1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለንደኑ ጉባዔ ስምምነትና ገቢርነቱ

ረቡዕ፣ መጋቢት 30 2001

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉና በዕድገታቸው የተራመዱ ሃገራትን የጠቀለለው የቡድን-ሃያ ስብስብ መንግሥታት መሪዎች ባለፈው ሐሙስ ለንደን ላይ ያካሄዱት ጉባዔ ውጤት ከያቅጣጫው “ታሪካዊ” ግምት ተሰጥቶት ነው የሰነበተው።

https://p.dw.com/p/HSEc
የቡድን-ሃያ ጉባዔ
የቡድን-ሃያ ጉባዔምስል AP

የጉባዔው ተሳታፊዎች በዓለም የፊናንስ ገበዮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማስፈንና ስርዓቱንም አጠቃላይ በሆነ መልክ ለመለወጥ ተስማምተዋል። ዋሺንግተን ላይ ከአራት ወራት በፊት ተካሂዶ በነበረው የመጀመሪያ የፊናንስ ጉባዔ ተነድፎ የነበረውን የተግባር ዕቅድ አሁን ወደ ጭብጥ የዕርምጃ ሰነድነት ለመለወጥ፤ በሌላ አነጋገር ገቢር ወደማድረጉ ደረጃ ለመሸጋገር ተችሏል ነው የተባለው። ለመሆኑ የለንደኑ ስምምነት ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት የጊዜው የኤኮኖሚ ችግር በሚጠይቀው መጠን ለመቀየር በቂ ነወይ? የታዳጊ አገሮች፤ በተለይም የአፍሪቃ ተጠቃሚ የመሆን ዕድልስ እስከምን ነው?

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የታዳጊውን ዓለም ያህል ክፉኛ የጎዳው የለም። እያደር መታየት የያዘው ሃቅ ይህ ሲሆን የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲቲት ሃላፊ ፕሮፌሰር/ዶር/ዲርክ ሜስነር ትናንት በዶቼ ቬለ ራዲዮ ጣቢያ ተገኝተው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በታዳጊው ዓለም በቀውሱ ተጽዕኖ ሳቢያ የድሃ-ድሃው ሕዝብ ቁጥር በሰፊው እየጨመረ ነው።

“በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ በዚህ ዓመት ከ 53 እስከ 100 ሚሊዮን ተጨማሪ ሕዝብ የድሃ-ድሃ ይሆናል። የድሃ-ድሃ የሚባሉት በቀን ከአንዲት ዶላር ተኩል ባነሰች ገቢ መኖር ያለባቸው ናቸው። እነዚሁ ባለፈው ዓመት በምግብ ዋጋ መናር ወደ ከፋው ድህነት ከተንሸራተቱት 150 ሚሊዮን ሰዎች ተደምረው በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዓለም ኤኮኖሚ ችግር 250 ሚሊዮን ተጨማሪ የድሃ-ድሃ ሕዝብ ተፈጥሯል ማለት ነው”

የቡድን-ሃያ መንግሥታት ጉባዔ ዓላማ የወቅቱን መሰል ዓለምአቀፍ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ እንዳይደገም ለማድረግ የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ ነበር። በመሆኑም በለንደኑ ጉባዔ ከብዙ በጥቂቱ በፊናንስ ገበዮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማስፈንና ስርዓቱን በሰፊው ለመጠገን፤ እንዲሁም የዓለም ንግድን ለማረጋጋትና ቀውሱ ክፉኛ ለመታቸው ታዳጊ አገሮች አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል ዕርዳታ ለመስጠት ተስማምተዋል። ዓለምአቀፉ የፊናንስ ድርጅት IMF እና ሌሎች የገንዘብ ድርጅቶችም ቀውሱን ለመታገል እንዲችሉ ተጨማሪ በጀት ያገኛሉ ነው የተባለው። ይህ ሁሉ እርግጥ በወቅቱ ዓለምን ወጥሮ ከያዘው ጭብጥ ምላሽን የሚጠይቅ የኤኮኖሚ ክስረት አንጻር አስፈላጊ ዕርምጃ ነው።

ቡድን-ሃያ መንግሥታት ከዓለም ኤኮኖሚ ሃይል 80 በመቶውን የሚጠቀልሉ ናቸው። በመሆኑም በማቆልቆል ሂደት ላይ የሚገኘውን የዓለም ኤኮኖሚ መልሶ ለማቅናት ከነርሱ የተሻለ ሌላ አማራጭ አይኖርም። ይህም ሆኖ ግን የለንደኑ ጉባዔ ስምምነቶች ከዛሬ ወደነገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍሬ ሊሰጡ መቻላቸው ወይም በቅርቡ የረባ ለውጥ መታየቱ የሚያጠያይቅ ነው። ይህ ደግሞ ፋታ በማይሰጥ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን የታዳጊ አገሮች ሁኔታ ያከብደዋል። ፕሮፌሰር/ዶር/ዲርክ ሜስነር የፖለቲካ ቀውስ እንዳይከተል ነው ያስጠነቀቁት።

“አጠቃላዩን የፊናንስን ቀውስ ማሕበራዊ ተጽዕኖ ሲመለከቱት የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ወደ ድህነት ቀውስ እየተሻገረ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በታዳጊ አገሮች ተጨማሪ ድህነትን ይፈጥራል። በቀላሉ ወደ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊቀየርም የሚችል ነው። ደካማና ያልተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ያላቸው አገሮች ደግሞ ጥቂቶች አይደሉም። እንግዲህ የኤኮኖሚው ቀውስ በማሕበራዊና በድህነት ቀውስ በኩል የፖለቲካ ቀውስም ሊሆን ይችላል”

ወደ ለንደኑ ጉባዔ ውጤት መለስ እንበልና ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት ታላቅ የኤኮኖሚ ውድቀት ወዲህ ተመሳሳይ ባልታየለት ሁኔታ የተከሰተውን የፊናንስ ቀውስ ስርዓቱን ሥር ነቀል በሆነ መልክ ሳይለውጡ ጠጋግኖ በአጭር ጊዜ ለማረጋጋት መቻሉ ሊያምኑት ያዳግታል። ለመሆኑ የእስካሁኑ የፊናንስ ስርዓት እንዳለ ሊጠገን የሚችል ነወይ? ጉባዔው ይህን ጥያቄ ጨርሶ አላነሣውም።

በጉባዔው ላይ ዋናው የሁሉም መፍትሄ ሆኖ የታየው መነጋገሪያ ጉዳይ ገንዘብ ብቻ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ችግር የተጣባውን ኤኮኖሚና የዓለም ንግድን መልሶ ለማነቃቃት፤ የከሰሩ ባንኮችን በብድር ለመደገፍና ቀውሱ እየደቆሳቸው ያሉትን ታዳጊ አገሮች ለመርዳት፤ የሁሉም መፍትሄ ገንዘብ ላይ አተኩሯል። ከወቅቱ ችግር ለመላቀቅ እርግጥ ገንዘብ ለማስፈለጉ አንድና ሁለት የለውም። ይሁንና ባለፉት ዓመታት በዓለምአቀፉ የፊናንስ ድርጅቶችና በዓለም ንግድ ረገድ ሲነሱ የቆዩት የተሃድሶ ወሣኝ ጥያቄዎች ተገቢውን ትኩረት ያገኙ አይመስልም። ያለውን ስርዓት በገንዘብ በማጠናከር ብቻ በመወሰን ዘላቂ መፍትሄ ማግኘቱ የሚከብድ ነው የሚሆነው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አዲስ የዓለም ኤኮኖሚ ስርዓት ለማስፈን አሜሪካ ውስጥ የተፈጠሩት የብሬተን-ዉድስ ድርጅቶች የዓለም ባንክና የምንዛሪው ድርጅት IMF በታዳጊ አገሮች የበለጸጉት መንግሥታት ጥቅም ማስጠበቂያ ናቸው በመባል በየጊዜው ሲወቀሱ ነው የኖሩት። በዕውነትም በዓባል መንግሥታቱ መካከል የተጣጣመ ወይም ሚዛን የጠበቀ የድምጽ ድርሻ የለም። 185 ዓባል ሃገራትን በሚያቅፈው የዋሺንግተን የፊናንስ ድርጅት ውስጥ አሜሪካ ብቻዋን 17 ከመቶውን ድምጽ ስትይዝ ውሣኔን የመግታት አቅምም አላት።
ለግንዛቤ ያህል ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት የሚከታተለው ድርጅት መንግሥታት ከክስረት አደጋ ላይ ሲወድቁና የገንዘብ ችግር ሲገጥማቸው ብድር በመስጠት ይደግፋል። ድርጅቱ በወቅቱ የፊናንስ ቀውስ ለተጎዱ ለምሳሌ ሁንጋሪያን፣ ሊቱዋኒያንና ሩሜኒያን ለመሳሰሉ አገሮች በሚሊያርድ የሚቆጠር ብድር መስጠቱ የቅርብ ትውስት ነው። የዓለም ባንክም እንዲሁ ለታዳጊ አገሮች ታላቁ ገንዘብ አቅራቢ አካል ነው። መዋቅራዊ ልማትን፣ የግል ኤኮኖሚ ዘርፍ መስፋፋትን፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ፕሮዤዎችን ያራምዳል፤ ድህነትን በመታገሉ ረገድም ይረዳል። እርግጥ ከለንደኑ ጉባዔ ስምምነት ወዲህ በነዚህ የገንዘብ ድርጅቶች ውስጥ ሃብታም መንግሥታት ያላቸው ተጽዕኖ እየቀነሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል። አለበለዚያ ቻይናን የመሳሰሉትን በተፋጠነ ዕድገት የሚገሰግሱ አገሮች ያለዚህ ተሥፋ ለማግባባት ባልተቻለም ነበር።

ይሁንና ጥያቄው በ IMF ውስጥ ያለው የድምጽ ድርሻ መስተካከል በተጨባጭ መቼና በምን ፍጥነት ዕውን ሊሆን ይችላል ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ድርጅቱ አጠቃላይ መዋቅራዊ ለውጥም ያስፈልገዋል። በዚህ ላይ ቁርጥኛ ዕርምጃ እስካልተደገ ድረስ ለድርጅቱ ገንዘብ መጨመሩ ብቻውን ችግሩን ይፈታል ማለቱ የሚገድ ነው። የዓለም ንግድን ለማነቃቃት መታሰቡም በድሆችና ሃብታም አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስወገድ ጭብጥ ዕርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ችግሩ በገንዘብ ድጎማ ዘላቂ መፍትሄ ማገኘቱ ያጠያይቃል። የዓለም ንግድን ፍትሃዊ ለማድረግ ለዓመታት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ጨርሶ የተሰናከለው የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር መልሶ ሊንቀሳቀስ አልቻለም።
በተለይ ሃብታም አገሮች ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡትን ድጎማ በሚገባ ለመቁረጥና ለታዳጊ አገሮች ገበዮቻቸውን ለመክፈት በቂ ዕርምጃ አለመውሰዳቸው የድርድሩ መክሽፍ ዓቢይ መንስዔ እንደነበር ይታወቃል። የበለጸጉት መንግሥታት የእርሻ ድጎማ የታዳጊውን ዓለም ገበሬ ይበልጥ የፉክክር አቅም እያሳጣ የባሰ ድህነት ላይ የጣለ ጉዳይ ነው። ይሄው የዶሃ ድርድር ጉዳይ በለንደኑ ጉባዔ ላይ የተረሣ ነገር ሆኖ ነው ያለፈው። በዓለም የፊናንስ ስርዓት ላይ አጠቃላይ ለውጥ ለማስፈን ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተነግሯል። ይሁንና የታሰበው ዕርምጃ ሁሉ የነበረውን በአዲስ መልክ ከማቅረብ ሌላ በመሠረታዊ ለውጥ ላይ ያለመ አይመስልም።

የፊናንሱ ቀውስ ያስከተለውን መዘዝ ለመታገልና ኤኮኖሚን መልሶ ለማነቃቃት ቀደምቱ የበለጸጉ መንግሥታት እስካሁን ወደ አምሥት ቢሊዮን ዶላር ገደማ አፍሰዋል። ችግሩ ገና ብዙ ወጪን የሚጠይቅ መሆኑም ከወዲሁ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። በሌላ አነጋገር ሃብታሞቹ አገሮች ራሳቸው ብዙ ቀዳዳዎችን መድፈን ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንጻር የታዳጊ አገሮችን ችግር ለማቃለል በቢሊዮን የተገባው ቃል ራሱ ገቢር መሆኑ በመጠኑም ቢሆን እንዴት የሚያሰኝ ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ የተባለውን ሁሉ ገቢር ማድረግ ይቻላል ከተባለ ውጤቱን ለማየት ጊዜ መጠየቁም አይቀርም። ይህም በተለይ ለአፍሪቃ መጪዎቹን ዓመታት እጅግ ከባድ የሚያደርግ ነው የሚሆነው።

“በ OECD አገሮች፤ ማለት በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች የኤኮኖሚው ማቆልቆል እነዚሁ በ 2009 ዓ.ም. ሁለት በመቶ ያነሰ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት እንደሚኖራቸው ነው የሚገመተው። ይህም የዓለም ንግድን መዳከም ያስከትላል። ከበፊቱ ዓመታት አንጻር የሚያስገቡት ምርት ይቀንሣል ማለት ነው። በወቅቱ የሚገመተው የዓለም ንግድ ዘጠኝ በመቶ እንደሚያቆለቁል ነው። ይህ ከሆነ ታዳጊ አገሮች በውጭ ንግድ ዕድገታቸውን አረጋግተው መቀጠል አይቻላቸውም”

ዓለምአቀፉ የፊናንሱ ቀውስ በርከት ባሉ የአፍሪቃ አገሮች ባለፉት ዓመታት በተከታታይ የታየውን ዕድገት ሌሎች ምክንያቶችም ታክለውበት ከአሁኑ መልሶ እንዲቆረቁዝ አድርጎታል። የጥሬ ሃብት ዋጋ በዓለም ገበዮች ላይ መውደቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ሲቀንስ በሌላ በኩል የኑሮ ውድነት ድህነትን ይበልጥ እያስፋፋ ነው። የምንዛሪ ክምችታቸው ተሟጦ ለለየለት የክስረት አደጋ እስከመጋለጥ የደረሱ አንዳንድ አገሮችም ተማጽኖ እስከማሰማት መድረሳቸው አልቀረም። የተባበሩት መንግሥታት ድህነትን በግማሽ የመቀነስ የሚሌኒየም ግብ እያደር ይበልጥ የማይደረስበት እየሆነ ሲሄድ ነው የሚታየው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ