1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ዉጊያና ሥጋቱ

ሰኞ፣ መጋቢት 26 2003

የእርስ በርስ ጦርነት እና አለም አቀፍ ድብደባ የዛሬዋን ሊቢያ የትናንቷ ኢራቅ፥ የነገዉን የቃዛፊ ፍፃሜ ያለፈዉን የሳዳም አይነት እንዳደርገዉ ነዉ ሥጋቱ

https://p.dw.com/p/RFG2
አማፂዉ-ና የጠፋችዉ አጃቢያምስል AP

04 04 11

የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ የሐገሪቱን ገሚስ ግዛት ባፍታ የማዳረሱ ፍጥነት፣ የጦር መኮንን፣ ሚንስትር አገረ-ገዢዎችን የማሳዳሙ ፅናት አረብ ዓለምን-አጃቢ ጉድ አሰኝቶ ነበር።የኮለኔል ሙዓመር ቃዛፊን አገዛዝ የመጨረሻ-መጀመሪያን አርድቶ ወይም አብስሯልም።አብዮቱ ባፍታ የአርባ ሁለት ዘመኑን ሥርዓት ጥርስ-ጥፍርን የመመነጋገሉ ዉጤት ጉድ አሰኝቶ ሳያበቃ ሕዝባዊም፣ ሠላማዊነቱንም ማጣቱ ነዉ-የጉዱ ጉድ።የቃዛፊ አገዛዝ መፈፀሙ ዛሬም ቢሆን ብዙዎችን አላጠራጠረም።ሕዝባዊዉን አብዮት በቅፅበት ያዳፈነዉ የእርስ በርስ ጦርነት እና አለም አቀፍ ድብደባ የዛሬዋን ሊቢያ የትናንቷ ኢራቅ፥ የነገዉን የቃዛፊ ፍፃሜ ያለፈዉን የሳዳም አይነት እንዳደርገዉ ነዉ ሥጋቱ።የሥጋቱ ምክንያት፥ ምልክትና ፍንጩ ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

ፈረንሳይ፥ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግሥታት ዉሳኔን ለማስከበር ባሉት ዘመቻ የሊቢያ መንግሥትን ጦር መደብደብ ሲጀምሩ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ድብደባዉ አዉገዘዉ ብዙ ጮኸዉ ፎክረዉም ነበር።

«በሊቢያ ላይ የተቀነባበረ ሴራ አለ።ሊቢያን ለመቆጣጠርና ነዳጅ ዘይታችንን ለመዝረፍ ያለመ ሴራ።ሊቢያዉያን በሕይወት እያሉ ይሕ አይፈቀድም።ይፋለማሉ እንጂ።»

የቃዛፊን የአርባ-ሁለት ዘመን አገዛዝ ለማስወገድ በነፍጥ መዋጋት የጀመሩት አማፂያንም እንደ ቃዛፊ ሁሉ በርግጥ ሊቢያዉን ናቸዉ።ምናልባትም የወደፊቷ ሊቢያ መሪ።የተጣማሪዎቹ ሐገራት ጦር የቦምብ ሚሳዬል ድብደባ ግን ለነሱ እና እነሱ እንወክለዋለን ለሚሉት የሊቢያ ሕዝብ የምሥራች ነበር።ፌስታ።በሩምታ ተኩስ ተቀበሉት።

ጊዜ ጊዜን፥ ቦምብ-ሚሳዬልን፥ ቦምብ-ሚሳዬል ተክቶ ድብደባዉ ሁለተኛ ሳምንቱን ደፈነ። ቅዳሜ። በሁለት ሳምንቱ ጊዜ የተጣማሪዎቹ ጦር መኖሪያ ቤቶችን፥የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ደብድቧል፥ ሠላማዊ ሰዎችንም ገድሏል የሚል ዘገባ መሰማቱ አልቀረም።ሊቢያን የሚደበድበዉን ጦር የአዛዥነት ሥልጣን ባለፈዉ ሳምንት የተረከበዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ( ኔቶ) ወቀሳ-ዘገባዉን በቀጥታም ባይሆን ከግምት ማስገባቱን አስታዉቆ ነበር።የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንደርስ ፎግሕ ራስሙስን ጦራቸዉ ለሰላማዊ ሰዎች ጥንቃቄ እንደሚደረግ በድጋሚ ቃል ገብተዋልም።

«በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ መሠረት አላማችን ሠላማዊ ሰዎችንና ሠላማዊ ሰዎች የሚኖሩበትን አካባቢ ከቃዛፊ ጥቃት መከላከል ነዉ።»

Italien Libyen Demonstration Pazifisten
ጦርነቱን የሚቃወሙ ሠልፈኞች-ሮምምስል AP

ተጣማሪዎቹ መንግሥታትም ሆኑ ጥምር ድርጅታቸዉ የገቡትን ቃል በቅጡ ገቢር ማድረጋቸዉ የወታደራዊና የፖለቲካ ተንታኞችን ብዙ እንዳነጋገረ የድብደባዉ ሁለተኛ ሳምንት ተዘከረ።ቅዳሜም እንደ ወትሮዉ ተረኛዉ ቦምብ ሚሳዬል ሊቢያ ላይ ዘነበ።

የቃዛፊ ተቃዋሚዎች የወትሮ ፌስታ ደስታ ግን ቅዳሜ አልነበረም።እንዲያዉም የጥንካሬ መሠረት፥ የድላቸዉ ፈር ቀዳች የሆኑት የተጣማሪዎቹ የጦር አዉሮፕላኖች ከጣሏቸዉ ቦምቦች ቢያንስ አንዱን ለማየት ከቻሉት አማፂያን የተሰማዉ ዉግዘት-እርግማን ነበር።

«የተጣማዎቹ አዉሮፕላኖች ነበሩ።አይቻቸዋለሁ።ቦምቦች እየጣሉ ነበር።ይሕ ግድያ ነዉ።አብዮቱን መግደል ነዉ።»

በትንሽ ግምንት አስራ-ሰወስት አማፂያን ተገደሉ።ከኢራቅ እና ከአፍቃኒስታኑ ዉጊያ እንደለመድነዉ የወዳጅ ተኩስ ወይም ኮላተራል ዳሜጅ ይሉታል-የደብዳቢዉ ጦር አዛዦች።የእግረ መንገድ ወይም መናጆ ጥፋት እንደማለት።

የዋሽንግተን-ለንደን ፓሪስ መሪዎች ደጋግመዉ የጠቀሱት፥ የኔቶ ፀሐፊ ባለፈዉ ሳምንት የደገሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ በሊቢያ ላይ ከጣለዉ ማዕቀብ አንዱ ወደና ከሊቢያ የጦር መሳሪያ እንዳይገባ-እንዳይወጣ፥ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥም ይደነግጋል።

የአለም አቀፉን ድርጅት ዉሳኔ ለማስከበር የዘመተዉ ጦር ድብደባ አንደኛ ሳምንቱን በደፈነበት ሰሞን የፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አለን ዡፔ መንግሥታቸዉ አጥብቆ የተሟገተለት፥ ቀድሞ የጀመረዉ ድብደባ ከታለመለት ግብ ለመድረስ የዕለታት ወይም የሳምንታት ጊዜ ነዉ-የቀረዉ ብለዉ ነበር።ግቡ ደግሞ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን አጋዛዝ ማስወገድ እንደሆነ የተጣማሪዎቹ መንግሥታት መሪዎች ያልተናገሩበት ጊዜ ጥቂት ነዉ።

የማቀቡን ፅናት፥ የድብደባዉን ሒደት ከሁሉም በላይ የሊቢያን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወሰን ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ለንደን ላይ የተሰየመዉ ጉባኤ ተካፋዮች ግን የዡፔ ቃል-የተጣማሪዎቹ መንግሥት መሪዎች እቅድ በቀላሉ ገቢር እንደማይሆን ተገንዝበዉት ነበር።የጋራ ግንዛቤዉ ተጣማሪዎቹን መንግሥታት ለሌላ መፍትሔ ሲያስገድድ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አዲሱን እቅዳቸዉን ይፋ አደረጉ።

«ወደ ሊቢያ የጦር መሳሪያ ማስገባት ካለብን እንችላለን ብሎ መናገር ተገቢ ነዉ።ባሁኑ ጊዜ ሁሉንም አማራጮቻችን እንመለከታለን።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ባለፈዉ ሮብ።የሊቢያን አማፂያንን ወደ ማስታጠቁ ያዘነበለዉን የዋሽንግተኞችን አቋም ፓሪሶችም ደገፉት።የቀድሞዋ የሊቢያ ቅኝ ገዢ ኢጣሊያ ግን አልተቀበለችዉም።የሮሞች ምክንያት የሊቢያ አማፂያንን ማስታጠቅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጣለዉን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የሚጥስ ነዉ-የሚል ነዉ።ሊቢያን ከሚደበድቡት ግንባር ቀደም ሐገራት ብሪታንያ ግን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ዊሊያም ሔግ ያኔ እንዳሉት መንግሥታቸዉ አንዱንም አልወሰነ።

«እነዚያን የተባበሩት መንግሥታት ዉሳኔዎችን የምንገነዘባቸዉ የጦር መሳሪያዉ ማዕቀብ በመላዉ ሊቢያ የሚፅና ነዉ።ይሁንና መሳሪያዎቹን ለእራስ መጠበቂያነት ለሚያዉሉት ወገኖች ብቻ በሆነ ሁኔታ ማስታጠቁ ምናልባት ተገቢ ይሆን ይሆናል።ያም ሆኖ ገና አልወሰንም።»

ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ግን የዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን አባባል በማግስቱ አፈረሱት።እና የለንደንን ሠልፍ ከዋሽንግተን ፓሪሶች ጋር አስተካከሉ።

«የኛ አመለካከት (ዉሳኔዉ) ሠላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለሚከላከሉ ሐይላት ድጋፍ መስጠትን የግድ አይከለክልም የሚል ነዉ።»

ማዕቀቡ እንዲጣል አጥብቀዉ የተሟገቱት፥ያረቀቁት ያስፀደቁትም የፓሪስ፥ ለንደን ዋሽንግተን መንግሥታት ናቸዉ።ማዕቀቡን በጦር ሐይል ለማስከበር በሚል ሊቢያን የሚደበድቡትም እነሱዉ ናቸዉ።የማዕቀቡን ይዘት ትርጓሚዎቹም እነሱነተቸዉ በርግጥ አላጠራጠረም።

ሰወስቱ መንግሥታት ሥለ ማዕቀቡ ይዘት ባለፈዉ ሳምንት አዲስ በሰጡት ትርጓሜ መሠረት የሚወስዱ ወይም ሊወስዱ ያሰቡትን እርምጃ ገቢር የሚያደርጉበት መንገድ ግን አነጋጋሪ ነበር። የድብደባዉ ሁለተኛ ሳምንት ቅዳሜ ሲዘከር ትልቁ ዜና የተጣማሪዎቹ የጦር አዉሮፕላኖች የሊቢያ አማፂያንን ገደሉ የሚለዉ ብቻ አልነበረም።የዚያኑ ዕለት ቅዳሜ ሁለተኛዉ ትልቅ ዘገባ በዶሐ-ቀጠር በኩል ከሥራቃዊ ሊቢያ ተሰማ።

«ምንጫችን እራሱ ሥልጠናዉን ተካፍያለሁ ያለ አማፂ ተዋጊ ነዉ።ሥሙን አንጠቅስም።ካሜራ ፊት መቅረብም አልፈለገም።ተዋጊ መሆኑን ግን አረጋግጠናል።ምሥራቃዊ ሊቢያ ዉስጥ በሚስጥር ሥለተቋቋመዉ ማሰልጠኛ ተቋምም በዝር ዝር አስረድቶናል።እራሱም ለሰወስት ሳምንት ሥልጠና ወስዷል።እንዳለዉ የአሜሪካና የግብፅ ልዩ ጦር ባልደረቦች ለሊቢያ ተዋጊዎች ልዩ ሥልጠና እንደሚሰጧቸዉ ገልፆልናል።»

አልጀዚያራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገቢ። በዘገባዉ መሠረት የዋሽግተን፥ ለንደን፥ ፓሪስ መሪዎች የሊቢያ አማፂያንን ለማስታጠቅ አስበናል ከማለታቸዉ በፊት አማፂያኑን ማሰልጠን ማስታጠቁ ተጀምሯል። የኦባማ፥ ካሜሩን መግለጫ በተሰማበት ዕለት ሐሙስ ደግሞ ካቱሻ የተሰኘዉን የትከሻ ላይ ሮኬት የጫነች መርከብ ከግብፅ ምሥራቃዊ ሊቢያ ገብታለች።

የዩናይትድ ስቴትሷ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ከጥቂት ሳምንታት በፊት የትልቅ ሐገራቸዉን ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች መብለጡን የመሰከሩለት አል-ጀዚራ ከጋስ-ሐብቷ እኩል ስሟን የሚያስጠራላት ቀጠር ደግሞ ለሊቢያ አማፂያን ቴሌቪዥን ጣቢያ ከፍታለች።

የዩናይትድ ስቴትሱ መከላከያ ሚንስትር ሮበርት ጌትስ ሐገራቸዉ አማፂያኑን ማሰልጠን ማስታጠቋን አላረጋገጡም።አላስተባበሉምም።ሚንስትሩ እንዳሉት ግን ግብፅ፥ ቀጠርም ሆነች ሌሎች ሐገራት ቢያደርጉት የአለምን ሕግ ለማስከበር ጦር ያዘመተችዉ ሐገር የአለም ሕግ ተጣሰ ብላ አትቃወመምም።

«(አማፂያኑን) ማሠልጠንን በተመለከተ፥ መርዳትን በተመለከተ ሐቁ ይሕን ማድረግ የሚችሉ ብዙ ሐገራት አሉ።ይሕ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ የምታደርገዉ አይደለም።ሌሎች ሊያደርጉት ይችላሉ።»

የቱኒዚያ እና የግብፅ ሕዝባዊ አመፅ ባየለበት ሰሞን አመፀኛዉን ሕዝብ ለመርዳት ቀርቶ የሁለቱን ሐገራት አምባገነኖች በሚገባቸዉ ስም «አምባገነን» ለማለት የደፈረ የዋሽንግተን፥ ለንደን፥ ፓሪስ ሹም አልነበረም።እንዲያዉም ፓሪሶች የቤን ዓሊን አፋኝ-ገዳይ የሥለላ ሐይል ለማስታጠቅ ሲጣጣሩ ነበር-ቢን ዓሊ እብስ ያሉት።

USA Libyen Tomahawk Rakete wird abgefeuert
ቶምሐዋክምስል dapd

የሊቢያ ሕዝብ ገዢዎቹን ተቃዉሞ አደባባይ መዉጣቱ በተሰማ ሳልስት ሰወስት የኔዘርላንድስ ኮማንዶ ወታደሮች ሲርት ዉስጥ ተያዙ።የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ወደ ቬኑዙዌላ መሸሻቸዉን የሚጠቁም መረጃ ደርሶኛል ባሉ ሳምንት SAS በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጣራዉ የብሪታንያ ልዩ ጦር ባልደረቦች ቤንጋዚ ዉስጥ ተያዙ።ከድብደባዉ በፊትና በሕዋላ የተጀመረዉ ሴራ ቀጥሎ የሊቢያ መንግሥት ባለሥልጣናትን እያስከበለ ነዉ።እስካሁን የመጨረሻዉን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩን ለንደን ዶሏል።

የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ የቱኒዚያ፥ ግብፅ የመን ብጤዉን ሕዝባዊ ሠላማዊነት ከተቀማ በርግጥ ወር ደፈነ።አመፁን የተካዉ ዉጊያ ድብደባ ዳግማዊት ኢራቅን አለያም ዳግማዊት ሶማሊያን ሰሜን አፍሪቃ፥ ዳግማዊ ሳዳምን ትሪፖሊ ማሳየት አለማሳየቱ ነዉ-የከንግዲሁ ጥያቄ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ