1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍፃሜ 70 ኛ ዓመትና ጀርመናውያን

ዓርብ፣ ሚያዝያ 30 2007

በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ የተፈጀበት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያበቃበት 70ኛው ዓመት ሰሞኑን ጀርመን ውስጥ በተለያዩ ዝግጅቶች እየታሰበ ነው ።

https://p.dw.com/p/1FKFl
Deutschland Berlin Illustration Brandenburger Tor bei Kriegsende im April 1945
ምስል picture-alliance/dpa/H. Wiedl

15742478#link:18256868#link:18217700#link:6364531#link:17221562በዓለም ታሪክ እጅግ ብዙ ህዝብ ያለቀበት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ኃያላን መንግሥታት በሁለት ጎራ ተሰልፈው ያካሄዱት እስከዛሬ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ከባድ ጦርነት ነው ። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው ፋሺሽት ኢጣልያ የዓለም መንግሥታት ማህበር አባል የነበረችውን ብቸኛ አፍሪቃዊት ሃገር ኢትዮጵያን በመስከረም 1928 መውረር እንደጀመረች ቢሆንም ን አውሮፓውያንና ሌሎችም የጦርነቱ መነሻ የሚያደርጉት የጎርጎሮሳዊውን መስከረም 1 1939 ማለትም ነሐሴ 8 1931 ጀርመ ን ፖላንድን የወረረችበትን ዕለት ነው ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ30 በላይ የሚሆኑ ሃገራት 100 ሚሊዮን ህዝቦች በቀጥታ ተካፍለዋል ።የጦርነቱ ዋና ተዋናዮች አጠቃላይ የኤኮኖሚ የኢንዱስትሪና የሳይንስ አቅማቸውን ሙሉ በሙሉ ባዋሉበት በዚህ ጦርነት ከ50 እስከ 80 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ አልቋል ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጦርነቱ ለኳሽ በናዚ ጀርመን ሽንፈት በተባበሩት ተጓዳኝ ኃይሎች ማለትም በአሜሪካን በብሪታኒያ በፈረንሳይ ና በሶቭየት ህብረት ድል አድራጊት ካበቃ በዚህ ሳምንት 70 ዓመት ሆነው። በጎርጎሮሳዊው በ1945 ግንቦት መጀመሪያ ላይ ዋና ከተማይቱ በርሊን በሶቭየቶች እጅ ስትወድቅ ተሸናፊው የናዚ ጀርመን ጦር እጁን ሰጥቷል ።በኋላም ግንቦት 8 ፣ 1945 የድል አድራጊዎቹ ተጓዳኝ መንግሥታት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት በተገኙበት የናዚ ጀርመን የተለያዩ ክፍለ ጦሮች የበላይ አዛዦች በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ጀርመን ያለ አንዳች ቅድም ግዴታ እጅ መስጠቷን በካርልስሆርስት በርሊን በሃገሩ ሰዓት አቆጣጠር ለእኩለ ለሊት 15 ደቂቃ ሲቀረው በፊርማቸው አረጋገጡ ። ይህም ጀነራል አልፍሬድ ዮሰፍ ፈርዲናድ ዮድል በተባለ የጀርመን የመከላከያ ኃይል ከፍተኛ የጦር አዛዥ በራድዮ ተነገረ ።

Flash-Galerie Ende 2. Weltkrieg Kapitulation Wilhelm Keitel in Berlin Karlshorst
ፊልድ ማርሻል ቪልሄልም ካይትልምስል picture-alliance/akg

«እኛ ከዚህ በታች ፊርማችንን ያስቀመጥን የጦር አዛዦች ያለ አንዳች ቅድመ ግዴታ ሃገሪቱ እጅ መስጠትዋን እናረጋግጣለን።ስለሆነም በምድር በባህርና በአየር የተሰማሩ እስካሁን በጀርመናውያን የሚታዘዙ ኃይሎቻችንን በሙሉ በሶቭየት ቀዩ ጦር የበላይ አመራር ስር መሆናቸውን እናረጋግጣለን»

የጀርመንን ሽንፈት በፊርማቸው ያረጋገጡት የናዚ ጀርመን የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ፊልድ ማርሻል ቪልሄልም ካይትል፣ የአየር ኃይሉ አዛዥ ሃንስ ዩርገን ሃንስ ሽቱምፕፍ ና የባህር ኃይሉ አዛዥ አድሚራል ሃንስ ጌዮርግ ፎን ፍሪድቡርግ ናቸው ።የሙኒኩ የታሪክ ተቋም ባልደረባ የታሪክ ምሁሩ ዮሐንስ ሁርተር ያኔ የሆነውን አሰገራሚ ነው የሚሉት ።

«ጀርመን እጅ መስጠትዋን ያረጋገጠው የያኔው የጀርመን መንግሥት ሳይሆን የጦር ኃይሉ ነው ።በህጋዊ አመለካከት ይህ በነዚያ ቀናት ከተፈፀሙት አስገራሚ ነገሮች አንዱ ነው ።»

እነዚህ የጦር አዛዦች ናዚ ጀርመን እጅዋን መስጠትዋን በፊርማቸው ያረጋገጡት የያኔው የናዚ ጀርመን መሪ አዶልፍ ሂትለር ከአንድ ሳምንት በፊት ህይወቱን ካጠፋ በኋላ በይፋ ከተኩት ከፕሬዝዳንት ካርል ዶኔትስ ጋር ከተካሄደ ምክክር በኋላ ነበር ።ያኔ የዶኔትስ መንግሥት ከመናገሻዋ ከተማ ከበርሊን ሸሽቶ ሰሜን ጀርመንዋ ፍሌንስበርግ ከተማ ነበር የሚገኘው ።ከካርልስሆርስቱ ፊርማ በኋላ ግን ወደ በርሊን ተመልሷል ።ግንቦት 23 ፣ 1945 ፕሬዝዳንቱ ዶኔትስና የመንግሥታቸው አባላት በሙሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ ። ግንቦት 23 ፣ 1945 ፕሬዝዳንቱ ዶኔትስና የመንግሥታቸው አባላት በሙሉ በእንግሊዞች በቁጥጥር ስር ዋሉ ። ጀርመኖች እጅ መስጠታቸው ይፋ እንደሆነ የያኔው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል እለቱን ከማናቸውን ቀናት የላቀ ሲሉ በማወደስ የድሉን ዜና ለህዝባቸው ዳግም አበሰሩ ።

Flash-Galerie Ende 2. Weltkrieg Kapitulation Wilhelm Keitel in Berlin Karlshorst
ፊልድ ማርሻል ቪልሄልም ካይትልምስል picture-alliance/akg

« ይህ የናንተ ድል ነው ። ለነፃነት የተገኘ ድል ። በረዥሙ ታሪካችን ከዛሬዋ ቀን የበለጠ ታላቅ ቀን የለንም ።»

ናዚ ጀርመንና የጀርመን ጦር ኃይል ድል መሆኑ የተበሰረበት ማስታወቂያ ሲነገር ሉነበርግ በተባለችው የሰሜናዊት ጀርመን ከተማ ከተማ የህዝቡ ስሜት ምን ይመስል እንደነበረ የብሪታኒያ የዜና ማሰራጫ ኮርፖሬሽን ቢቢሲ በዚያ የነበሩት ጀርመኖች ምንም ዓይነት አስተያየት ሲሰጡ እንዳልተሰማ ነበር የዘገበው ።

«ማስታወቂያው ሲነገር ጀርመናውያን ቆመው ሳይንቀሳቀሱ አንድም አስተያየት ሳይሰጡ መልዕክቱን በፀጥታ ሲያዳምጡ ነበር ። የሉነበርግ ነዋሪዎች እንዴት እጃቸውን እንደሚሰጡ መመሪያ ሲሰጣቸው ለጊዜው ፀጥ ካሉ በኋላ ምንም ሳይናገሩ መበታተን ጀመሩ ።»

ጀርመን እጅ የመስጠትዋ ዜና ከተሰማ በኋላ በርካታ ናዚዎችና ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም በጠላት እጅ በመውደቃቸው እንሰቃያለን ብለው የሰጉ ሌሎች ጀርመናውያን ህይወታቸውን በገዛ እጃቸው አጥፍተዋል ። በሺህዎች ከሚቆጠሩት ከነዚህ ሰዎች መካከል ዜናው በመላ ጀርመን በተዳረሰበት በማግስቱ ግንቦት 9 ፣1945 ህይወታቸውን ያጠፉት ኒደርሽላይሸን ከተማ ውስጥ ግላትስ በተባለው አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ባልና ሚስት ይገኙበታል ።የጀርመናዊው የላቲን ቋንቋ መምህር የዮሐንስ ታይነርት ባለቤት ሂልደጋርት ታይነርት በባለቤታቸው የማስታወሻ ደብተር ላይ «ጦርነቱ አብቅቷል ፤ የጠመንጃ ድምጽም አይሰማም »የሚሉ ዐረፍተ ነገሮችን አሰፈሩ ።ብዙም ሳይቆዩ ዮሐንስ ታይነርት በሽጉጥ መጀመሪያ የባለቤታቸውን ከዚያም የራሳቸውን ህይወት አጠፉ ።ፎርፖመርን በተባለው የጀርመን ግዛት ውስጥ በምትገኘው ዴምኒን በተባለችው አነስተኛ ከተማ ውስጥ ከ700 እስከ 1 ሺህ እንደሚደርሱ የተገመቱ ጀርመናውያን ከናዚ ሽንፈት በኋላ ህይወታቸውን በገዛ እጃቸው አጥፍተዋል ። ከናዚ ጀርመን ሽንፈት በኋላ አንዳንድ ጀርመናውያን ህይወታቸውን በገዛ እጃቸው ካጠፉበት ምክንያት ውስጥ ፀፀትና ፍርሃት ዋነኛዎቹ መሆናቸውን «ልጄ ሆይ ራስን በጥይት እንደምትገድል ቃል ግባልኝ »የተሰኘው መፀሀፍ ደራሲ ጀርመናዊው ፍሎርያን ሁበር ያስረዳሉ ።

70 Jahre Kriegsende Westwall Siegfriedlinie
ድል አድራጊዎቹ ወታደሮች ወደፊት ሲገሰግሱምስል picture-alliance/dpa

« እንግዲህ የራስን ህይወት የማጥፋቱ ምክንያት በመጀመሪያ ደረጃ የተለያዮ ገጽታ አለው ። በአንድ በኩል የጠላትን በመጀመሪያ ደረጃ የሶቭየት ህብረትን ጦር በመፍራት ነው ። ብዙዎቹ በፈፀሙት ግፍ የጥፋተኛነት ስሜት ነበራቸው ። በዚህም የተነሳ በኋላ ሊከተል የሚችለውም ፍርሃት አስፍኖባቸው ነበር ።አብዛኛዎቹ ከ12 ዓመታት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በኋላ ዓለም ምን ልትመስል እንደምትችል መገመት የተሳናቸው ነበሩ ።»

Karlshorst, 1945
ናዚ ጀርመን ካርልስሆርስት በርሊን እጅዋን መስጠትዋን በፊርማ ያረጋገጠችበት ቤትምስል Deutsch-Russisches Museum, Berlin-Karlshorst

በሌላ በኩል በናዚዎች ግፍና መከራ ለተፈፀመባቸው በርካታ ሰዎች ዜናው ደስታና ፈንጠዝያን ነበር ያስከተለው ። ናዚ ጀርመኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሰዎች ይገደሉና በቁም ይሰቃዩበት ከነበረበት ትልቁ የፖላንዱ የአውሽቪትዝ ማጎሪያ በህይወት የተረፉት የ90 ዓመትዋ አዛውንት ኤስተር ቤጃራኖ ዜናው እንደተሰማ ፈንቅሏቸው የወጣው ደስታ እንዳስጨፈራቸው ያስታውሳሉ ።

Deutschland Zweiter Weltkrieg, Einmarsch der Alliierten
ምስል picture-alliance/dpa

«ሁላችንም በአንድ ላይ ክብ ሰርተን ደንሰናል ።እኔ እየዘፈንኩ ያ ለኔ ነፃነቴ ነበር ። ያኔ ነፃ ሰዎች መሆናችንን አውቀናል ። »

ናዚ ጀርመኖች ሰዎችን ይገድሉና ቁም ስቅል ያሳዩባቸው የነበሩት የተለያዩ የማጎሪያ ስፍራዎች የተያዙ ሰዎች ናዚዎች ሽንፈታቸውን በይፋ ካሳወቁበት ግንቦት 8 ፣ 1945 በፊት ነበር ነፃ እንዲወጡ የተደረጉት ። በተለያዩ ካምፖች ውስጥ ከነበሩት ከነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ ከተያዙበት ሲለቀቁ መሄጃም ያጡ እንደነበር ነው የታሪክ ምሁሩ ዮሐንስ ሁርተር የተናገሩት ።

«ከናዚ ጀርመን አገዛዝ በኋላ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤት አልባ ሆነው ነበር ። ብዙዎች በግዳጅ ሥራ የተሰማሩ የጦር እስረኞች ስደተኞች ቀድሞ ማጎሪያ ውስጥ የነበሩ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ነበሩ ። ፍርሃት ና ጥቃቱ የሚረሳ አልነበረም ከዚህም በላይ እግሬ አውጭኙ ስደትና መሳደዱ ከትውልድ ቦታ መፈናቀሉና ሃገር አልባ የመሆኑ ስሜት ተደበላልቆባቸው ነበር ።»

ግንቦት 8 ፣ 1945 በይፋ ያበቃው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከዚያም በላይ ሊዘልቅ ይችል እንደነበረ ነው የሚነገረው ። የጦርነቱ ፍጻሜ እንዲፋጠን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ተጓዳኞቹ ኃይሎች ከሁለት ወር በፊት ማለትም በመጋቢት ወር ምዕራብ ጀርመን ሬማገን ያለውን የሉደንዶርፍን ድልድይ መቆጣጠራቸው ነው ። ።የአሜሪካን ጦር መጋቢት 7 1945 የያዘውን ይህን ድልድይ ናዚ ጀርመን ብዙ ጊዜ ለማውደም ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል ።በወቅቱ በታላቁ የራይን ወንዝ ላይ ከነበሩት 40 ድልድዮች ውስጥ አንዱ የነበረው የሉደንዶርፍ ድልድይ መያዙ የተጓዳኞቹ ኃይል ወታደሮች ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ጀርመን በቀላሉ ገስግሰው ድሉን እንዲያፋጥኑ ምክንያት መሆኑ ይነገራል ። ያኔ ናዚ ጀርመንን ተባብሮ ይወጋ የነበረው ተጓዳኙ ኃይል ድልድዩ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ባሉት 3 ሳምንታት ሩር ወደ ተባለው ወደ ጀርመን የኢንዱስትሪ አውራጃ 25 ሺህ ወታደሮችን ለማሻገር ችለዋል ። ከዚያ ቀደምሲል የናዚ ጦር የሽንፈቱን ቁልቁለት የተያየዘው በአሁኑ ቮልጎግራድ በያኔው ስታሊን ግራድ በምትባለው የሶቭየት ህብረት ከተማ ከነሐሴ 23 1942 እስከ የካቲት ሁለት 1943 በተካሄደ ከበባና ውጊያ የተቀዳጀው ወሳኝ ድል ነው ።

Deutschland 2. Weltkrieg Brücke von Remagen
የሉደንዶርፉ ድልድይምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ዘገባና ትንታኔ

ዘገባና ትንታኔ

70 Jahre Kriegsende