1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ጊዜያዊ ሁኔታ፣

ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2003

በሊቢያ የህዝብ አመፅ ይቃጣል ተብሎ ሳይታሰብ ፤ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ፣ተጀምሮ እንደቀጠለ ነው። ይሁንና በግብፅ የታየውን ቁጥብነት ያላንጸባረቁት የአገሪቱ የጦር አኤሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች፣ ለተቃውሞ አደባባይ በወጣው ህዝባቸው ላይ መተኮሳቸው ከተዘገበ ወዲህ በዓለም ዙሪያ ፤

https://p.dw.com/p/R3D3
በቤንጋዚ፣ የወታደሮችና የሲቭል ተቃዋሚዎች ኅብረትምስል AP

 በኢራንና በጋዛ አስተዳዳሪዎች በሆኑት  የሐማስ አመራር አባላት ጭምር ፤ ውግዘትን ነው ያስከተለው። በመቶ የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሰልፈኞች፣ በሩምታ ተኩስ  የተገደሉበት ድርጊት ፤ ዓለምን ክፉኛ ነው ያስደነገጠው። ስለሊቢያ ወቅታዊ ይዞታ --ተክሌ የኋላ---

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት በዝግ ስብሰባ ይመክራል፤  የዐረብ መንግሥታት ማኅበር አምባሳደሮችም ፣  ካይሮ ውስጥ  በዛሬው ዕለት ስለሊቢያ ለመምከር ቀጠሮ ይዘዋል።

 41 ዓመታት በሥልጣን ላይ የሚገኙትን አሁን የ 68  ዓመት አዛውንት የሆኑትን የሊቢያውን መሪ፣ ሙኧመር ቓዛፊን በመቃወም ህዝብ አደባባይ መውጣት ከጀመረ ካለፈው ማክሰኞ ወዲህ ፣ የዓይን ምሥክሮች እንዳሉት በቤንጋዚ የወደብ ከተማ ብቻ ቢያንስ 300 ሰዎች ፤ በመዲናይቱ ትሪፖሊም በትናንትናው ዕለት ብቻ፣ 150 የተቃውሞ ሰልፈኞች ተገድለዋል። የተቃውሞው ወገን ግን ከ 560 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነው የገለጠው። ኧል ዐረቢያ የተሰኘው ማሠራጫ በበኩሉ  1,400 የሚሆኑ ሰዎች ደብዛቸው መጥፋቱን በዛሬው ዘገባው ላይ ገልጿል።  ግድያውን በመቃወም ፣ በዓለም ዙሪያ ብዙዎቹ የሊቢያ ዲፕሎማቶች፣ ራሳቸውን ከሙአመር ጋዳፊ አገዛዝ በማራቅ ፤ ከተቃውሞው ጎራ ተሰልፈዋል። በተባበሩት መንግሥታት የሊቢያ አምባሰደር ምክትል ፣ ኢብራሂም ኧል ዳባሺ ፣ ኒው ዮርክ ውስጥ ትናንት ባስቸኳይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በሊቢያ ምሥራቃውያን ከተሞችም ሆነ አሁን በትሪፖሊ የተካሄደው፣ በእርግጥ የለየለት የህዝብ ጭፍጨፋ ነው። ከትሪፖሊ ከሰዎች የሚልኩልን መልእክት እንደሚለው፣ ፈላጭ ቆራጩ መንግሥት መንገድ ላይ የሚታየውን ማንኛውንም ሰው እየገደለ ነው። የውጭ ቅጥረኛ ወታደሮቻቸውን በየመንገዶቹ አሠማርተዋል። እነርሱም ፣ ማንም የተቃውሞ ሰልፈኛ ብቅ ካለ ተኩሰው ነው የሚገድሉት። ሞቱም- አልሞቱም በሰልፈኞች ላይ እንዲሁ በቀጥታ እያነጣጠሩ ነው የሚተኩሱ። እንደሚመስለኝ፤ አንድ ርእሰ-ብሔር ፣ በጨዋ ደንብ፣  ተቃውሞአቸውን  በሚያሳዩ ሰልፈኞች ላይ እንዲተኮስ ሲያደርግ ፤ ይህ የመጀመሪያ ይመስለኛል። ልጃቸው ትናንት በሊቢያ ህዝብ ላይ ግልፅ በሆነ ቋንቋ ጦርነት አውጇል።»

ሊቢያዊው ዲፕሎማት ኢብራሂም ዳባሺ፣ ሃገራት በመላ፣ በቀጥታ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ፣ኮሎኔል ጋዳፊና አገዛዛቸው ፣ ህዝቡን መጨፍጨፍ ያቆሙ ዘንድ እንዲያሳስቧቸው፤ ይህን ለማስፈጸምም እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል በማለት ጠንከር ያለ አቋም አንጸባርቀዋል።   የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን፤ በሊቢያ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የተወሰደው ብርቱ የኃይል እርምጃ፣ በዓለም አቀፍ ነጻ መርማሪ ቡድን እንዲጣራ አሳስቧል። በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የተወሰደውን እርምጃ፣ የእስላማውያን አገሮች ጉባዔም ድርጊቱን በማውገዝ፣ እርምጃው ፤ ለሰብአዊ መብትና  ለእስላማዊ እሴቶችም ክብር ያልሰጠ  ነው ብሏል።   

ጋዳፊ ወደ ደቡብ አሜሪካ ሳይሸሹ አልቀሩም የሚል ዜና ከተናፈሰ ወዲህ፤ ባለፈው ሌሊት በአገሪቱ ቴሌቭዥን ለ 20 ሴኮንድ ሲናገሩ ታይተዋል። ሌሊቱን፤ ትሪፖሊ ውስጥ  ከደጋፊዎች ጋር ለማሰለፍ ፈልገው  ፤ በዝናብ ሳቢያ ተፈጻሚ እንዳላደረጉት  ቢወሳም ፣ ጋዳፊ ፣ ይህን ያሉበት ፊልም መቼና በስንት ሰዓት እንደተቀረጸ አልተወሳም።  ካገር እንዳልወጡ ለማሳወቅም የሊቢያው መሪ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በአረንጓዴ ው አደባባይ ነበርሁ። እዚህ ፤ ትሪፖሊ ውስጥ እንጂ  በ ቬነዝዌላ እንደማልገኝ ለማሳየትም ከወጣቶች ጋር ተነጋግሬአለሁ። የመገናኛ ብዙኀን ውሾች የሚሉትን አትመኗቸው።»

ሊቢያ ፤ በተቃውሞ ሰልፍ በተናጠችበትና አገዛዙም ብርቱ እርምጃ መውሰዱ  በሚነገርበት የአንድ ሳምንት ቀውጢ ጊዜ፣ ብዙ የውጭ አገር ተወላጆችም በጭንቅ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።  ግብፅ፤  ከ 1-1,5 ሚሊዮን የሚሆኑ በሊቢያ የሚገኙ ዜጎቿን ድንበር ላይ ለመቀበልና እርዳታ ለማድረግ ተዘጋጅታለች። ትናንት 5,000 ያህል ግብጻውያን ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን 10,000 ያህል ድንበር ላይ  እንደሚገኙ ተነግሯል። የቤንጋዚ አኤሮፕላን መንኮብኮቢያ መሥመር  ሙሉ-በሙሉ መደምሰሱን የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አህመድ አቡል ጌይት ገልጸዋል።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ