1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልማት ርዳታዎችና መጠነኛዉ ዉጤት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 3 2006

የጀርመን የኤኮኖሚና የልማት ትብብር ሚኒስቴር ሀገሪቱ ለልማት የምታዉለዉን የርዳታ በጀት ማሳደጉን አስታወቀ። ምክር ቤት ከትናንት በስተያ በልማት በጀቱ ላይ ክርክር አካሂዷል። የተቃዉሞ ፖለቲከኞች ሀገሪቱ ከዓመታት በፊት ለአዳጊ ሃገራት የልማት ርዳታ የበለጸጉት በየዓመቱ እንዲያዋጡ ከተስማሙበት መጠን ለመድረስ ጀርመን ይቀራታል ሲሉ ተችተዋል።

https://p.dw.com/p/1BghE
Afrika, Entwicklungsminister Gerd Müller, Südsudan, Entwicklungszusammenarbeit
ምስል DW

በአዳራሹ ከሚገኙ መቀመጫዎች አብዛኞቹ ሰዉ አልባ ነበሩ፤ የጀርመን ምክር ቤት በሀገሪቱ የልማት ፖሊሲ ላይ ለመከራከር በቀጠረበት ዕለት። የሀገሪቱ የኤኮኖሚና የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር የልማት ፖሊሲዉ በአዲሱ የሀገሪቱ ጥምር መንግስት ለየት ያለ እና ከፍተኛ ትኩረት እንዳገኘ ነዉ ያመለከቱት። ይህም ጀርመን ለልማት ርዳታ የምትሰጠዉን የገንዘብ መጠን ከፍ ለማድረግ በመወሰኗ ይታያል ነዉ የሚሉት። በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ጀርመን ለልማት ርዳታ 6,44 ቢሊዮን ዩሮ ስትመድብ፤ ካለፈዉ ዓመት በጀት በ147,4 ሚሊዮን ይበልጣል። በሚመጣዉ ዓመትም መጠነኛ ጭማሪ እንደሚደረግ ነዉ የተገለጸዉ። የልማት ሚኒስትር ሙለር እንደሚሉትም ጀርመን ለዚህ ዘርፍ ይህን ያህል መጠን ያለዉ ገንዘብ ስትመድብ የመጀመሪያ ነዉ።

«የደረስንበት ስምምነት ከዚህ ቀደም በጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ታሪክ ከፍተኛዉ በጀት ነዉ።»

Afrika, Entwicklungsminister Gerd Müller, Südsudan, Entwicklungszusammenarbeit
ምስል DW

ይህ በልማት ርዳታ ስም ወደዉጭ የሚፈስ በርካታ ገንዘብ ትርጉም ካለዉ ተግባር ላይ ይዉላል ወይ የሚለዉ አዘዉትሮ የሚጠየቅ ጥያቄ መሆኑን ያመለከቱት ሚንስትሩ፤ በዚህ የልማት ርዳታ አንዳንዶች ስኬታማ ዉጤት ማስመዝገባቸዉን ገልጸዋል። አያይዘዉም ሌሎችም እንዲሁ በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ የተሻለ ዓለም ለመፍጠር እንዳስቻላቸዉም አብራርተዋል። ሆኖም እየጨመረ በሄደዉ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ምክንያት የልማት ፖሊሲዉ ፈተና እየገጠመዉ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። እንዲያም ሆኖ በፅናት በሚከናወኑ ጥረቶች የምግብ እህል እጥረትና መሰል ችግሮች ስጋት ሊወገድ እንደሚችል አመልክተዋል።

የጀርመን የኤኮኖሚና ልማት ትብብር ሚኒስቴር ወደአራት ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ከሚመድብላቸዉ ተግባራት ትልቁን ሥፍራ የሚይዘዉ ከመንግስታት ጋ የሚኖረዉ የሁለትዮሽ እና የቴክኒክ ትብብር አንዱ ነዉ። ቀሪዉ በጀት ለሶስት ዓበይት ፕሮጀክቶች የሚዉል ነዉ። ከነዚህ ለየት ያሉ ፕሮጀክቶች አንዱ «ረሃብ የሌለባት ዓለም» የተሰኘዉ 70 ሚሊዮን ዮሮ ገደማ ተመድቦለታል። 20 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ ዴሞክራሲን ለማስፋፋትና ሰዎች በየአካባቢያቸዉ የኤኮኖሚ አቅጣጫ እንዲቀይሱ ለማበረታታት ይዉላል። ሰላም የራቃቸዉን አካባቢዎች፤ ሰሜን ኮርያ ና መካከለኛዉ ምሥራቅን ለማረጋጋት ለሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች የሚዉል በጀትም ተመድቧል። ሙለር ወደደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ እና ሶርያ ድንበር አካባቢ በተጓዙበት ወቅት የተመለከቱት እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል።

«ከአንዳንዶቻችሁ ጋ በደቡብ ሱዳን መጠለያ ጣቢያዎች፤ በሶርያ የድንበር አካባቢ፣ እንዲሁም ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዉስጥ ያለዉን ሁኔታ ተመልክቻለሁ። የሕፃናቱን አይን ስትመለከቱና ለመኖር የተገደዱበትን አስከፊ ሁኔታ ታስተዉላላችሁ።»

Entwicklungsminister Gerd Müller Engagement Global
ምስል Engagement Globald, Thomas Ecke

በደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪቃና ሶሪያ በጦርነት ምክንያት ተሰደዉና ተፈናቅለዉ በአሰቃቂ ሁኔታ ለመኖር የተገደዱትን ወገኖች መንግስታቸዉ መዘንጋት አይፈልግም ይላሉ ሙለር ። እናም ስደተኞቹ የሚገኙበትን የአኗኗር ይዞታ ለመለወጥ የተለየ ተግባር መከናወን ይኖርበታል። ለዚህም 70 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ይመደባል። በተጨማሪም ፌደራል መንግስት በዓለም ዓቀፉ የአየር ንብረትና የአካባቢ ጥበቃ ላይም አተኩሮ መሥራቱን ይቀጥላል። እንዲሁም HIV AIDSን፣ TB እና ወባን ለማጥፋት ለሚሠሩ መርሃግብሮችም 240 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል።

የተቃዉሞ ፖለቲካ ወገኖች ግን ለልማት ትብብሩ የተጨመረዉ የገንዘብ መጠን አንሷል ነዉ የሚሉት። የአረንጓዴ ፓርቲ የጀርመን ምክር ቤት አባል አንያ ሃይዱክ የኑሮ ሁኔታ 10 በመቶ ጭማሪ በሚያሳይበት በዚህ ወቅት የልማት ትብብር ሚኒስቴር በጀቱ ላይ ያደረገዉ የ3,7 በመቶ እድገት እዚህ ግባ አይባልም ባይ ናቸዉ። የግራዉ ፖለቲከኛ ሃይከ ሄዝልም እንዲሁ መንግስት ለሚላቸዉ የልማት ተግባራት ጭማሪዉ ፍፁም በቂ አይደለም አሳፋሪም ነዉ ይላሉ። ሌሎች በርካታ ፖለቲከኞችም እንዲሁ ጀርመን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከስምምነት የተደረሰዉን ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ 0,7 በመቶዉን ለልማት ተግባር ማዋል የሚለዉን ዘንድሮም ገና አልደረሰችበትም ሲሉ ይተቻሉ። ሶሻል ዴሞክራቷ ዞንያ ሽቴፋን በአሁኑ ወቅት ጀርመን 0,38 በመቶዉን እንደያዘች ነዉ የሚያመለክቱት። በዚህ አካሄድም በመጪዉ ጎርጎሮሳዊ ዓመት ከተቀመጠዉ ጣሪያ መድረስ አትችልም ባይናቸዉ። ከበለፀጉት ሃገራት እነ ብሪታንያ ከዓመታት አጠቃላይ ገቢያቸዉ ለታዳጊ ሃገራት የልማት ተግባር ይዉል ዘንድ የተወሰነዉን ይህን ኮታ ካለፉ ሰንብተዋል።

ናኦሚ ኮንራድ/ ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ