1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህፃናት መብት 25ኛ ዓመት

ዓርብ፣ ኅዳር 12 2007

ለህጻናት ዓለማችን ከ25 ዓመት በፊት ከነበረው አሁን ይሻል ይሆን? ልክ ትናንት ከ25 ዓመት በፊት ነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህፃናት መብት ውል ያዘጋጀው። ባለፈው 25 ዓመታት የሆነውን አጠቃላይ ሂደት በአጭሩ በዛሬው የወጣቶች ዓለም እንቃኛለን።

https://p.dw.com/p/1DrDm
Symbolbild Sierra Leone Hunger
ምስል picture-alliance/dpa

እ.ኤ.አ. ኅዳር20 , 1989 ዓም ነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለህፃናት መብት ያሠናዳው ውል የፀደቀው። የጎርጎሮሲያዊው 2014 ዓ.ም. የህፃናት መብት ስኬት የታየበት ዓመት ሳይሆን አልቀረም። በዚህ ዓመት ሁለት የህፃናት መብት ተሟጋቾች የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ፓኪስታናዊቷ የ17 ዓመቷ ማላላ ዩሱፍዛይ ፤ ልጃ ገረዶች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ብዙ ታግላለች። ሌላኛው ካይላይ ሳትያርቲ ናቸው። የ60 ዓመቱ ህንዳዊ የልጆች የጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም ብዙ ታግለዋል። ማላላ ከኖብል ተሸላሚዎቹ በእድሜ ትንሽ መሆኗ ብቻ ሳይሆን ገና እጅግ ወጣትም ናት።

በ1980ዎቹ መጀመሪያ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሕጻናት መብት ስምምነት አስተባባሪ የነበሩት ኒጅል ካንትዌል« በህፃናት ላይ ያለው አመለካከት ፣ የበፊቱን ምስል ቀይሯል። ህፃናት ድጋፍ የሚሹ ሰዎች ብቻ አይደሉም። »ይልቁንስ ይላሉ ካንትዌይ፤« እነዚህ ህፃናት የራሳቸው ሌላ ገፅታ እንደፈጠሩ ነው የሚታየው። እና ለህፃናት መብት በሚያሳዩት ተሳትፎ ከልብ ሊደመጡ እንደሚገባ ያሳያል።»

ህፃናት የወላጆች መገልገያ እቃ ወይም ሀብት ብቻ እንዳልሆኑ እና የራሳቸው መብት እንዳላቸው አሁን ድረስ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ግልፅ አይደለም። ይህ አመለካከት የሚያሳየው የህፃናት መብት ውሉ ምን ያህል ወሳኝ እንደነበር ነው ይላሉ ኒጅል ካንትዌል« በተግባር ላይ የዋለውን የሰብዓዊ መብት ውል በሥራ ላይ ያዋሉ ወይም ያፀደቁት ፤ በፍፁም ይህንን በህፃናት ላይም እንጠቀም ብለው ሐሳብ ላይ አይመጡም ። መቼም ይሄን ያህል የሚል ወደ ታች የእድሜ ገደብ የለም። ስለልጆቹ ያሰበ የለም ። የመብቱ ውል የህፃናትን መብት ከቶውኑ አላጤነበትም ነበር። ይህ ነበር ከዚህ ቀደም በህፃናት ላይ የነበረው አመለካከት። የመብታቸውን ጉዳይ በተመለከተ እንዳልተፈጠሩ ነው የተቆጠሩት።»

Friedensnobelpreis 2014 Malala Yousafzai, Kailash Satyarthi
ማላላ ዩሱፍዛይ እና ካይላይ ሳትያርቲምስል Reuters

በውሉ የተስማሙት ሀገራት በ54 አንቀጽ ያሠፈሩት፤ ጭቆናን፣ ብዝበዛን፣ በአካል እና የወሲብ ጉዳይ የመሣሰሉትን ይመለከታል። ይኸው ውል በግልፅ እያንዳንዱ ህፃን ነፃ የሆነ ህይወት ከማግኘት በተጨማሪ ትምህርት ቤት የመሄድ መብት እንዳለው አስቀምጧል። ከዚህም በተጨማሪ ሐሳባቸውን በነፃ የመግለፅ እና የመደመጥ መብት አላቸው። የህፃናት ደህንነት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ይህ ውል ከፀደቀ ከ25 ዓመታት በኋላ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት በምህፃሩ UNICEF በነዚህ ዓመታት ውስጥ ምን አይነት ለውጦች ታዩ የሚል ጥያቄ አንስቷል። በርግጥ ዓለማችን ከ25 ዓመት በፊት ከነበረው አሁን ለህፃናት የተሻለ ሆኗል? መልሱ ፤ አዎ ብቻ ሳይሆን ግን፤ የሚልም ያስከትላል።« አንዳንድ ትልቅ ማሻሻል የተደረጉባቸው አካባቢዎች አሉ። በጤና፣ በልጅ አስተዳደግ፣ በመሳሰሉት አካባቢዎች ለውጡ የሚታይ ነው። ምንም እንኳን በትምህርቱ ረገድ ብዙም ጥሩ ርምጃ ባይታይ።»

ይላሉ ኒኮሌት ሙዲ ጄኔቫ ከሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት።እንደ UNICEF አንድ በ2014 ዓ.ም. የተወለደ ህፃን፣ ከ 25 ዓመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር፣ አምስተኛ አመቱን የማክበር እድሉ ከፍተኛ ነው ። በተሻሻለ መድሐኒት እና ክትባት አማካይነት ካለፉት 24 ዓመታት ጀምሮ የህፃናት ሞት በግማሽ መቀነሱ ይነገራል። ይህ ማለት ግን በአንፃሩ በዓለም ዙሪያ በየቀኑ 17 000 ህፃናት ፣ አብዛኞቹ በበሽታ እንደሚሞቱ ነው።

Deutschland UN UNICEF Kinderrechte sind Menschenrechte Kinderrechtskonvention
ለህፃናት መብት የሚታገሉ ወጣቶች በጀርመንምስል picture-alliance/ dpa

ለህፃናት ሞት ዋንኛ መንስዔ ሆነው የሚጠቀሱት ድህነት፣ የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት የመሣሰሉት እንደሆኑ UNICEF ይገልፃል። እንደ ድርጅቱም ይህንን ድህነት መዋጋት ትልቁ ኃላፊነት ነው። ቢሆንም በዚህም ረገድ መሻሻል እንደታየ ድርጅቱ ይናገራል። በማደግ ላይ ባሉት ሀገራት እጅግ በድህነት ሥር የሚኖረው ሰው ቁጥር በግማሽ መቀነሱ ይነገራል። እ.ኤ.አ. በ1990 ከሁለት አንዱ ሰው በአዳጊ ሀገራት እጅግ በከፋ ድህነት ስር ሲኖር እ.ኤ.አ. በ2010 ዓ.ም. አንድ አምስተኛው ሰው ብቻ መሆኑ ተገልጿል። ከነዚህም ውስጥ የህፃናቱ ቁጥር እንደሚበልጥ ኒኮሌት ሙዲ ያምናሉ።« እዚህጋ ከገቢ፣ ከጎሳ፣ ከአካል ጉዳተኛ መሆን ወይም አለመሆን አንፃር ትልቅ ለውጥ እናያለን፣ እና ደግሞ ሌሎች አካባቢዎች አሉ ለውጡ በቀስታ የሚታይባቸው።እነዚህም መከላከል ረገዱ ላይ ነው፤ በልጆች ላይ የሚደርስ የኃይል ርምጃ፣ ጉልበት ብዝበዛ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ የመሳሰሉ። በነዚህ አካባቢዎች ቀስ ብሎ ነው ለውጥ የሚካሄደው። ለጉልበት ብዝበዛው ክትባት ተሰቶ የሚያበቃ ነገር አይደለም። ርምጃዎቹን በዚህ ረገድ ተግባራዊ ለማድረግ ትንሽ ከባድ ነው »

የህፃናት መብቱ ውል እንደ ምሁሮቹ ከሆነ የዓለም አቀፍ የህፃናት ደንቦች እንዲሻሻሉ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት የዓእማቱ (ሚሊኒየም) የልማት ግብ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ይታመናል። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እ.ኤ.አ. በ2000 ዓ.ም. እስከ2015 ዓ.ም. ድህነትን ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የምግብ እጥረትን ለማጥፋት ትልቅ እቅድ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።«በቀላሉ ሊሳኩ የሚችሉትን እቅዶች በስራ ተግብረናቸዋል። መተግበር ያልቻልነው ድሆች እና የተገለሉት ጋር መድረስ ነው። ይሄንኑ ነው የህፃናት መብት ውሉ ከዚህ የሚሊኒየም የልማት ጎል በኋላ ወዴት እንደሚቀጥል አቅጣጫ የሚያሳየን። እስካሁን ልንደርስላቸው ያልቻልነውን በፍጥነት መርዳት ይኖርብናል።»

የህፃናት መብት ውሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካፀደቃቸው ፈጣን ውሎች አንዱ ነው። የትኛውም የዓለማችን ሀገራት ወዲያው ነው የተቀበሉት። እ.ኤ.አ. በ1990 ዓ.ም. በስራ ላይ የዋለውን ውል በአሁኑ ወቅት 194 ሀገራት ተቀብለውታል። ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ብቻ ናቸው ያላፀደቁት። ኢትዮጵያ ይህንን ውል ከመጀመሪያ አንስቶ ያፀደቀች ሀገር ናት። ሳሻ ዌስተርቢክ የUNICEF የኢትዮጵያ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ኢትዮጵያ ውስጥ በህፃናት መብት ረገድ ባለፉት 25 ዓመታት የተከናወነውን እንደሚከተለው ገምግመውታል። «ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ቁልፍ ከሚባሉ ግቦች መካከል ብዙዎቹን በማሳካት ከፍተኛ ለውጥ አስመዝግባለች። ለምሳሌ ያህል በ1990 ከአንድ ሺ 204 ያህሉ ይሞቱ ነበር። በ2012 ይህን በሁለት ሶስተኛ በመቀነስ ወደ 68 ዝቅ ማድረግ ችላለች። ይህም ኢትዮጵያ ከምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች መካከል በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የህጻናት ሞት ከሶስት አመት በፊት ማሳካት ችላለች። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በትምህርት በኩል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ቁጥር በ1990 ከነበረበት32 በመቶ ወደ መቶ በመቶ አካባቢ ከፍ አድጓል።64 በመቶ ኢትዮጵያውያንም የንጹህ ውሃ አቅርቦት አላቸው።''

Bildergalerie Kinderarmut Bangladesch Armut Weltkindertag
የህፃናት የጉልበት ስራ በባንግላጂሽምስል Mustafiz Mamun

በኢትዮጵያ የታዩት ስኬቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል የሚሉት ሳሻ ዌስተርቢክ የUNICEF የኢትዮጵያ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ቢሆንም የህጻናትን ደህንነት ለማረጋገጥ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን ያስረዳሉ። «በከተማና የከተማ አካባቢዎች የሚገኙ ድሆች ትኩረት የተነፈጋቸው በመሆኑ ትኩረት ያሻቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የንጽህና አጠባበቅ ሁኔታው በአዲስ አበባ ከ90 በመቶ በላይ ሲሆን በጋምቤላ ግን ወደ 30 በመቶ ያሽቆለቁላል። ሌላ ምሳሌ ብንመለከት በትግራይ፤አፋር እና አማራ ክልሎች ያለው የህጻናት እድገት ምጣኔ 50 በመቶ ሲሆን በአዲስ አበባ ግን ከ20 በመቶ በታች ነው። እና የእድገት አማላካቾቹ በአዲስ አበባ እና በክልሎች መካከል ሰፊ ልዩነት የሚታይበት ነው። ይህ እኛን እጅጉን ያሳስበናል። ምክንያቱን እያንዳንዱ ህጻን በየትም ቢኖር እኩል እና ፍትሃዊ እድል እንዲኖራቸው ህይወታቸውም የተስተካከለ እንዲሆን እንፈልጋለን።»

Integration von Behinderten in Afrika Sport Deutsche Schule
አዲስ አበባ በጀርመን ትምህርት ቤትምስል DW/J. Jeffrey

በተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መብት መሰረት ገለልተኛ በሆነ የህፃናት መብት ኮሚቴ አማካይነት ሁሉም መንግሥታት፣ በየ 5 ዓመቱ በሀገራቸው ስለተገኘው መሻሻልም ሆነ ተግዳሮት መዘገብ ይጠበቅባቸዋል። ይኼው ኮሚቴ በዚሁ በመገባደድ ላይ ባለው የጎርጎሮሲያውያን 2014 ዓም መጀመሪያ ላይ የካቶሊካውያን ቄሶች ህፃናትን ይደፍራሉ ስለሚባለው ጉዳይ የቫቲካን ተወካዮች የመነጋገሪያ ርእስ አድርገውት ነበር። በተደጋጋሚ ልጆች መብታቸውን ተጠቅመው ስለደረሰባቸው በደል ይፋ ያደርጋሉ። የህፃናት መብት ውሉ አቅም ከፍተኛ ነው ይላሉ የህፃናት መብት ምሁር ኒጅል ካንትዌል

« በአግባቡ ሊገለገሉበት የሚገባ አንድ መሣሪያ ነው። አንድ መዶሻ ብቻውን ምሥማር መቶ አያውቅም። ይህ እንዲሆን መዶሻውን በእጅ መያዝ ያስፈልጋል። ውሉም ተመሳሳይ ነገር ነው። መውሰድንና እና መጠቀምን ይጠይቃል።

ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ