1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሁለቱ ሱዳኖች ሱዳን ግጭት

ሐሙስ፣ ግንቦት 2 2004

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ግጭትና ርስ በርስ መወነጃጀልን አቁመው ድርድር እንዲጀምሩ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በቅርቡ ውሳኔ አሳልፏል። 2 ቱ ሐገራት ለዚህ ውሳኔ ተገዥ መሆናቸውን ባሳወቁ በጥቂት ቀናት ውስጥ ትናንት ሱዳን

https://p.dw.com/p/14sx9
ምስል picture-alliance /dpa

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ግጭትና ርስ በርስ መወነጃጀልን አቁመው ድርድር እንዲጀምሩ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በቅርቡ ውሳኔ አሳልፏል። 2 ቱ ሐገራት ለዚህ ውሳኔ ተገዥ መሆናቸውን ባሳወቁ በጥቂት ቀናት ውስጥ ትናንት ሱዳን በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ ከአየርና ክምድር ድብደባ አካሂዳለች። ሁለቱ ሐገራት ድርድር እንዲጀምሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊያበቃ ሳምንት ሲቀረው በተፈፀመው በዚህ ጥቃት መዘዝና የአካባቢው ሐገራት ችግሩን በመፍታት ረገድ በሚኖራቸው ድርሻ ላይ ሂሩት መለሰ በእንግሊዘኛው ምህፃር ISS በመባል በሚጠራው ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አንድሪውስ አታ አሳሞዋን አነጋግራ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች።
ሱዳንና ደቡብ ሱዳን አለመግባባቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር እንዲፈቱ የሚጠይቀውን ባለፈው ሳምንት የተላለፍወን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔና የአፍሪቃ ህብረትን የሰላም እቅድ መቀበላቸውን ካሳወቁ ጥቂት ቀናት ናቸው የተቆጠሩት።

UN Sicherheitsrat zu Sudan und Iran
ምስል AP

የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔም ሁለቱ ሐገራት አማፅያንን ከመደገፍ እንዲቆጠቡ፣ ከሚያወዛግቡዋቸው አካባባዎች ወታደሮቻቸውን እንዲያስወጡ፣ የፊታችን ረቡዕ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ድርድር እንዲጀምሩ ይጠይቃል። ሆኖም በመካከሉ ትናንት ሱዳን በ 2ቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ጥቃት መፈጸሟ ተዘግቧል። ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው በእንግሊዘኛው ምህፃር ISS በመባል የሚጠራው ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ እርምጃውን አስገራሚ ብለውታል። ኦሳሞዋ እንደሚሉት ጥቃቱ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ የሚፃፀረር ነው።
«ሱዳን በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ና የአፍሪቃ ህብረት ያወጣውን የሰላም እቅድ ለማክበር ቃል ገብታ ደቡብ ሱዳንን ከደበደበች በጣም አስገራሚ ነው። ምክንያቱም በውሳኔው ሁለቱ ወገኖች ከያዟቸው ቦታዎች ለቀው እንዲወጡና በተለይ በግልፅ እንደተጠቀሰው የቦምብ ድበደባው እንዲቆም የሚጠይቀውን ቅድመ ሁኔታ በቀጥታ መጣስ ነው የሚሆነው ስለዚህ ይህ በእውነት በጣም አስገራሚ ነው የሚሆነው።»
ሁለቱ አገራት ድርድር ይጀምራሉ ተብሎ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት ይህን መሰሉ ጥቃት መድረሱ ብዙ ጥያቄዎችን ያስከትላል። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከአሁን በኋላ ምን ዓይነት እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል? የአፍሪቃ ህብረትስ ምን ያደርጋል የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች መሰንዘራቸው አይቀርም። አሳሞዋ እንደሚሉት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትም ሆነ የአፍሪቃ ህብረት ሁኔታዎቹን አጣርተው በውሳኔው እንደተቀመጠው ማዕቀብ በሚጥሉበት ሁኔታ ላይ በፍጥነት መነጋገራቸው አይቀርም። ያም ሆኖ የውሳኔው መጣስ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጥረት አለመስመር ተደርጎ ሊወሰድ ይችል ይሆናል። አሳሞዋ ግን ችግሩ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አይደለምና ተጠያቂነቱ ከሁለቱ ወገኖች አይወርድም ነው የሚሉት ።

«ማንም በዚህን መሰሉ ጥቃት ይሳተፍ፣ የወጣውን የሰላም እቅድ አላከበረም። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊሄድ የሚችልበት ደረጃ የተገደበ ነው። ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ የሰላም እቅዱንና ችግሩን ማስወገድ የሚችልባቸው መንገዶች ሊያቀርብ ይችላል። ሆኖም መወሰድ ያለበት ትክክለኛ መንገድ ግን ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሁለት ወገኖች ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ላይ ነው የሚወድቀው። በዚህ ረገድ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ መፍትሄ መፈለጉ አልተሳካለትም ማለት አልችልም፤ ሁኔታው እየተባባሰ ከሄደ ግን ሁለቱን ወገኖች ነው ተጠያቂ የማደርገው።»
ሱዳንና ደቡብ ሱዳን መቃቃራቸው ከሰፋና የአፍሪቃ ህብረትም ሽምግልና ከጀመረ በኋላ አንዳንድ የአካባቢው ሐገራት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየተጠየቀ ነው። ለምሳሌ ደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳ የበኩሏን ድርሻ እብድታበረክት በቅርቡ ጠይቃለች። ዩጋንዳ ደግሞ ኢትዮጵያና ኬንያን ከመሳሰሉ አስቀድሞ ለደቡብ ሱዳን ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ ሐገራት ይተባበሩኝ እያለች ነው። አሳሞዋ ግን በዚህ አይስማሙም፤
«እነዚህ ሐገራት በሙሉ የሚገኙበት የአፍሪቃ ህብረት በከፈተኛ ደረጃ ያዋቀረው፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን የሚሸመግል በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ታቦ ኢምቤኪ የሚመራው የሽምግልና ጥረት እንደቀጠለ ነው። ይህ እየተካሄደ የአካባቢው ሐገራት በሁለቱ ሱዳኖች ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራ ቢያደርጉ ተመሳሳዩን ሥራ መድገምና የአፍሪቃ ህብረትን ሙከራ አሳንሶ ማየት ነው የሚመስለኝ። እነዚህ ሐገራት የትኛውንም ሚና ይጫወቱ ምንም ዓይነት ድጋፍ ይኑራቸው የአፍሪቃ ህብረት የጀመረውን መንገድ በቅንነት ማየት ይገባቸዋል።»

Neues Hauptquartier der Afrikanischen Union AU in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/dpa


የአፍሪቃ ህብረት ጥረት ካልተሳካ ብቻ ነው እንደ አሳሞዋ የአካባቢው ሐገራት ለግጭቱ አማራጭ መፍትሄዎችን መፈለግ የሚገባቸው። ሰለዚህ ይላሉ ኡጋንዳ ኬንያና የኢጋድ አባል ሐገራት በሙሉ ለአፍሪቃ ህብረት ጥረት ድጋፍ መስጠት ነው የሚጠበቅባቸው። ሁለቱ ሱዳኖችም ቢሆኑ ሸምጋይ ፍለጋ መባዘን አይገባቸውም።
«ሌሎች ሸምጋዮችን ፍለጋ ወዲያና ወዲህ ማለት ለችግሩ የሚፈይደው ነገር የለም። አሁን በእጃችን ለያዝነው ጉዳይ ትኩረት እንስጥ፤ ይህ ሂደት ካልተሳካ ሌላ አማራጭ እንፈላጋለን። የተለያዩ ሸምጋዮች ተመሳሳይ ሂደት ውስጥ እንዲገቡ ከገፋፋን የአንዳቸውንም ተግባር ማስፈፀማችንን አጠራጣሪ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ በአዎንታዊነት አይሰራም።»

ሂሩት መለሰ

ሸዋዮ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ