1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሌሶቶ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራና «ሳዴክ»

ሰኞ፣ ነሐሴ 26 2006

በደቡብ አፍሪቃ ንዑስ ግዛት በሌሴቶ ንጉሳዊ አስተዳደር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሳይካሄድ አልቀረም የሚል ዜና ከተሰማ በኋላ፣ ሶስት የደቡብ አፍሪቃ ልማት ማኅበረሰብ፣ በምሕፃሩ የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት የፖለቲካ የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የተጠቃለሉበት ኮሚቴ ትናንት አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ስለሌሶቶ ጊዚያዊ ሁኔታ መከረ።

https://p.dw.com/p/1D4xN
Lesotho Maseru Militär Hauptquartier nevorstehende Friedensverhandlungen
ምስል picture-alliance/AP Photo

የሃገሪቱ ጦር ኃይል ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ዋናዉን የፖሊስ ጣቢያ፤ የራድዮ እና የቴሌቭዝን ስርጭት ጣቢያዎችን እና ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ላጭር ጊዜ በቁጥጥር ሥር ካደረገ በኋላ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መሸሻቸው ተሰምቶዋል።

የሌሶቶ ጠቅላይ ሚንስትር ቶማስ ታባኔ የመፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮብኛል በሚል ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከሸሹ በኋላ አዲሱ የሌሶቶ ጦር ኃይል ዋና አዛዥ ማፓራንኮ ማሃኦ ወታደሮቹ ወደየሰፈራቸው እንዲመለሱ አዘዋል። የጦር ኃይሉም ጠቅላይ ሚንስትሩን እንደሚደግፍ አስታውቀዋል። ይሁንና፣ በወቅቱ የሀገሪቱን ሥልጣን የያዘው ወገን በውል አልታወቀም።
ሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎች ባላት በሌሶቶ የጦር ኃይሉ አካሄደው የተባለውን መፈንቅለ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ለማፈላለግ የደቡብ አፍሪቃ የልማት ማኅበረሰብ «ሳዴክ» አባል ከሆኑት ደቡብ አፍሪቃ፣ ናሚቢያ እና ዚምባብዌ የተውጣጡ የፖለቲካ፣ የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ኮሚቴ ትናንት እሁድ ሌሊት ተገናኝቶ መክሮዋል። ደቡብ አፍሪቃ የሚገኙት የሌሴቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ መፈንቅለ መንግሥቱ የተካሄደዉ በምክትላቸዉ ሞቴዦአ ሜት ሲንግ አቀነባባሪነት ነዉ ሲሉ ወቅሰዋል።
«መንግሥት ግልበጣ ነዉ ተብሎ መጠርጠሩ፤ በርግጥ ሙሉ በሙሉ ስህተት አይደለም። መንግሥት ግልበጣ ነዉ የሚያሰኘዉ ነገር አለ። ነገር ግን ሙከራው ገና በጥንስሱ ተቀጨቶዋል። ሁኔታዉ በተቻለ ፍጥነት እንዲረጋጋ እየሰራንም ነዉ።» ወቃሽ እና ተወቃሽ የሌሶቶ ባለስልጣናት ታባኔ እና ሜትሲንግ ከደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ጋር እና በ«ሳዴክ» ስብሰባ ለመገኘት አሁን እዝያዉ ደቡብ አፍሪቃ እንደሚገኙ ነዉ የተገለፀዉ።
ውዝግቡ የተጀመረው ባለፈዉ ቅዳሜ ወታደሮች የሀገሪቱን ቁልፍ መስሪያ ቤቶች የራድዮ እና የቱሌቭዥን ጣቢያም ላጭር ጊዜ በተቆጣጠሩበት፣ ከትላልቅ ፖሊስ ጣቢያዎች መሳሪያ ከያዙ እና የጠቅላይ ሚንስትሩን መኖሪያ ቤት በከበቡበት ጊዜ ነበር። በዚሁ ሂደት በአብዛኛዉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ታባኔ ታማኝ በሆኑ ፖሊሶች እና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜትሲንግ ታማኞች ናቸዉ ተብሎ በሚታመን ወታደሮች መካከል በተነሳ የተኩስ ልዉዉጥ አንድ ወታደር እና አራት የፖሊስ ኃይላት ቆስለዋል።
የጦር ኃይሉ ማፓራንኮ ማሃኦ ባለፈዉ አርብ ሌተና ጀነራል ኬኔዲ ካሞሊን በመተካት አዲሱ የጦር ኃይሉ አዛዥ ተብለው የተሰየሙበትን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ፣ ሌተና ጀነራል ኬኔዲ ካሞሊ በስልጣናቸው እንዲቆዩ ነበር የጠየቀው።
በደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ቃል አቀባይ ክሌሶን ሞንየላ እንደገለጹት፣ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ለሌሶቶ ጦር ኃይል ጠንካራ ማስጠንቀቅያ አስተላልፎአል፤
«የደቡብ አፍሪካ መንግስት፣ ልክ እንደ አፍሪቃ ኅብረት፣ ሕገ መንግስታዊ አሰራርን ባልተከተለ የመንግስት ለውጥ ላይ ያለው አቋም ተመሳሳይ ነው። እና ይህንኑ የአፍሪቃ ኅብረት አቋም በድጋሚ ለማጠናከር ይፈልጋል። ይህ ዓይነቱ ኢ ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጥ በዝምታ ሊታለፍ እንደማይችል ያስጠነቅቃል።»
እንድያም ሆኖ መፈንቅለ መንግሥት ተፈፀመ መባሉን የሌሴቶ ወታደራዊ ኃይል ሃሰት ሲል አጣጥሎዋል። የወታደራዊ ኃይሉ ቃል አቀባይ ናቲሌሌ ናቶይ እንዳስረዱት፣ ፖሊስ ታባኒ የሚመሩትን ፓርቲ አባላት አስታጥቆ ተፎካካሪያቸው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ሜትሲንግ የሚመሩትን የሌሶቶ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ ፓርቲ አባላትን ሊያጠቃ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ለጦር ኃይሉ ከደረሰው በኋላ ብቻ ነበር በየፖሊስ ጣቢያ መሳሪያ ለመሰብሰብ የገባው።
ከባድ ፉክክር የታየበት ከጎርጎረሳዊ 2012 ዓ,ም የሌሶቶ ምርጫ በኋላ፤ ሀገሪቱ ጥምር መንግሥት መመስረትዋ ይታወቃል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ታባኔ ይህ ጥምር መንግሥት ያለምንም የጋራ መግባባት ዉሳኔ ያሳልፋል ሲሉ ቅሪታ አሰምተዉ ነበር። የሌሶቶ የዴሞክራሲ ኮንግረስ ፓርቲ መሪና፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜትሲንግ በበኩላቸዉ፤ ባለፈዉ ሰኔ ወር ፓርላማዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ታባኔ ላይ አይተማመንም ሲሉ፤ ድምፅ እንዲጠይቅ መገፋፋታቸዉ ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Putsch-Versuch in Lesotho 30.08.2014
ምስል Getty Images/Afp/Mujahid Safodien
Thomas Motsoahae Thabane Premierminister Lesotho
ምስል picture-alliance/dpa