜን ጀርመንዋ በሀምቡርግ ለህግ ባለሞያነት የሚያበቃቸውን ሁለተኛ ብሔራዊ ፈተና ወስደው ብሬመን ውስጥ በህግ ባለሞያነት ማገልገል ጀመሩ ። በፓርቲያቸው በFDP በምክር ቤት የተወከሉ አባላት ቡድን ረዳት ተመራማሪ ሆነው ነበር በ1956 ሥራ የጀመሩት ። በዚሁ ሃላፊነት እስከ 1959 ሰርተዋል ። 1959 እስከ 1965 ደግሞ የፓርቲው አስተዳደር ውስጥ ሰርተዋል ። ከ1962 እስከ 1964 የፓርቲያቸው ብሔራዊ ፀሃፊ የነበሩት ጌንሸር ከ1965 እስከ 1998 የምዕራብ ጀርመኑ የኖርድ ራይን ቬስትፋልያ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ፓርላማ አባል ነበሩ ። ጌንሸር ፓርቲያቸው FDP ከሶሻል ዴሞክራቶች ጋር ተጣማሪ መንግሥት በመሰረተበት በጎርጎሮሳዊው 1969 በመራሄ መንግሥት ዊሊ ብራንድት መንግሥት የአገር አስተዳደር ሚኒስትር ነበሩ ። ጌንሸር ለዚህ ለከፍተኛ ሥልጣን ከበቁ በኋላም የሃገራቸው የጦርነት ታሪክ በመንግሥታቸውና በህዝቡ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ለማስቀረት ባደረጓቸው ጥረቶች ከፍተኛ ውጤቶች ላይ ለመድረስ የበቁ ታላቅ ሰው መሆናቸውን አቶ መስፍን አማረ ያስታውሳሉ ።

Hans-Dietrich Genscher UNESCO Konferenz Chemiewaffen Paris Frankreich 1989
ምስል picture-alliance/AFP/ Perry

በ1974 ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል መራሄ መንግሥት የሆኑት ጌንሸር ጀርመን ከተዋሃደች በኋላም እስከ 1992 በነዚህ ሃላፊነቶች ላይ ለ18 ዓመታት ቆይተዋል ። ከ1974 እስከ 1985 የፓርቲያቸው የFDP ሊቀመንበር ነበሩ ።በዚሁ ወቅት ጌንሸር በ1982 ሶሻል ዴሞክራቶች በመተው ከክእህትማማቾቹ ከክርስቲያን ዴሞክራት ና ከክርስቲያን ሶሻል ህብረት ጋር ተጣማሪ መንግሥት መሰረቱ ። ሶሻል ዴሞክራቱን መራሄ መንግሥት ሄልሙት ሽሚትን በክርስቲያን ዴሞክራቱ ሄልሙት ኮል የተካው ይህ ውሳኔያቸው ብዙ አወዛግቧል ። ፓርቲው ከተጣማሪው ከሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር በተለይ በምጣኔ ሃብትና በማህበራዊ ጉዳዮች ፖሊሲ ላይ ልዩነቱ እየሰፋ መሄዱን ነው እንደ ምክንያት ያቀረበው። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ጌንሸር ምሥራቅና ምዕራቡን ዓለም ለሚያግባባ የፖለቲካ መርህ ነበር የሚቆሙት ። ከሶቭየት ህብረት ጋርም የምሥራቅ ምዕራብ ውይይት እንዲቀጥል የሚያያደርግ ፖሊሲ ነበር የሚያራምዱት ።ጌንሸር ዓለም ዓቀፍ ችግሮች በድርድር ይፈታሉ በሚለው ጠንካራ አቋማቸውም ይታወቃሉ ።በዚህ የዲፕሎማሲ ጥበባቸውም «ሁለት የሉፍትሃንሳ አውሮፕላኖች አትላንቲክ ውቅያኖስን ሲያቋርጡ ጌንሸር ሁለቱም ውስጥ ይኖራሉ »እስከ መባልም ተደርሶ ነበር ።በተለይ ጌንሸር ምዕራባውያን የማይደግፉ በሚያስመስሏቸው በአንዳንድ አቋማቸው ምክንያት አሜሪካንን ያስቆጡ ነበር። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ጌንሸር መሃል መንገድ መያዛቸው ጀርመን ጠንከር ያለ እርምጃ እንድትወስድ የሚፈልጉትን የአሜሪካን ፖሊሲ አውጭዎችን ያበሳጭ ነበር ። ጀርመን የኔቶ አባልነቷን ሳታጣ የምሥራቁ ና የምዕራቡ ዓለም አገናኝ ድልድይነት ሚና እንዲኖራት የማድረጉ የጌኔሸር ጥረት በአሜሪካውያን ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም ።ጌንሸር በሥልጣን ዘመናቸው በ1980 ዎቹ የኔቶ የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎች ጀርመን መተከላቸውን ተቃውመዋል ።በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የነበሩት የሮናልድ ሬገን አስተዳደር ጀርመን ከምዕራባውያን ህብረት ወጥታ የራስዋን መርሃ ግብር መከተል ጀመረች ወይ የሚል ጥያቄ እስከ ማንሳት ደርሰው ነበር በ1984 ከኢራኑ አብዮት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴህራንን በመጎብኘት የመጀመሪያው የምዕራብ ሃገር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ ። ከዚሁ ጎን ለጎን በ1980 ዎቹ የአውሮፓ ህብረትን መሰረት ለመጣል በርካታ ጥረቶች ሲያካሂዱ ነበር ። ። ከዚያም በኋላ አውሮፓ የጋራ መገበያያ ገንዘብ እንዲኖረው ግፊት ያደርጉ ከነበሩ ፖለቲከኞችም አንዱ ነበሩ ። ለረዝም ጊዜ በምክትል መራሄ መንግሥትነትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነር ያገለገሉት ጌንሸው ጌንሸር በ1992 ከ23 ዓመታት አገልግሎት በኋላ በፈቃዳቸው ከፌደራል መንግሥት የሥራ ሃላፊነት ተሰናበቱ ። ጌንሸር ከፌደራል መንግሥቱ ፖለቲካ ቢገለሉም በፓርላማ አባልነት ቀጥለዋል ። ከበስተጀርባ ሆነው ለፓርቲያቸው ለነፃ ዴሞክራቶች ፖርቲ ድጋፍ መስጠታቸውን አላቆሙም ።

Deutsche Wiedervereinigung 1990
ምስል picture-alliance/dpa

በበርካታ ጠንካራ ጎኖቻቸው የሚወደሱት ጌንሸር በ1991 በዩጎዝላቪው ጦርነት ለቀድሞዎቹ የዩጎዝላቭያ ግዛቶች ለክሮኤሽያና ለስሎቬንያ በግንባር ቀደምትነት እውቅና መስጠታቸው ከሚያስተቻቸው ውሳኔዎች አንዱ ነው ። ጌንሸር ዲፕሎማሲያዊ እውቅና የሰጡት ውጊያውን ያስቆማል በሚል ተስፋ ቢሆንም የዚያን ጊዜው የተመድ ዋና ፀሃፊ ሃቭየር ፔሬዝ ደኬያር ጀርመን ለክሮኤሽያና ለስሎቬንያ እውቅና መስጠትዋ በቀድሞዋ ዩጎዝላቭያው ግጭት ሊያባብስ እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር ።ይህን ዶክተር ለማ ይህን የጌንሸር ውሳኔ አጠያቂ ብለውታል ።

የጀርመንን ስም ለማደስ፣ ለአውሮጳ ህብረትና ለጀርመን ውህደት እንዲሁም ቀዝቃዛው ጦርነት እንዲያበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ታሪክ የሚያስታውሳቸው ታላቁ ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ሃንስ ዲትሪሽ ጌንሸር ባለፈው አርብ ከቦን ወጣ ብሎ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አርፈዋል ። ጌንሸር 89 ዓመታቸው ነበር ። በጌንሸር ማንነት ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ ያበቃል ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ