1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለውጥ ተስፋ በታንዛንያ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 2 2008

አዲሱ የታንዛንያ ፕሬዚደንት ጆን ፖምፔ ማጉፉሊ የሃገራቸውን ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች ለማሻሻል እየወሰዱ ባሉት ርምጃ ብሩሁን ተስፋ በመፈንጠቅ በብዙ አፍሪቃውያን ዘንድ አዎንታዊ አመለካከት አተረፉ።

https://p.dw.com/p/1HLzx
Tansania Präsident John Magufuli
ምስል Getty Images/AFP/D. Hayduk

የለውጥ ተስፋ በታንዛንያ

በታንዛንያ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊው ጥቅምት 25፣ 2015 ከተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በኋላ በሃገሪቱ ታሪካዊ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ለውጥ ይኖራል የሚል ተስፋ ሚኖር መስሎ ነበር። ይሁንና፣ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ሃገር ነፃነቷን ከተጎነፀፈች ወዲህ ስልጣኑን የያዘው የገዢው የቻማ ቻ ማፒንዱዚ ፓርቲ እንደገና ማሸነፉ እና ዕጩው ጆን ፖምፔ ማጉፉሊ 58% የመራጩን ድምፅ በማግኘት የፕሬዚደንትነቱን ስልጣን መያዛቸው ይታወሳል። እርግጥ፣ የተጠበቀው ለውጥ ገሀድ ባይሆንም፣ በማጉፉሊ አመራር በሃገሪቱ አስገራሚ ሂደት መታየት ጀምሮዋል።

ፕሬዚደንት ማጉፉሊ ምክር ቤቱ፣ ሚንስቴሮች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ወኪሎች ወጪን ለመቀነስ የተለያዩ ርምጃዎችን አነቃቅተዋል። አዲሱ ፕሬዚደንት በመጀመሪያው የስልጣን ቀን ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ መገኘታቸውን ለማረጋገጥ ሳይታሰብ ወደ ገንዘብ ሚንስቴር ሄደዋል። በሶስተኛውም ቀን ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በስተቀር ሌሎቹ የመንግሥት ሰራተኞች ወደ ውጭ ሃገር እንዳይጓዙ ትዕዛዝ አስተላለፉ፣ ምክንያቱም፣ እንደ ማጉፉሊ ገለጻ፣ ለዚህ ዓይነቱ ጉዞ የሚወጣው ገንዘብ ለሌላ ለሕዝቡ ጥቅም የሚሰጥ ዘርፍ ላይ ሊውል ይችላል። ለምሳሌ ፣ በታንዛንያ ከጥር፣ ጎርጎርዮሳዊው 2016 ዓም በኋላ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ነፃ ለማድረግ ታስቦዋል። ማጉፉሊ በአራተኛው የስራ ቀን ሳይታሰብ ትልቁን የሃገሪቱን የመንግሥት ሀኪም ቤት ጎብኝተው ነበር፣ በዚያ ሕሙማን ወለል ላይ ተኝተው፣ የሕክምና መሳሪያዎች ተበላሽተው ባገኙበት ጊዜ የሀኪም ቤቱን ኃላፊ ከስራቸው አሰናብተው የሀኪም ቤቱን አስተዳደርም በትነዋል።

Tansania Wahlen CCM John Magufuli Anhänger
ምስል Reuters/S. Said

ታንዛንያ ባለፈው ረቡዕ ፣ ህዳር 29፣ 2015 54ኛውን የነፃነት በዓል አስባ ውላለች። ዕለቱ ግን እንደ ሌላው ጊዜ በደመቀ ስነ ስርዓት አልተከበረም። ምክንያቱም ፕሬዚደንት ጆን ፖምፔ ማጉፉሊ ማንኛውንም ክብረ በዓል በመሰረዝ፣ የታንዛንያ ዜጎች ዕለቱን መንገዶችን እና ግቢያቸውን በማፅዳት እንዲያሳልፉት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል። ማጉፉሊ የነፃነት ዕለትን የመሰለ በዓል ለማዘጋጀት የሚወስደውን ወጪ ገንዘብ ማባከን ነው በማለት መንግሥታቸው ገንዘቡን የኮሌራ በሽታን ለመታገል ለተጀመረው ጥረት እንደሚያውሉት ገልጸዋል። እንደተሰማው፣ የኮሌራ በሽታ በምዕራባዊ ታንዛንያ ባለፉት ወራት የብዙ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቶዋል። ፕሬዚደንቱ ከባለተቋማት እና ከነጋዴዎች ጋር ስብሰባ በማካሄድ፣ ግብር አለመክፈል እንደሚያስቀጣ አስታውቀው፣ ያለባቸውን እዳ እንዲያከፍሉ አሳስበዋል።

« ለዓመታት ለመንግሥት ግብር ያልከፈላችሁ ነጋዴዎች ይህንኑ እዳችሁን እንድትከፍሉ የሰባት ቀናት ጊዜ ሰጥቼአችኋላሁ። ይህን በማድረግ ሰላማችሁን ታገኛላችሁ። የሚያስፈልገን የሕዝብን መንግሥት የምናንቀሳቅስበት ገንዘብ ነው። ስለዚህ ይህን ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ሁሉ በሃገሪቱ ሕግ መሰረት ቅጣት ይጠብቃቸዋል። እኛ በንግዱ ማህበረሰብ አንፃር ትግል እያካሄድን አይደለም፣ የመንግሥትን ግብር እንዲከፍሉ ግን እንፈልጋለን። »

Tansania Wahlen John Magufuli
ምስል Reuters

በዚሁ የመንግሥታቸውን ወጪ ለመቀነስ በያዙት ፖሊሲ ከተቃዋሚ ቡድኖች ብርቱ ትችት የተፈራረቀበትን ገዢው የቻማ ማፒንዱዚ ፓርቲያቸውን ገፅታ ለማሻሻል አስበዋል።

ከጎርጎሪዮሳዊው 2000 ዓም ወዲህ የታንዛንያ ካቢኔ አባል፣ ብዙውን ጊዜም በስራ ሚንስትርነት ያገለገሉት ማጉፉሊ በዚሁ ኃላፊነታቸው በወሰዱዋቸው ቆራጥ ውሳኔዎች « ቡልዶዘር» የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው የሃገር አመራሩን ስልጣን ከተረከቡ አሁን አንድ ወር ከስድስት ቀን የሆናቸው ማጉፉሊ እስካሁን የመንግሥታቸውን ወጪ ለመቀነስ እና ሙስናን ለመታገል ያሳዩትን የስራ ሂደት ብዙ የታንዛንያ ዜጎች እና ሲቭሉ ማህበረሰብ ጥሩ ጅምር አድርገው ተመልክተውታል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቡድን ኃላፊ የሆኑት ሞዘስ አላን ርዕሰ ብሔሩ ለሕዝብ የቆሙ መሆናቸውን እንዳስመሰከሩ ገልጸዋል።

« ፕሬዚደንቱ የመንግሥቱን በጀት ወጪን ለመቀነሱ ተግባር ነው ትኩረታቸውን የሰጡት። በዚህ መንገድ ቀደም ባሉ ዓመታት ርምጃ ተወስዶ አያውቅም። ስለዚህ እኛ ታንዛንያውያን ፕሬዚደንት ማጉፉሊ ወጪን በመቀነሱ ረገድ ለሕዝብ የሚጠቅም አሰራር በመከተላቸው ኩራት ተሰምቶናል። ማጉፉሊ ቅድሚያ ሰጥተው እየተከተሉት ያለውን አሰራር ስንመለከት፣ በተቻለ መጠን የመንግሥታቸውን ወጪ ለማሰነስ እና ብክነት እንዳይኖር ለማድረግ፣ እንዲሁም፣ ለመንግሥት መግባት ያለበት ግብር በትክክል እንዲከፈል እና የሃገራችንን የተፈጥሮ ሀብት ተገቢ የሆነ በጀት በመመደብ መጠቀም የምንችልበትን አሰራር ማረጋገጥ ነው። »

የፖለቲካ ተንታኞች ፕሬዚደንት ማጉፉሊ የመንግሥቱን ወጪ ለመቀነስ የወሰዱዋቸውን ጠንካራ ርምጃዎች አዎንታዊ ሲሉ ቢያሞግሱም፣ ቀጣይነቱ አስተማማኝ መሆኑን የሚጠራጠሩ የታንዛንያ ዜጎች ጥቂቶች አለመሆናቸውን የ«ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ» የተባለው የመገናኛ ብዙኃን ቡድን ተንታኝ አዳም ኢሁቻ አመልክተዋል።

« ምናልባት እንደ ጋዜጠኞች አለፍ ብለን በመሄድ፣ ይህ እቅዳቸው እስከ መቼ ሊቀጥል እንደሚችል መጠየቅ ይገባናል ብየ አስባለሁ። ምክንያቱም፣ ለምሳሌ የነፃነት በዓላችንን አታክብሩ ማለት ትክክል አይደለም፣ እስከ መቼ? ርምጃዎቹ ሁሌ ይቀጥላሉ ብዬ አላስብም። ለአንድ ጊዜ መቀበል ይቻላል፣ ምክንያቱም፣ መንግሥት አንዳንድ በጣም አጣዳፊ ጉዳዮችን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማሰባሰብ አለበት። »

Karte Tansania und Sansibar Englisch
ምስል DW

የተቃዋሚ ቡድኖችም ጅምሩ ጥሩ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል። ይሁንና፣ ማጉፉሊ ውሳኔዎችን ምንም እንኳን ጥሩ ቢሆኑም፣ የሀገሪቱን ሕጎች ችላ በማለት ለብቻቸው ማንንም ሳያማክሩ በመውሰድ ላይ ናቸው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በምክር ቤት ከተወከሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የአንዱ ዋነኛ ፓርቲ እንደራሴ ዚቶ ካብዌ ፕሬዚደንቱ በሃገሪቱ ተጠያቂነትን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት ምክር ቤቱ መደገፍ እንዳለበት አስረድተዋል፣ ይህ ግን ህግን እና ደንብን የተከተለ መሆን እንደሚኖርበት አስታውቀዋል።

የማጉፉሊን ርምጃዎች ያሞገሱ የታንዛንያ ዜጎች ለአዲሱ ፕሬዚደንታቸው አድናቆትታቸውን እና እንደ ሃገሪቱ ዜጎችም የተሰማቸውን ኩራት በማህበራዊ መገናኛ መረቦች መግለጻቸውን ቀጥለዋል። የማጉፉሊ ርምጃዎች ግን በታንዛንያ ብቻ አይደለም ሞገስ ያገኙት፣ በጎረቤት ሃገራት ዜጎችም ዘንድ አድናቆትን አትርፈዋል። ለምሳሌ፣ አንዱ የኬንያ ተወላጅ እንዳለው፣ ብዙ ኬንያውያን ታንዛንያዊው ፕሬዚደንት ለመሪዎቻቸው አርአያ እንዲሆኑ ተስፋ አድርገዋል።

« የኬንያ ዜጎች ማጉፉሊ ጥሩ ርምጃዎች በመውሰድ ላይ ናቸው ብለው ያስባሉ። እና የኛ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታም እንደ ማጉፉሊ የመንግሥታቸውን ወጪ መቀነስ የሚያስችል ርምጃ በመውሰድ በሕዝባቸው ትከሻ ላይ ያረፈውን ሸክም ቢያቃልሉ መልካም ይሆናል። »

የታንዛንያ ፕሬዚደንት ካቢኔአቸውን ለማቋቋም ካሁን ቀደም ከነበሩት ፕሬዚደንቶች የበለጠ ጊዜ የወሰዱ ሲሆን፣ ማጉፉሊ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፉትን የቀድሞ የካቢኔ አባላትን እምብዛም የማይታወቁ የገዢው ፓርቲ ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ባለስልጣናት በመተካት ከእስካሁኑ የተለየ አመራር እንደሚከተሉ ጠቁመዋል። ይህን እቅዳቸው ተግባራዊ ማድረግ መቻል አለመቻላቸው ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ያሳያሉ።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ