1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ 200ኛ ዓመት፣

ረቡዕ፣ ጥቅምት 3 2003

በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ የሁምቦልትን ዩኒቨርስቲ 200ኛ ዓመት ክብረ-በዓል ፣ የአለክሳንደር ፎን ሁምቦልትን የጉዞ ምርምር፣ እንዲሁም ፣ የጀርመን መዲና በርሊን፣ ለምዕተ-ዓመታት የነበራትን የሳይንስ ምርምር ማእከልነት እንዳስሳለን።

https://p.dw.com/p/Pdan
የ 300 ዓመታት የሳይንስ ምርምር(በበርሊን የሚታይ ትርዒት)ምስል dapd

ጀርመን ውስጥ በመዲናይቱ በርሊን፣ ከዚህ ወር አንስቶ እስከ መጪው ታኅሳስ ወር ማለቂያ ገደማ ድረስ ፤ በ ማርቲን -ግሮፒየስ ህንጻ በሚገኘው ቤተ- መዘክር ፣ የጀርመንን የ 300 ዓመታት ሳይንሳዊ ምርምር ሂደት የሚያስቃኝ ፣ «የዓለም ዕውቀት » በሚል ርእስ የተሰናዳ ትርዒት ለህዝብ ይታያል። ትርዒቱ ፤ ይበልጥ የሚያተኩረው እጅግ በታወቁ ጀርመናውያን ተመራማሪዎች፣ ፈልሳፊዎችና የኖቤል ተሸላሚዎች ላይ ነው። ከአነዚህ መካከል፣ እጅግ ታዋቂው የዓእማቱ ሳይንቲስት ወይም የፊዚክሱ ሊቅ፣ አልበርት አይንሽታይን፣ እ ጎ አ በ 1938 ዓ ም፣ ከ ሊዘ ማይትነር ጋር የአቶምን ቅንጣት ለመክፈል የበቁት ሳይንቲስት ኦቶ ሃን፣ የሥነ-ቅመማ ው ታዋቂ ሮበርት ኮህም ሆኑ፣ ያኮብና ቪልሄልም ግሪም የተባሉት ወንድማማች የቋንቋ ምሁራንና ታዋቂ የተረት ተረት ጸሀፍት ይገኙበታል። ለአሁኑ ዘመን የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ግሥጋሤ፣ የቀድሞው የሳይንስ ምርምር መሠረት መሆኑንም ነው «የዓለም ዕውቀት »የተሰኘው ትርዒት ለማሳየት የሚሞክረው። ፣ትርዒቱ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የበርሊኑ ሁምቦልት ዩኒቨርስቲ የተመሠረተበትን 200ኛ ዓመት ካለፈው እሁድ አንስቶ በማክበር ላይ እንዳለ ነው። በዓለማችን ዕውቀትን በማካበት ረገድ ፣ በርሊን የቱን ያህል ድርሻ አበርክታለች? እ ጎ አ ጥቅምት 10 ቀን 1810 ዓ ም፣ የተመሠረተው የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት Christoph Markschies

«በሂሳብ የመሪነቱን ቦታ ከያዙት መካከል ነን። የጥንት የሥልጣኔ ቅርሳ-ቅርሶችን በመራመር ረገድ፣ በማኅበራዊ ሳይንስና በትምህርት ምርምርም ፣ በዓለም ውስጥ የመሪነቱን ሥፍራ ከያዙት ተቋማት መካከል እንደመራለን። ባልታወቅንባቸው የምርምር ዘርፎችም ማለፊያ ስም ለማትረፍ ጥረት እናደርጋለን።»

ቀድሞ በፕረሻውያን የሁምቦልት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም፤ ይባል የነበረው፣ በእውቁ ዘርፈ ብዙ ተመራማሪ አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት ታላቅ ወንድም ፣ ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት አነሳሺነት የተመሠረተው የከፍተኛ ትምህርት ማእከል ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ በ 4ኛው ዓመት (እ ጎ አ 1949) ወዲህ ሁምቦልት ዩኒቨርስቲ የሚል ሥያሜ አግኝቷል። የቪልሄልም ፎን ሁምቦልት የ 2 ዓመታ ታናሽ ወንድም አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት እ ጎ አ በሰኔ ወር 1799 ዓ ም፣ ወደ ደቡብ አሜሪካ በመጓዝ፣ በብዙ አገሮች በመዘዋወር፣ በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች፣ በፊዚክስ፣ ሥነ ቅመማ፣ ሥነ-ምድር፣ ማዕድናት፣ እሳተ ገሞራ፣ ሥነ-ህይወት ፣ ሥነ ዐራዊት፣ የወቅያኖስና የየብስ የአየር ንብረት፣ እንዲሁም ሥነ ፈለክ ጥናት ማድረጉ ይታወቃል። ደበብ አሜሪካን በሳይንሳዊ ምርምር የቃኘው ሁምቦልት ሁለተኛው ኮሎምበስ የሚል ተቀጥላ ስም ለማግኘትም የበቃ ነበረ። ከፈረንሳዊው ሀኪምና የሥነ ዕጽዋት ተመራማሪ ከነበረው ፈረንሳዊው ባልደረባው Aime Bonpland ጋር የአማዞንን ጥቅጥቅ ደን፤ የኤንደስን ምጡቅ ተራሮች፣ ዕጽዋትና የአየር ጠባይ አጥንተዋል። በፔሩና ኤኳዋዶር በኮል ሜክሲኮን አስሰው ዩናይትድ እስቴትስን ጎብኝተው በዚያ ዘመን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን ጋር ተገናኝተው እ ጎ አ በ1804 ዓ ም ነበረ ቦርዶ ፈረንሳይ የገቡት ። አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት፣ ወደ በርሊን ተመልሶ ወንድሙ ባቋቋመው ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሆኖ ከመሥራቱ በፊት ፈረንሳይ ውስጥ ከምርምር ጋር በተያያዘው ሥራው 20 ዓመት ተቀምጧል። እ ጎ አ በ 1829 ፣ ከሩሲያው ንጉስ «ዛር» ቀዳማዊ ኒኮውስ በቀረበለት ግብዣ መሠረትም ከዑራል ተራሮች ባሻገር ሳይቤሪያን በማሰስ የሥነ-ምድር፣ የማዕድንና የስነ-ህይወት ምርምር አካሂዷል። ከዚያም ተመልሶ በበርሊን የምርምር ሥራዎቹን ያዘጋጀ ሲሆን ፤ ከ 1845-1862 ዓ ም፣ ሳይንሳዊ ሥራዎቹን በ 5 ጥራዞች አሳትሞ አቅርቧል። ወደ 90 ዓመት ገደማ እንደተጠጋ እ ጎ አ ግንቦት 6 ቀን 1859 ዓ ም ያረፈው አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት፣ እርሱ ባካሄደው ሰፊ ምርምር፣ ወንድሙም ባቋቋመው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ፣ ሁምቦልት ዩኒቨርስቲ በቀጥታ እነርሱን አስታዋሽ ነው ማለት ይቻላል።

በ1810 ዓ ም፣ በፕረሻው ንጉሥ ሳልሣዊ ፍሪድሪኽ ቪልሄልም ዘመን የሁምቦልት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲከፈት፣ ንጉሡ፤ በቀጥታ ለተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚበጅ ትምህርት የሚሰጥበት ፣ ከፍተኛ ተቋም እንዲመሠረት ሲሹ፣ ፎን ሁምቦልት፣ ነጻና የተሟላ ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም እንዲገነባ ነበረ አልመው የተነሱት። አዲሱ ዩኒቨርስቲ የሆነው ሆኖ፣ በአገሪቱ የታወቁ ምሁራንን እያማለለ ወደ በርሊን እንዲጓዙ አደረገ። እናም፣ ፈላስፋው Johann Gottlieb Fichte የአዲሱ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኑ። የሥነ-መለኮት ምሁሩ Fridrich Schleiermacher እና ፈላስፋው Georg Friedrich Hegel ጠቃሚ ትምህርት በሚያካፍሉባቸው ቦታዎች የሰበሰቡ የነበሩ ተማሪዎች የፖለቲካ ልሂቃንን ቡድን መፍጠር ቻሉ። ስለ ፍጥረተ ዓለም (ኮስሞስ) የቪልሄልም ወንድም አሌክሳንደር ሁምቦልት ይሰጠው የነበረው ትምህርትም በ 1827 ዓ ም፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ረገድ አዲስ ደረጃ ማስገኘት ቻለ። በኋላም፣ ከ Göttingen ወደ በርሊን ሁምቦልት ተቋም የተዛወሩት ወንድማማቹ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን ያኮብና ቪልሄልም ግሪም፣ አዲስ አመርቂ ሥራ ለማከናወን ችለዋል።

እ ጎ አ በ 1900 የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ፣ ዝነኛ መምህራንን ፣ ለኖቤል ሽልማት የታጩና ያገኙትንም አሳባስቦ ነበር። እዚህም ላይ የጥንት ታሪክ ተመራማሪ የነበሩትን ቴዎዶር ሞምሰንን ወይም የፊዚክሱን ሊቅ አልበርት አይንሽታይንን መጥቀስ ይቻላል።

እ ጎ አ በ 1848 ዓ ም፤ ተጀምሮ የተደናቀፈውን አብዮት ተማሪዎችና ፕሮፌሰሮች ደግፈውት አንደነበረ የሚታበል አይደለም። በዩኒቨርስቲና በመንግሥት መካከል በተለዋወጡ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውጥረቶች የተወገዱበት ሁኔታ አልነበረም። የናዚዎች ፍልስፍና በኋላም የሶሺያሊስቷ ምሥራቅ ጀርመን ፖለቲካ ለአንዳንድ ፕሮፌሰሮች አይዋጥላቸውም ነበረ።

የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ የተቋቋመበት 200ኛ ዓመት እየታሰበ ባለበት ወቅት የተከፈተው« የዓለም ዕውቀት» የተሰኘው ትርዒትም ይህን አልደበቀም። ጠንቀኛውን ጋዝ ፣ በጀርመንኛ «አሞኒያክሲንተዘ» የተባለውን የናይትሮጂንና ሃይድሮጂን ጋዝ ድብልቅ የፈለሰፉትና የኖቤል ሽልማት ያገኙት Fritz Haber አልተረሱም። በአንደኛው የዓለም ጦርነት፣ በዚሁ ጋዝ ሳቢያ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው ፣ ለመከላከያ በተሠሩ እርዶች ውስጥ የተረፈረፉት። የናዚዎች ዘረኛ ርእዮት፣ ሰዎች እንዳይወልዱ የሚያደርግ አምካኝ መርፌ እንዲወጉ የተደረገበት ተግባር፣ የታወቁ አይሁድ ምሁራን የተባረሩበትና በርሊን በዚህ እርምጃው እንደተባለው «የዕውቀት መዲና » ያሰኛትን ዝናም ሆነ ማዕረግ ያጣችበትን ትርዒቱ እንደሚያሳይ ነው የተገለጠው። አሁንም የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ክሪስቶፍ ማርክሺስ ---

«ከዚህ የታሪክ ህመም ማገገም አይቻልም ፤ ዘግናኝ ነበረና! አሁን ቀስ-በቀስ ፣ ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሚያስገኝ፣ ድሮ እንደነበርነው የሳይንስ መዲና ለመሆን በመሥራት ላይ ነን። ነገር ግን ያ ያለፈውን ዘግናኝ የታሪክ ምዕራፍ ሊረሣ የሚችል አይደለም።»

በአሁኑ ጊዜ፣ 34,000 ተማሪዎች የሚገኙበት የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ፤ በምዕራብ በርሊን እ ጎ አ በ 1948 ዓ ም ከተቋቋመው (Freie Universität = ነጻ ዩኒቨርስቲ )ቀጥሎ በትልቅነት ሁለተኛ ነው።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ