1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ሮሮ

ሐሙስ፣ መጋቢት 6 2010

«ንፋስ ስልክ ላፍቶ ሃና ማርያም አካባቢ የሚኖሩን ቤቶቻችንን አፈረሱብን ሲሉ አማረሩ። «የቆዩ ቤቶችን ሁሉ ነዉ ያወደሙት። ሕጻናት ከትምህርት ቤት ሲመጡ ቤታቸዉ ላያቸዉ ላይ ፈርሶ ነዉ የጠበቃቸዉ። እየተሽቀዳደሙ ቆርቆሮ እየነቀሉ እና በመኪና እየጫኑ ቆርቆሮዉን ይሸጣሉ፤ ግርግዳዉን በዶዘር ያፈርሳሉ፤ በጣም ያሳዝናል። ለማን አቤት እንበል?» ብለዋል

https://p.dw.com/p/2uP7u
Äthiopien Empörung über den Abriss von Häusern in Lafto
ምስል Haregeweyene GO

«ቆርቆሮዉን ይሸጣሉ ፤ ግርግዳዉን በዶዘር ያፈርሳሉ»

በአዲስ አበባ ከተማ አጎራባች ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ሰፈራ ሃና ማርያም በተባለዉ ስፍራ ሕገ-ወጥ ናቸው በሚል ቤቶቻችን እየፈረሱብን ነዉ ሲሉ ነዋሪዎች አማረሩ። አካባቢዉ ላይ ቤቶቹ መፍረስ ከጀመሩ ዛሬ ሳምንት እንደሞላቸዉ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት የላፍቶ ነዋሪዎች ቤት አፍራሾቹ ቤቱን ከአፈረሱ በኋላ ቆርቆሮዉን ወስደዉ እንደሚሸጡም ተናግረዋል። በአካባቢዉ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች እንዳሉም ነው የጠቆሙት።   

በላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማርያም ወረዳ ልዩ ስፍራዉ ናሆም አደባባይ በተባለ ቦታ የሚገኙ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ቤት ፈረሳዉ የተጀመረዉ ልክ የዛሬ ሳምንት ነዉ። አካባቢዉ ላይ ከ 50 ሺህ በላይ የመኖርያ ቤቶች ይፈርሳሉ ተብለዋል። በስፍራው ከ 10 ዓመት በላይ ኖርያለሁ ያሉት ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉ ባለትዳር እና የልጆች አባት አቶ ሸዋንግዛዉ አበበ ቦታዉ ለባለ ሃብት ይሰጣል እንደተባሉም ገልጸዋል።

Äthiopien Empörung über den Abriss von Häusern in Lafto
ምስል Haregeweyene GO

«ለባለ ኃብት ከዉጭ ሃገር ለሚመጡ ለዲያስፖራዎች ቦታዉ ተሸጥዋል ልቀቁ ነዉ ያሉን። የምናዉቀዉ ነገር የለም ቦታዉን ከገበሪ ነዉ ገዝተን የገባነዉ። ገበሪዉ መሪቴ እንዴት ይሸጥብኛl ግብር አልበላሁበትም ሲል በዱላ ድብደባ ይደርሳል። አካባቢዉ ላይ ወደ 50 ሺህ የሚሆን ቤት ነዉ ያለዉ ሁሉም ይፈርሳል ተብሎአል። ካርታ ያለዉ ቤት አብሮ እየፈረሰ ነዉ»

ቤቱ የፈረሰበት በየቦታዉ ወደ ዘመድ ተጠግቷል ግማሹም እዛዉ ሜዳ ላይ ነዉ ያሉን ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁን የአካባቢዉ ነዋሪ በበኩላቸዉ ኮማንድ ፖስቱ ለአንድ ቀን በፈረሳዉ መሳተፉን ነዋሪዎች  ተናግሯል ይላሉ። 

«ነዋሪዎች ሄደዉ ምክንያቱን ጠይቀዋል። ኮማንድ ፖስቱ ከአዋጁ በኃላ ነዉ ያፈረስኩት እኔ ጨርሼ ወጥቻለሁ ብሎአል፤ ሌላዉ እኔ አይመለከተኝም መባላቸዉን ሰምቻለሁ። » የደረሰልን አካል የለም ሕጻናት ልጆቻችን በየሜዳዉ ተበትነዉብን ነዉ ያሉት።» ሲሉ ሌላኛዉ ስማቸዉ እንዳይነገር የጠየቁ ግለሰብም ምሬታቸዉን ገልፀዋል።

«ንፋስ ስልክ ላፍቶ ሃና ማርያም አካባቢ በጣም ችግር ላይ ነን ያለነዉ፤ እስካሁንም የደረሰልን አካል የለም። ሕጻናት ሜዳ ላይ ተበትነዉብን ነዉ ያሉት። 78 ዓመት የቆየ ቤት ሁሉ ነዉ እየፈረሰብን ያለዉ። ዳር ዳር ላይ አዳዲስ የተሰሩ ቤቶች ነበሩ፤ እናፈርሳለን ብለዉ የተወሰኑ ቤቶችን አፈረሱና ከዝያም ከሁለተኛዉ ቀን በኋላ ዶዘር ነዉ ይዘዉ የመጡት። የቆዩ ቤቶችን ሁሉ ነዉ ያወደሙት። ሕጻናት ከትምህርት ቤት ሲመጡ ቤታቸዉ ላያቸዉ ላይ ፈርሶ ነዉ የጠበቃቸዉ። እየተሽቀዳደሙ ቆርቆሮ እየነቀሉ እና በመኪና እየጫኑ ቆርቆሮዉን ይሸጣሉ ፤ ግርግዳዉን በዶዘር ያፈርሳሉ፤ በጣም ያሳዝናል።ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉ ሰዎች ሜዳ ላይ ነዉ ያሉት ሸራ ወጥሮ መቀመጥ እንኳ አይቻልም። ሲጀመር ሰዉን እንኳ በአይን ማየት አይፈልጉም። ምን አይነት በቀል እንደሆነ አልገባንም። የዛሬ ሁለት ዓመት እንዲሁ ብዙ ሰዉ ተፈናቅሎ ነበር። »  

Äthiopien Empörung über Abriss von Häusern in Addis Abeba
ምስል DW/H. Go

ቤቱን የሚያፈርሱበት ምክንያቱ ተነግሮአችኋል? « ምንም የተነገረን ነገር የለም»  በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የሚታየዉ ቀዉስ ሳይበቃ ቤት ማፍረሱ ለምን እንደሆን አልገባንም ያሉት ነዋሪዉ አክለዉም አፍራሾቹ ኮማንድ ፖስቱን ተማምነዉ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።

የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ገርጂ አካባቢ ወረገኑ የሚባል ቦታ ላይ «በሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ተገንብተዋል» የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች መፍረሳቸው ይታወሳል።  ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ በንፋስ ስልክ ለሙ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01  ስለተጀመረዉ የቤት ፈረሳ ጉዳይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ቀበሌዉ የሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ካህሳይ እና ወደ አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ያደረግነዉ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ አልተሳካም።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ