1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ መስከረም 15 2010

«ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ» ግንባታ በሰዎችም ላይ ይሁን በተፈጥሮ ላይ ሊያመጣ የሚችለዉን ጉዳት ለማጥናት ከሶስቱም አገሮች፣  ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን አንድ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። ቢ.አር.ኤል እና አርቴሊያ የተባሉ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ግድቡ ሊያደርስ ይችል ይሆናል የሚባለውን ጉዳት የማጣራት ስራ ተሰጥቷቸዋል። 

https://p.dw.com/p/2kg8T
Sudan Khartum Abkommen gemeinsame Nil-Wasser Nutzung
ምስል AP Photo/Mohammed Abd el-Moaty, Egyptian Presidency

የቴክኒካዊው ጥናት መዘግየት

በፈረንሳይ መቀመጫቸዉን ያደረጉት ቢአርኤል እና አርቴሊያ የተሰኙት ሁለት ኩባንያዎች የኢትዮጵያ «ታላቁ ህዳሴ ግድብ» ወደ ግብጽና ሱዳን የሚፈሰው የዉሃ መጠን እና በተፈጥሮ ላይ ሊኖረዉ የሚችለዉን ተፅዕኖ ለማጥናት የተዋዋሉት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር። በዚያን ጊዜ ጥናቱን ለማጠናቀቅ 11 ወራት እንደሚወስድም የቢአር ኤል የበላይ ሐላፊ ጊለስ ሮኩሊያን ጠቅሰው ነበር።

የግብፅ የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሳሜህ ሹክር ባለፈዉ ሳምንት ከኢትዮጵያ አቻቸዉ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በኒዉዮርክ በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ጎን በተገናኙበት ጊዜ በግድቡ ላይ የሚደረገዉ ጥናት ሂደት ዘገምተኛነት እንዳሳሰባቸዉ ገልጸው፣ ጥናቱን እንዲከታተል የተቋቋመዉ የሶስትዮሹ የብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ እንቅስቃሴ እንደተጠበቀው አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

ኩባንያዎቹ ከጥቂት ጊዜ በፊት የመጀመሪያውን የጥናቱን ዘገባ ለሶስትዬዎሹ የብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዳሰረከቡና በዚሁ ላይ ከሶስት በላይ ዉይይቶች እንደተደረጉ የግብፅ ዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃላቀባይ አህመድ አቡዘይድ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ይሁን እንጅ ምንም እንኳን ግብፅ ከአራት ወር በፊት ለኮሚቴዉ በቀረበዉ ዘገባ ላይ ብትስማማም፣  ከሌሎቹ አገሮች ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አልመቻሏን ቃል አቀባዩ አህመድ ተናግረዋል። ምክንያቱንም ሲያብራሩ፣

«እንደምታዉቀዉ የቴክኒክ ኮሚቴዉ ኩባንያዎቹ የሚወስዱትን  እያንዳንዱን ርምጃ እና ዉሳኔ ማፅደቅ አለበት። ባሁኑ ሰዓት ኩባንያዎቹ ባቀረቡት የጥናቱ የመጀመርያ ዘገባ ላይ ኮሚቴዉ ከሶስት ዙር በላይ ዉይይት አድርጎበታል። ይሁን እንጅ ኮሚቴዎቹ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም። ለዛም ነበር እኛ ስምምነት ላይ መድረስ እንዲችሉ በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩ የሚንስቴሮች ስብሰባ የጠራነው። በኮሚቴዉ ዉስጥ የተወከሉት አገሮች በዉይይቱ ዙር አቋማቸዉን መቀየር አለፈለጉም። በኛ አስተያየት፣ ጊዜ እየባከነ ስለሆነ ጉዳዩ አሁን በሚንስትሮች ደረጃ መታየት አለበት።»

Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል picture-alliance/AA/Minasse Wondimu Hailu

ግብፅ የሚስቴሮቹ ስብሰበ በካይሮ ላይ እንዲደረግ ለኢትዮጵያና ለሱዳን ጥሪ አድርጋ መልስ በመጠባበቅ ላይ መሆኗን አህመድ ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል።

ጥናቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እየተካሄደ ነዉ የሚሉት የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለዉ ግንኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል  የዉጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹ እንደሚሰሩ በኒዉዮርክ ውይይታቸው ላይ ግልጽ ማድረጋቸውን  እና የግድቡን ጥናት በተመለከተ ሌላ የተነሳ ልዩ ሀሳብ አለመኖሩን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የግብፅን ስጋት እንደሚረዱት እና ኢትዮጵያ ሶስቱ አገሮች የተፈራረሙትን «Declaration of Princples»እንደምታከብር መግለጻቸው  የሚታወቅ ነው።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ በዶይቼ ቬሌ የፌስቡክ ድረ ገፅ ላይ ባካሄድነው ዉይይት ከተሳተፉት መካከል  አንዳንዶች ግድቡ በታችኛዉ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት ያደርሳል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ «የግድቡ ጥናት ዘገየም ፈጠነ ኢትዮጵያ እንደሆን ሥራዋን እየሰራች ነው፣»  በማለት አስተያየታቸዉን አጋርተውናል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ