1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለውጥ ዕድሎች ለምን ይከሽፋሉ? ከፈረሱ ጋሪው እየቀደመ

ዓርብ፣ ነሐሴ 17 2011

“የመጣበትን መመልከት ያልቻለ፥ የሚሔድበትን አያውቅም” እውነትም ግን ያለፉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ዕድሎች ስለምን ከሸፉ? በኢትዮጵያ የተከሰቱ የለውጥ ዕድሎች በሙሉ በልኂቃኑ ይሁንታ የመጡ እና የሔዱ በመሆናቸው ሕዝቡ የኹነቱን ጥቅምና ጉዳት ሳይረዳ፣ ወደ ተግባር ለመሔድ የሚደረገው ጥረት ደጋፊ በማጣት ለክሽፈት ይዳርጋል።

https://p.dw.com/p/3OMDD
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

የለውጥ ዕድሎች ለምን ይከሽፋሉ?

ትላንት በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለአፍሪካ አዳራሽ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ለውጥ ሒደት በተመለከተ ትልቅ ኮንፈረንስ ሲካሔድ ነበር፤ ኮንፈረንሱ ዛሬም ይቀጥላል። በኮንፈረንሱ ላይ ከቀረቡት የውይይት አጀንዳዎች መካከል ቀልቤን የሳበው “በኢትዮጵያ ታሪክ የተሳኩ እና የከሸፉ የለውጥ ሒደቶች” የሚለው ነበር። ውይይቱን የመሩት ገብሩ ታረቀ (ዶ/ር) የአንቶኒ ግራምሺን አባባል ተውሰው “የመጣበትን መመልከት ያልቻለ፥ የሚሔድበትን አያውቅም” በማለት ነበር ከታሪክ የመማርን አስፈላጊነትን ያስረዱት። እውነትም ግን ያለፉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ዕድሎች ስለምን ከሸፉ? ዛሬስ ካለፈው ምን መማር እንችላለን።

ከፈረሱ ጋሪው እየቀደመ

አንጄሎ ዴል ቦካ የተባሉ ጣልያናዊ በደረሱት “ላ ንጉሥ” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ የ1953ቱን የኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግሥት እንዲህ የሚያስታውሱት “ሕዝቡ በገለልተኝነት የተመለከተው” ክስተት እንደሆነ አድርገው ነው። ይህ ገጠመኝ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትዕይንት የሚገልጽ ነው። ብዙ ጊዜ ሕዝቡ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና መልሶች ተመልካች እንዲሆን ከመደረጉ በስተቀር የሚማከርበት ዕድል አያገኝም። ማርቲን ሉተር ኪንግን ጨምሮ ብዙ ስኬታማ የሲቨል ነጻነት ንቅናቄ መሪዎች እንደሚናገሩት የሁሉም ነገር መጀመሪያ ሕዝብን ማንቃት ነው። ሕዝብ ትግሉ ለምን እንደሆነ ማወቅ አለበት። በመቀጠል መደራጀት እና መተግበር ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ የተከሰቱ የለውጥ ዕድሎች በሙሉ በልኂቃኑ ይሁንታ የመጡ እና የሔዱ በመሆናቸው ሕዝቡ የኹነቱን ጥቅምና ጉዳት ሳይረዳ፣ ወደ ተግባር ለመሔድ የሚደረገው ጥረት ደጋፊ በማጣት ለክሽፈት ይዳርጋል።

የሕዝቦች ትግል እየተጠለፈ

በ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት የተጠናቀቀው በወታደራዊው መንግሥት ተጠልፎ ነው። ምንም እንኳን ዋናው የትግሉ መሪዎች እና የጥያቄዎቹ አቅራቢዎች የሠራተኛ ማኅበራት፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበራት እና የመሳሰሉት ቢሆኑም ደርግ በመጨረሻ ቤተ መንግሥት በመግባት እና የአብዮቱ ጠባቂ አድርጎ ራሱን በመሾም ከመሬት ላራሹ በቀር ሌሎች ጥያቄዎች ሊመለሱበት የሚችሉትን ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ሕልም አጨናግፏል። አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ለዓመታት በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ሲካሔድ የነበረውን ተቃውሞ የኦዴፓ እና አዴፓ ጥምረት እንደመሰላል ተንጠላጥሎበት የኢሕአዴግ አንድ ቡድን በአሸናፊነት እንዲወጣ እና በባለድልነት እንዲፎክር አድርጎታል። ይህም በተቃውሞ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በመጪው የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ዕድል እንኳን እንዳያገኙ አድርጓል።

አንድ ችግርና አንድ መፍትሔ እየተፈለገ

በ1966ቱ አብዮትም ይሁን በ1983ቱ የስርዓት ሽግግር ወቅት የታዩት ተመሳሳይ ክስተቶች ይኸው የኢትዮጵያን ችግር አንድ ብቻ፣ መፍትሔውም አንድ ብቻ አድርጎ ማየት ነው። የአብዮቱ መሪዎች ነን ያሉት ሰዎች የኢትዮጵያ ችግር የመደብ ጭቆና ነው በሚል የመሬት ላራሹን ጥያቄ ከመለሱ በኋላ ሌላውን ሁሉ አለባብሰው ለማለፍ ሞክረዋል። በ1983 ደግሞ የኢትዮጵያ ችግር የብሔር ጭቆና ነው በሚል አገሪቱን በብሔር ፌዴራሊዝም በማወቀር ምዕራፉ ተዘግቷል በማለት ለማለፍ ሞክረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር በአንዴ በርካታ ችግሮች፣ እና ለነዚህም መፍትሔ የሚሆኑ በርካታ አማራጮች የሚኖሯት አገር መሆኗን ዘንግተዋል። እየመጡ የሚሔዱት አገዛዞች ችግሮቹን ለዘለቄታው መፍታት የተቸገሩባቸውና ለውጦቹ የከሸፉበት አንዱ ምክንያት ይኸው አንድ ችግር ብቻ አለ የማለት አባዜ ነው።

ሥር ነቀል ለውጥ እየተመረጠ

ያለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያስተምረን የለውጥ ዕድሎች ከሚከሽፉባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው ቀስ በቀስ በመሻሻል እና የተገኘውን ድል ይዞ ለተጨማሪ በመታገል ፈንታ፥ ሁሉንም ነገር በአንዴ ለማግኘት በመሞከር አልያም የተገኘውን በመናድ የማፈራረስ ልምድ አንዱ ነው። በ1966ቱ አብዮት ወቅት ምንም እንኳን ግዙፍ ጭቆና የነበረበት የፊውዳል ስርዓት ቢገረሰስምና የገባሩ ስርዓት ቢቀርም፣ ዴሞክራሲያዊነትም፣ ሶሻሊዝሙም አሁኑኑ ካልሆነ የሚለው የልኂቃኑ ፍላጎት ግን የተገኘውን ድል እንኳን በቅጡ ሳያጣጥሙ የአንድ ትውልድ ልኂቃን በገፍ ለእልቂት እንዲዳረጉ አስገድዷል። በተመሳሳይ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በተለይ ተቃዋሚዎች ገዢው ቡድን ያመነላቸውን የፓርላማ መቀመጫ በመቀበል እና እየተደራደሩ በመቀጠል ፈንታ ሁሉንም ካላገኘን የትኛውም ይቅርብን የሚመስል ዓይነት ውሳኔ በመወሰናቸው እዚያ የታሪክ ነጥብ ላይ ለመድረስ የተሔደው መንገድ ሁሉ የባከነ ሆኖ እንዲያልፍ አድርጓል።

ልኂቃኑን ማሥማማት እየከበደ

በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የትላንቱ ውይይት ላይ ዲማ ነጎ የተባሉት ታዋቂ ፖለቲከኛ የኢትዮጵያ ልኂቃን መሐከል ያለው ክፍፍል ለታሪካዊ የለውጥ ዕድሎች መክሸፍ አንድ መንስዔ መሆኑን ይጠቅሳሉ። እውነትም፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልኂቃን በኢትዮጵያ ታሪክ አረዳዳቸው፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚበይኑበት መንገድ እና ኢትዮጵያ ወደ የት፣ በየት በኩል መሔድ አለባቸው የሚሉት ላይ በብዛት አይስማሙም። ይህም የለውጥ ዕድሎችን ለሁሉም በሚበጅ መልኩ እንዳይጠቀሙ አስገድዷቸዋል።

የውጭ ኀይሎች ጣልቃ እየገቡ

የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እና አምባሳደር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ ደግሞ በኢትዮጵያ ተከስተው ለነበሩ የለውጥ ዕድሎች መክሸፍ የውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት ቀላል እንዳልነበረ ይሥማማሉ። በርግጥም ከአቤቶ እያሱ በተፈሪ መኮንን መገልበጥ ጀምሮ በተከሰቱ የተሳኩ እና ያልተሳኩ የለውጥ አጋጣሚዎች ውስጥ ከእንግሊዝ እስከ አሜሪካ እስከ የተባበሩት ሶቪየት ኅብረት ያሉ አገራት ጣልቃ ገብነቶች ቀላል የማይባሉ ሚናዎችን ተጫውተዋል።

የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪዎች “ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ እንደማንማር ነው” በማለት ፖለቲከኞች የታሪክን ስህተት እንደሚደግሙ በስላቅ ይናገራሉ። አሁን ጥያቄው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መሪዎች እና ጠቅላላው የፖለቲካ ልኂቃን በኢትዮጵያ ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ እያየነው የነበረውን አዎንታዊ ለውጥ፥ ከታሪክ ተምረው ያስቀጥላሉ ወይስ ያለፈውን ታሪክ በመድገም ያከሽፉት ይሆን? የወደፊቱ ታሪክ ውጤቱን ይነግረናል።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የ ቼ ቬለ «DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

በፍቃዱ ኃይሉ