1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የላይፕዚጉ ፊስቲቫል እና አጫጭር ባህላዊ ዘገባዎች

እሑድ፣ ጥቅምት 22 2002

በዛሪዉ ጥንቅራችን ስለ ታዋቂዉ የጀርመን የዶክመንተሪ ፊልም ፊስቲቫል እንዲሁም በጀርመን ድረ-ገጾች በሳምንቱ የሰፈሩትን ባህል ቀመስ ዜናዎች አጠር አጠር አድርገን ይዘን ቀርበናል

https://p.dw.com/p/KJzC
በፊስቲቫሉ አፍሪቃዊ መለያምስል DW

በያዝነዉ ሳምንት እዚህ በጀርመን አለም አቀፍ የዶክመንተሪ እና የምስል ፊልም ፊስቲቫል ተጀምሮአል። ይህ ዘንድሮ ለ 52 ኛ ግዜ የቀረበዉ የፊልም ፊስቲቫል በቀድሞዋ የምስራቅ ጀርመን ሁለተኛ ከተማ በነበረችዉ በላይፕዞክ ከተማ ሲሆን በፊስቲቫሉ ላይ ከ 69 አገሮች የመጡ የፊልም ስራ አዋቂዎች ተሳታፊዎች መሆናቸዉ ታዉቋል። በጀርመን ታዋቂ የፊልም ፊስቲቫል እንደሆነ የሚነገርለት ይህ የላይፕዚጉ የፊልም ፊስቲቫል ዘንድሮ የአፍሪቃን የዶክመንተሪ ፊልም ስራ ዋና ርእሱ በማድረጉም ለየት እንደምያደርዉ ተገልጾአል። በአዉሮጻ ከሚካሄዱ ፊልም ፊስቲቫሎች በተለይም በዶኩመንተሪ ፊልም ረገድ በላይፕዚግ ዉስጥ በየአመቱ የሚደረገዉ ፊልም ፊስቲቫል በትልቀቱና በርካታ አገራትን በማሳተፉ በኒደርላንድ አምስተርዳም ዉስጥ ከሚካሄደዉ ቀጥሎ በሁለተኛነት እንደሚገኝ ተገልጾአል። በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ እለት የተጀመረዉ ይህ አንድ ነገር ላይ ትንታኔ የሚሰጥ ፊልም ማለት የዶክመንተሪ ፊልም ፊስቲቫል በአለም አቀፍ ደረጃ ስድሳ ዘጠኝ አገራትን ሲያሳትፍ ሶስመቶ ሰላሳ ያህል ጥናታዊ ፊልሞችንም እንደሚመለከት ተገልጾአል። የዘንድሮዉ የጥናታዊ ፊልም ሊስቲቫል ዋና ርእሱ ወይም ዋና ትኩረቱ ያደሰገዉ የአፍሪቃን የዶክመንተሪ ፊልም ነዉ። በዝግጅቱ ላይ ከቀረቡ የአፍሪቃ ዶክመንተሪ ፊልሞች መካከል ከአንጎላ ለዉድድር የቀረበዉ «የሉዋንዳ የሙዚቃ ፋብሪካ» በተሰኘ የቀረበዉ የጥናታዊ ፊልም ቅንብር ነበር።
በቀረበዉ ፊልም ላይ በሳምንቱ መጨረሻ የአንጎላ ተወላጁ ወጣት የሙዚቃ አዋቂ አዲስ ሙዚቃ ለማዉጣት ጥረት ላይ መሆኑን ይናገራል። በሚኖርበት አንድ አነስተኛ እና በኑሮ ዝቅተኛ በተባለበት ቀይ ሁለት አስተኛ ክፍል ሁለት አነስተኛ የሙዚቃ መቀመርያ ስቱድዮ አዘጋጅቶአል። ሙዚቃዉን ቀምሮ አዉጥቶ እና አዉርዶ የሰራዉን ሙዚቃ የሚኖርበት የሉዋንዳ ከተማ ነዋሪ ሁሉ ሲያደምጥለት ይታያል። ሙዚቃዉ ከዘመናዊዉ የራፕ ሙዚቃ ከባህላዊዉ የከበሮ እና የክራር መሰሉን የሙዚቃ ቃና አገናኝቶ አዲስ ዜማን ያሰማል።
ከአጎላ ሉዋንዳ ከተማ እዚህ ላይፕዚክ ከተማ የዶክመንተሪ ፊልም ፊስቲቫል ላይ የቀረበዉ ፊልም አዘጋጅ የፊልም ማቀናበርያ ስቱድዮዉ ከጠዋት እስከ ማታ በስራ የተጠመዱ ሰዎች የተሞላ እና የሚያዜሙ ሰዎች ሙዚቃቸዉን ሲቀርጹ ሲወያዩ ይታያል። ይህ ጥናታዊ ፊልም በተለይ ወጣት አንጎላዉያን ኑሮን ነዉ የሚቃኘዉ። አንዲት ወጣት ስለ ሙዚቃዉ ህይወት «ባጠቃላይ እያንዳንዱ ወጣት ማለት ይቻላል ይህንን በባህላዊ እና በዘመናዊ ሙዚቃ በተቀናበረ ሙዚቃ በመታጀብ ያዜማል ይቀረጻልም። ይህ አይነቱ ሙዚቃ በአሁኑ ግዜ በሉዋንዳ ነዋሪ በሆኑ ወጣቶች ዙርያ በጣም ተወዳጅ ሆንዋል። በስቱዲዮ አዚመዉ ለመቀረጽ ታዳጊ ህጻናት ሳይቀሩ ነዉ የሚመጡት፣ አንዳንድ ግዜ ከአንድ መቶ ወጣቶች በላይ ነዉ ሰልፍ ይዘዉ ሙዚቃቸዉን ለመቅረጽ ቆመዉ ሲጠብቁ የሚታየዉ»
በቁሳቁስ በትክክል ያልተሟላ እና በጣም ጠባብ ክፍል ያለዉ የሉዋንዳዉ የሙዚቃ ስቱድዮ ዉስጥ ወጣቱ የሙዚቃን ፍቅር ለመግለጽ ተሰጦዉን ለሌላዉ ለማሳየት ስለ ሚደረገዉ ጥረት የሚተርከዉ ጥናታዊ ፊልም ዘንድሮ በላይፕዚጉ የፊልም ፊስቲቫል ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ፊልሞች አንዱ ነዉ። ሰላሳ ስድስት በምስል የተቀናበሩ ፊልሞች የቀረቡበት እና አስራ አምስት ከአፍሪቃ የመጡ ጥናታዊ ፊልሞች ለዉድድር የቀረቡበት ይህ ፊስቲቫል አሸናፊዉ ሰባ ሰባት ሽህ ይሮ ሽልማት እንደሚያገኝ ከወዲሁ ተገልጾአል። የፊልሙ ፊስቲቫል በዛሪዉ እለት ምሽት ላይ ይጠናቀቃል።
ሰሞኑን የጀርመን የባህል መድረክ ገጽ ላይ ከሰፈሩት ርዕሶች መካከል፣ አንዱ እና ሰፊዉን ቦታ የያዘዉ በዚሁ ሳምንት ዉስጥ የአለም የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ከዚህ አለም በሞት በተለየ በአራት ወሩ በመጨረሻዎቹ ወራቶች ዉስጥ በለንደን ዉስጥ ለአለም የሙዚቃ አፍቃሮዎቹ ሊያቀርብ የነበረዉ የሙዚቃን ድግስ በመለማመድ ላይ ሳለ የተቀረጸዉን ፊልም ለአለም ህዝብ ለመጀመርያ ግዜ ለእይታ መቅረቡ ነበር። አንድ ሰአት ከሃምሳ አንድ ደቂቃ ርዝመት ያለዉ This is it የተሰኘዉ የፖፕ ሙዚቃ ንጉሱን የመጨረሻ የሙዚቃ የህይወት ዘመን የሚያሳየዉ ይህ ፊልም በተለያዩ የአለም አገራት በመጀመርያ እለት ለእይታ ሲበቃ በአለም ዙርያ ያሉ የፊልም ቤቶች በጠቅላላ ሃያ ሚሊዮን ዶላር ማስገባታቸዉ ተጠቅሶአል። ባለፈዉ ዕረቡ ምሽት ላይ በአለም ዙርያ ያሉ 15 ሺ ፊልም ቤቶች ፊልሙን በአንድ ግዜ ለተመልካች ማቅረባቸዉም ተገልጾአል። በዚሁ ምሽት በጀርመን ብቻ 185 ሺ ተመልካች ይህንኑ የማይክል ጃክሰንን የመጨረሻ የሙዚቃ ልምምድ ትርኢት እንደተመለከቱ እና በጀርመን ይህን ያህል ቁጥር ህዝብ በአንድ ግዜ ማየቱ አንድ አዲስ ሁኔታ መሆኑም ተገልጾአል። የማይክል ሶስት ወንድሞች ይህንኑ ፊልም እንዳዩ ሲገለጽ እናቱ እና ታናሽ እህቱ በጥልቅ ሃዘን ብቻ መመልከት እንደማይችሉ መግለጻቸዉ ተዘግቦአል። በሌላ በኩል የማይክል ጃክሰን አባት ልጃቸዉ ማይክል ሞቶም ታላቅ ክብርና ገቢ እንዳለዉ ለጋዜጠኖች ገልጸዉ ይህ ቀርቶብኝ በህይወት ቢቆይልኝ ይሻለኛል ብለዉ የሰጡት ቃለ ምልልሳቸዉ ዳግም በማይክል ጃክሰን ወዳጆች በኩል ጥቁር ነጥብ እንዲያገኙ አድርጎአቸዋል። ማይክል ጃክሰን ከዚህ አለም በሞት ከተለየበት ቀን አንስቶ ያዜማቸዉ ሃያ ያህል ሙዚቃዎቹ በአለም የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ እስካሁን የመጀመርያዉን ቦታ እንደያዙ ተገልጾአል።

Flash-Galerie Michael Jackson This Is It
ምስል Sony Pictures

እንደ አዉሮፓዉያኑ የቀን መቁጠርያ ሰሌዳ የበጋዉ ወራት አልፎ ዝናብ የበዛበት ጭጋጋማዉ የክረምቱ መንደረሪያ የሆነዉ ወራት ከገባ አንድ ወር አስቆጥሮአል። በጀርመን የነበረዉ ሞቅ ያለ የአየር ጠባይ በቅስበት ተቀይሮ ሃይለኛ አጥንት የሚገባዉ ብርድ ከጀመረም ሳምንታትንን አስቆጥሮአል። ከዚሁ ጭጋጋማ ቀዝቃዛ አየር ጋር ተያይዞ በበርካታ አገራት የሚከበረዉ ሃለዊን ጥንታዊ የሆነ መጤ ባህላዊ በአል በትናንት ምሽት ለዛሪ አጥብያ በጀርመንም ተከብሮአል።
በጀርመንም በተለይ የራይንን ወንዝ ተንተርሰዉ የሚገኙት የጀርመን ግዛቶች በጉጉት ያከብሩታል። የበአሉ አከባበር በአስፈሪዉን ጭንብል ፊታቸዉን ሸፍነዉ፣ ግማሾች ጥቁር ቱታ ልብስ ላይ፣ አጽም አስመስለዉ በነጭ ቀለም ስለዉ፣ ሌሎች ደግሞ፣ ፊታቸዉን በቀይ በቀለም፣ ደም በማስመሰል እንደተጨማለቀ ቀብተዉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ፊታቸዉን ጥቁር ቀለም፣ ሌሎች ደግሞ ነጭ፣ እንደተመቻቸዉ፣ በመቀባት፣ ሰይጣን አለዉ የሚባለዉ ጥርስ አይነት ሰክተዉ፣ እየተሳሰቁ ሲያከብሩ ይታያል።

Halloween Flash-Galerie
ምስል DPA

በትናንትናዉ እለት በጀርመን ይህ ሃለዊን የተባለዉ መጤ በአል ትይዩ የበርሊን ግንብ የተገረሰሰበት ዕለት ታሰቦ ዉሎአል። ዓለምን በምሥራቅና ምዕራብ ከፍሎ የኖረው የቀዝቃዛው ጦርነት መለያ የበርሊኑ ግንብ የተገረሰሰበት ሃያኛ ዓመት በበርሊን ከተማ ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለር እንዲሁም መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በተገኙበት የቀድሞዉ አሜሪካ ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ፣ የቀድሞዉ ሩሢያው ፕሬዚደንት ሚሃኢል ጎርባቾቭና የጀርመን መልሶ-ውሕደት ወቅት ቻንስለር የነበሩት ሄልሙት ኮል በታሪክ ምሥክርነት ተገኝተዋል። የጀርመኑ ፕሪዝደንት ሆርስት ኮለር ሶሥቱን ፖለቲከኞች በአስተዳደር ጥበባቸው በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ የተዘጋውን በር ከፍተዋል ሲሉም አወድሰዋቸዋል። ጀርመናዉያንን ከአርባ አመታት ግድም ከፍሎ የቆየዉ ግን’ብ የተገረሰሰበትን እለት በየአመቱ በማክበር ታሪካዊ ባህላቸዉ አድርገዉታል።

አዜብ ታደሰ