1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለንደን ኦሎምፒክ

ሰኞ፣ ሐምሌ 23 2004

ባለፈው አርብ ምሽት ለንደን ላይ በደመቀ ትርዒት የተከፈተው የኦሎምፒክ ጨዋታ 30ኛው ኦሊምፒያድ ዛሬ የውድድሩን ሶሥተኛ ቀን እያሳለፈ ነው።

https://p.dw.com/p/15gnQ
ምስል picture-alliance/empics

ባለፈው አርብ ምሽት ለንደን ላይ በደመቀ ትርዒት የተከፈተው የኦሎምፒክ ጨዋታ 30ኛው ኦሊምፒያድ ዛሬ የውድድሩን ሶሥተኛ ቀን እያሳለፈ ነው። በጨዋታው መክፈቻ ምሽት የ 204 ሃገራት አትሌቶች የኦሎምፒኩን ስታዲዮም በሰልፍ ሲያደምቁ በተለይም የኦሎምፒኩን እሣት የማቀጣጠሉ ስነ ስርዓት እጅግ ማራኪና አስደናቂም ነበር። በዚህ መልክ የደመቀውን የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ በይፋ የከፈቱትም ንግሥት ኤልሣቤጥ ዳግማዊት ነበሩ።

«ሰላሣኛው የዘመናችን ኦሊምፒያድ የሚከበርበትን የለንደን ጨዋታ በይፋ እከፍታለሁ»

የብሪታኒያ ርዕሰ-ከተማ የኦሎምፒኩን ጨዋታ የማስተናገድ ዕድል ሲገጥማት ከጎርጎሮሳውያኑ 1908 እና 1948 ዓመተ-ምሕረት በኋላ የአሁኑ ለሶሥተኛ ጊዜ ሲሆን የመክፈቻው ትርዒትና ትዕይንት ውበት ሲታሰብ በዕውነትም ይገባታል የሚያሰኝ ነው። ትርኢቱ የብሪታንያን አካላት የአየርላንድን፤ የስኮትላንድን የዌልስንና የእንግሊዝን የምዕተ-ዓመታት ሃቅ፤ ከዚያው የተነሳውን የኢንዱስትሪ ዓብዮት፤ ብሪታኒያ ከዚያን ወዲህ ያደረገችውን ማሕበራዊና ባሕላዊ ዕድገት በሕብረ-ቀለማት እንደ መስታወት ያሳየ ነበር።

Olympia 2012
ምስል dapd

ለንደን ግዙፍ ለሆነው ግንቢያና አጠቃላይ ዝግጅት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ 15 ቢሊዮን ኤውሮ ገደማ ስታወጣ እስከፊታችን ነሐሴ 6 ቀን የሚዘልቀው ውድድር በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃም እየተደረገ ነው። ከ 10 ሺህ የሚበልጡት አትሌቶችም በጥሩ መንፈስ በውድድሩ እየተሳተፉና ለመሳተፍ እየተዘጋጁ ናቸው።

በ 30ኛው ኦሊምፒያድ የመጀመሪያው ሰንበት አልፎ ዛሬ ውድድሩ ሶሥተኛ ቀኑን ለማገባደድ ሲቃረብ ዋና፣ ተኩስ፣ የቢስክሌት እሽቅድድም፣ ክብደት ማንሣት ወዘተ-ባመዘኑባቸው ሁለት ቀናት ቻይና ስድሥት ወርቅ፣ አራት ብር፣ ሁለት ናሃስ፤ በጠቅላላው 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በቀደምትነት ትመራለች። በሜዳሊያው ተዋረድ ላይ ሁለተኛዋ ሶሥት ወርቅ፤ አምሥት ብርና ሶሥት ናሃስ ያገኘችው አሜሪካ ስትሆን ኢጣሊያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ፈረንሣይ፣ ሰሜን ኮሪያና ካዛክስታን እያንዳንዳቸው ሁለት ወርቅ በማሸነፍ ተከታዮቹ ናቸው።

የቻይናን ስኬት በተመለከተ የአገሪቱ መገናኛ አውታር ዛሬ አትሌቶቹ በመጀመሪያው ሰንበት ያስመዘገቡትን ውጤት በማወደስ በሌላ በኩል ግን ቡድኑ ከአራት ዓመታት በፊት በቤይጂንጉ ኦሎምፒክ አግኝቶት ከነበረው 51 የወርቅ ሜዳሊያ መጠን ላይ መድረሱን አጠያያቂ አድርጓል። ሆኖም ቢቀር በአርባ ወርቅ ከታላላቆቹ ሃገራት አንዷ መሆን መቻሏን የሚጠራጠር የለም።

በአጠቃላይ ስለ ኦሎምፒኩ ጨዋታና በተለይም ስለ ኢትዮጵያ አትሌቶች ሁኔታ በወቅቱ ለንደን ውስጥ የምትገኘውን ዘጋቢያችንን ሃይማኖት ጥሩነህን ዛሬ በስልክ አነጋግረናል።

Uwe Seeler HSV 1963 Bundesliga
ምስል picture-alliance/dpa

ቡንደስሊጋ

የእግር ኳሱ ስፖርት መድረኩን በአብዛኛው ለለንደኑ ኦሎምፒክ ለቆ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የጀርመን ቡንደስሊጋ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ሰንበቱን አክብሯል። የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ታዋቂ የቀድሞ ተጫዋቾች በተገኙበት በዓሉን ያከበረው ባለፈው ቅዳሜ ነበር። በጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 28 ቀን,1962 ዓመተ-ምሕረት የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን ም/ቤት ልዑካን በዶርትሙንድ ከተማ የዌስትፋሊያ ወርቃማ አዳራሽ በመሰብሰብ 103 ለ 26 በሆነ ድምጽ ቡንደስሊጋ ሕያው እንዲሆን ያደርጋሉ።

የዛሬው የፌደሬሺኑ ፕሬዚደንት ቮልፍጋንግ ኒርስባህም ከመጀመሪዋ ደቂቃ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆኑ ዕርምጃው ለጀርመን እግር ኳስ ወሣኝ ዕርምጃ እንደነበር ነው መለስ ብለው የሚያስታውሱት።

«ውሣኔው ለጀርመን እግር ኳስ አንዱ ትልቅ ዕርምጃ ነበር። በጊዜው በአምሥት አካባቢዎች ተከፍሎ የነበረው የሊጋዎች አወቃቀር በፌደራል ደረጃ አንድ-ወጥ እንዲሆን ይደረጋል። ይህ ደግሞ በጀርመን የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ምዕራፍን የከፈተ ነበር»

የጀርመን ቡንደስሊጋ ዛሬ በዓለም ላይ ጠንካሮች ከሚባሉት ሊጋዎች አንዱ ሲሆን ከጅምሩ ማራኪ እንደሆነ ነው አምሥቱን አሠርተ-ዓመታት ያሳለፈው። በዓሉ በፊታችን ነሐሴ 18 ቀን አዲሱ የቡንደስሊጋ ውድድር ወቅት በዶርትሙንድና በብሬመን ጨዋታ ይታሰባል። ያጋጣሚ ሆኖ ያኔም የመጀመሪያው የቡንደስሊጋ ግጥሚያ የተካሄደው በዶርሙንድና በብሬመን መካከል ነበር።

Formel 1 Ungarn Sieger Lewis Hamilton
ምስል Reuters

ፎርሙላ-አንድ

በትናንትናው ዕለት ሁንጋሪያ-ቡዳፔስት ላይ ተካሂዶ የነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም በብሪታኒያው ዘዋሪ በሉዊስ ሃሚልተን አሸናፊነት ተፈጽሟል። በዚሁ እሽቅድድም የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛ የወጣው ደግሞ የፈረንሣዩ ዘዋሪ ሮሜይን ግሮስዣን ነበር። ጠንካሮቹ ዘዋሪዎች ዜባስቲያን ፌትል በአራተኝነት፤ ፌርናንዶ አሎንሶም በአምሥተኝነት ተወስነዋል።

ከመላው የውድድሩ ወቅት ሃያ እሽቅድድሞች 11ዱ ተጠናቀው ሳለ አሁን በአጠቃላይ ነጥብ 164 አስቆጥሮ የሚመራው የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ