1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልማት ዕርዳታ፤ የአፍሪቃ መርገምት ወይስ ፈውስ?

ረቡዕ፣ ነሐሴ 30 1999

የልማት ዕርዳታ ከበለጸገው ሰሜን በዕድገት ኋላ ቀር ሆኖ ወደሚገኘው ደቡባዊ የዓለም ክፍል በይፋ ሲፈስ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ አሳልፏል። ይሁን እንጂ ዕርዳታው በጅቷል-አልበጀም ዛሬ ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/E0ci

ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታ በዛሬው መልክ መስጠት ከተጀመረ ከአምሥት አሠርተ-ዓመታት ገደማ ወዲህ በወቅቱ ጎልቶ የሚታየው ጥቂቶቹ ሃብታሞች ይበልጥ መካበታቸው፤ ብዙሃኑ ደግሞ ይባስ ድሃ እየሆኑ መምጣታቸው ነው። ይህ ሃቅ የልማት ዕርዳታ የታዳጊውን ዓለም ሕዝብ አልጠቀመም፤ ጨርሶ መቅረት አለበት የሚሉ ወገኖች ድምጽ እንዲበራከት አድርጓል። የልማት ዕርዳታ ፈውስ ወይስ መርገምት?

የልማት ዕርዳታ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተከሰተው የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ውልድ ነው። ለዚህ ነበር ያለፈው ምዕተ-ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ የልማት ዘመን የሚል ስያሜ የተሰጠው። ይሄው የልማት ዘመን እ.ጎ.አ. በጥር ወር. 1949 ዓ.ም. የጊዜው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሃሪይ ትሩማን ፖሊሲያቸውን ሲያስረዱ እንደጀመረም አንዳንድ የኤኮኖሚ ጠበብት ይናገራሉ። “የደረርንበትን የሣይንስ ግስጋሤና የኢንዱስትሪ ብልጽግና በመጠቀም በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ አካባቢዎች ዕድገት የሚበጅ አዲስ ዕቅድ ማስፈን ይኖርብናል። አሮጌው ኢምፐሪያሊዝም፤ ለውጭ ትርፍ የሚደረግ ብዝበዛ በዕቅዳችን ውስጥ ቦታ የለውም። የምናልመው የዴሞካራሲን መርሆ መሠረቱ ባደረገ የልማት ዕቅድ ላይ ነው” ሃሪይ ትሩማን!

ይህ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ዋዜማ የትሩማን ራዕይ ርዕዮተ-ዓለማዊ መንስዔ ነበረው። ለዋሺንግተንና ለአጋሮቿ ፖሊሲው ታዳጊው ዓለም ወደ ሶቪየቱ ኮሙኒስት ጎራ እንዳይኮበልል መከላከል እንጂ ሌላ ነገር አልነበረም። እርግጥ የአሜሪካ የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ ከዚህ አንጻር በጅምሩ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለምሣሌ የማርሻል-ፕላን ራሷ በጀመረችው የዓለም ጦርነት ተንኮታኩታ የወቀችውን ጀርመንን ለተዓምራዊ ዕድገት አብቅቷል። ደቡብ ኮሪያም የዚሁ ዕርዳታ ተጠቃሚ ነበረች። ይሁን እንጂ ፍቱንነት የታየበት የማርሻል-ፕላን በዓለም ላይ ተስፋፍቶ እንዲቀጥል አልተደረገም። ለዚህም ምክንያቱ ታዳጊውን ዓለም ከድህነት ከማላቀቁ ይልቅ የበለጸገው ዓለም የራስ ጥቅም ማመዘኑ ነው።

የልማት ዕርዳታ ግን ጨረ እንጂ አልቀነሰም

በዓለም ላይ በልማት ስም የሚቀርበው ይፋ የልማት ዕርዳታ በአሃዝ ደረጃ ለነገሩ እየጨመረ ነው የመጣው። ባለፉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት በእጥፍ ገደማ በመጨመር በ 2005 አንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። የግል ዕርዳታ አቅራቢዎች ዓመታዊ አስተዋጽኦም ቢሆን በአሜሪካ ብቻ እንኳ ቢያንስ 34 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ነው የሚነገረው። ይሁን እንጂ ኋላ ቀር በተባሉት ተቀባይ አገሮች የረባ ልማትን አላስከተለም። ዛሬ ከዓለም ሕዝብ ሁለት ሚሊያርድ የሚሆነው የመከራ ኑሮውን የሚገፋው ከአንዲት ዶላር ባነሰች የዕለት ገቢ ነው። በየቀኑ 25 ሺህ ሰዎች በረሃብና ከዚሁ በተያያዙ ምክንያቶች ይሞታሉ። ታዳጊው ዓለም፤ በተለይም አፍሪቃ የልማት ዕርዳታው ከተጀመረ ከብዙ አሠረት-ዓመታት ወዲህ ዛሬም ከድህነት አዙሪት መውጣት አልቻለችም።

ይህ ደግሞ በበለጸገው ዓለም የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ ላይ የሚሰነዘረውን ትችት እያጠነከረው ነው የመጣው። ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ ለአፍሪቃ ጠንቅ ሆነ እንጂ ለሕብረተሰብ ዕድገት አልበጀም ከሚሉት ቀደምት ተከራካሪዎች መካከል አንዱ የኬንያው የኤኮኖሚ ባለሙያ ጀምስ ሺኩዋቲ ናችው። ሺኩዋቲ የልማት ዕርዳታ በፍጥነት መቆም አለበት፤ እኛ አፍሪቃውያን ራሳችንን ልንረዳ እንችላለን ይላሉ። ኬንያዊው ባለሙያ ይህንኑ ዓላማ ለማራመድ ከስድሥት ዓመታት ገደማ በፊት ናይሮቢ ላይ Inter Region Economic Network የተሰኘ ሃሣብ አፍላቂ መድረክ ሲያቋቁሙ የልማት ዕርዳታ ቢሮክራሲና ጥገኝነትን ከማራመድ አልፎ ፋይዳ እንደማሌለው ያስገነዝባሉ።

በርሳቸው ዕምነት አፍሪቃን ይበልጥ ድሃና በሙስና የተዋጠች ነው ያደረገው። በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት መንግሥታት ላይ ጨርሶ ዓመኔታ የላቸውም። “G-8 መንግሥታት ለበለጠ ዕርዳታ ቃል ከመግባት ባሻገር ያከናወኑት አንድም ነገር የለም። ለነገሩ አሁንም ቃል መግባታችውን አላቆሙም። ግን ችግሩ አብዛኛውን ጊዜ ያሉትን አለማድረጋቸው ነው። በመሆኑም ለአፍሪቃ ሕዝብ ከንቱ ተሥፋ መስጠታችውን እስካላቆሙ ድረስ የተሻለ ነገር ይኖራል ብዬ አልጠብቅም” ሺኩዋቲ ይህን የተናገሩት ሰሞኑን አቋማችውን ለማብራራት በዚህ በጀርመን መዘዋወር በያዙበት ወቅት ነው።

የልማት ዕርዳታ ፍቱንነት ማጠያየቅ

የምዕራቡን ዓለም የልማት ዕርዳታ ዘይቤ የኬንያውን ተወላጅ ያህል ጠንከር ባለ መልክ የነቀፈ የኤኮኖሚ ባለሙያ አይገኝም። ሺኩዋቲ ዕርዳታው ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ ለአፍሪቃ ከመጥቀም ይልቅ መጉዳቱን፤ የምዕራቡ ዓለም የልማት ዕርዳታ ፖሊሲም በአንጻሩ የመሪዎች ምዝበራ እንዲስፋፋ ማድረጉን ነው የሚናገሩት። እንደርሳቸው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በዕውነት አፍሪቃን ማገዝ ከፈለጉ አስከፊ ያሉትን ዕርዳታቸውን ሊያቆሙ ይገባል። በቢሊዮን የሚቆጠረውን አብዛኛውን ዕርዳታ የተቀበሉት አገሮች በከፋ ሁኔታ ላይ የሚገኙት መሆናቸውም ለዕርዳው ከንቱነት የሚጠቅሱት ተጨማሪ ምክንያታቸው ነው።

ጀምስ ሺኩዋቱ ከጀርመኑ ሣምንታዊ መጽሄት ከሽፒግል ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ጉዳዩን ጠለቅ ብለው ሲያስረዱ በዕርዳታው ገንዘብ ግዙፍ ቢሮክራሲ ሲገነባ ነው የኖረው። አፍሪቃውያን ለማኝ ሆነው እንዲቀሩ እንጂ ነጻ እንዲሆኑ ለማስተማር አልተሞከረም። ከዚህ በተጨማሪም የልማት ዕርዳታ በታዳጊ አገሮች የውስጥ ገበዮችን የሚያዳክምና ለአፍሪቃ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን በግል የመቋቋም መንፈስ የሚቀጭ ነው የሆነው። በሺኩዋቲ አባባል ምናልባት ሊያምኑት የሚያስቸግር ቢመስልም ዛሬ የአፍሪቃን ዕድገት አንቀው ከያዙት ችግሮች አንዱ ይሄው የልማት ዕርዳታ ዘይቤ ነው። ለነገሩ ምዕራቡ ዓለም ይህን ዕርዳታ ቢያቆም ተራው አፍሪቃዊ በአዕምሮው አይመዘግበውም። እጅግ ተጎጂዎቹ ጥቅማቸው የሚነካባቸው ባለሥልጣናት ብቻ ናቸው።

የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሚናስ?

ሺኩዋቲ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችንም ቢሆን ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ አድርገው ነው የሚመለከቱት። የሚያራግፉት የዕርዳታ ቁሳቁስ በዝቅተኛ ዋጋ እየተሸጠ የአገሬውን ነጋዴ እንደሚያዳክም ይጠቅሳሉ። ጥያቄው የአፍሪቃ አገሮች ቢቀር በጅምሩ ያለ ልማት ዕርዳታ ሊቀጥሉ ይችላሉ ወይ ነው። ዓለምአቀፉን የልማት ዕርዳታ ዘይቤ በመተቸት እርግጥ ሺኩዋቲ የመጀመሪያው አይደለም። የልማት ዕርዳታ ፍቱንነት ዕርዳታው ገቢር በመሆኑ መጠን ላይ ጥገኛ መሆኑም ማነጋገር ከጀመረ ቆይቷል። ፔተር ባወርንና ሚልተን ፍሪድማንን የመሳሰሉ ነጻ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች የልማት ዕርዳታ ፍቱን ሊሆን እንደማይችል ያስረገጡት ገና በ 60ኛዎቹ ዓመታት ነበር። ይህ አመለካከት ከዚያን ወዲህ ብዙ ተከታዮችን ማግኘቱም አልቀረም።

በሌላ በኩል ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ ተገቢውን ውጤት፤ ማለት ዕድገትን አለማስከተሉ ብዙ ምክንያቶች አሉት። በተቀባይ አገሮች የሙስና መስፋፋትና ማሕበራዊ ለውጦችን የማጓተቱ ሁኔታ አንዱ ሲሆን ዕርዳታ የሚሰጠውንም በውል ለይቶ አለማስቀመም ሌላው ነጥብ ነው። የልማት ዕርዳታ ፍቱን ሊሆን እንዲችል ምን መልክ መያዝ ይርበታል? ይህ ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ ነው። አንዳንድ ተቺዎች የበዛ ከመንግሥት ለመንግሥት የሚቀርብ ዕርዳታ ስልታዊ ጠቀሜታ ያላችውን መሪዎች መደገፊያ ዘዴ በመሆኑ ጠቀሜታ አልነበረውም የሚል ክርክርም አካሂደዋል። ለዚህ የቀድሞውን የዛኢር አምባገነን ገዢ ሞቡቱ-ሤሤ-ሤኮን እንደ ምሳሌ ለማንሣት ይቻላል። ሞቡቱ ከሥልጣን በተወገዱበት ጊዜ በስዊዝ ባንኮች ያከማቹት ሃብት የአገሪቱን መላ የውጭ ዕዳ ለመክፈል የሚበቃ ነበር።

ሌላው ዓቢይ የትችት ነጥብ ምዕራባውያን መንግሥታት የራሳቸውን ጥቅምና መፍትሄ በሌሎች አገሮች ላይ ሲጭኑ መቆየታችው ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች የምዕራቡ ዓለም የተትረፈረፈ ምርት በድሆች አገሮች መራገፍ የውስጥ አምራቾችን በማዳከም ጥገኝነታቸውን ማጠናከሩም አለ። በአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት መረጃ መሠረት ባለፈው 2006 ዓ.ም. ብቻ በጠቅላላው ከሃብታሞቹ ወደ ድሆቹ አገሮች የፈሰሰው ገንዘብ ከ 100 ሚሊያርድ ዶላር ይበልጣል። አፍሪቃ ባለፉት አርባ ዓመታት ያገኘችው ዕርዳታ ደግሞ ከ 500 ሚሊያርድ ዶላር የማያንስ ነው። ግን ጦርነት፣ በሽታና ረሃብ በሚፈራረቅባት ክፍለ-ዓለም የረባ ስኬት አልታየም። ዛሬ ከሶሥት አንዱ አፍሪቃዊ ከድህነት ዝቅተኛ መስፈርት በታች በአሳዛኝ ሁኔታ ነው የሚኖረው።

የልማት ዕርዳታ ዓላማ ግቡ

የልማት ዕርዳታ ይቅር የሚሉት ኬንያዊው ጀምስ ሺኩዋቲ ፖሊሲው የከፋው ድህነት በመጀመሪያ ደረጃ የንብረትን በመንግሥት መወረስና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ማጠናከሩ አልቀረም። ሺክላቲ እንደሚሉት መንግሥታቱ ገንዘብ የሚያቀርቡት ከበጎ አድራጊነት የተነሣ አይደለም። ዘላቂ ግብና ምክንያት አላቸው። ይህ እርግጥ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ሃቅም ነበር። ዛሬ ደግሞ ግቡ ርዕዮተ-ዓለማዊ አይደለም። ገበዮችንና ጥሬ ሃብትን መቆጣጠር እንጂ! ሺክዋቱ በትችታችው በመንግሥታት ላይ ብቻ አይወሰኑም። ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶችን ጭምር ለራስ ጥቅም የሚነግዱ ናችው ሲሉ ይወቅሳሉ። የአውሮፓ ሕብረት የእርሻ ድጎማ ፖሊሲም እንዲሁ ሌላው የትችታችው ዒላማ ነው።
እርግጥ ብራስልስ ውስጥ ለኬንያው ባለሙያ ትችት ዋጋ ለመስጠት የሚፈልግ የለም። አንድ የአውሮፓው ኮሚሢዮን ቃል-አቀባይ የሰጠው ምላሽ በጥሩ ሁኔታ የሚራመድ የልማት ዕርዳታ ተቀባዮቹን አገሮች ሊጠቅም፤ ከዚያም አልፎ በጎ አስተዳደርን ሊያስከትልና ሙስናም ሊያስወግድም ይችላል የሚል ነው። እዚህ ላይ እርግጥ ቃልና ተግባር አንድ ሆነው አይገኙም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በጎ አስተዳደርንና የሙስናን መወገድ የዕርዳታ ቅድመ-ግዴታ አድርገው ማስቀመጣችው ባይቀርም ይህ ገቢር የሆነበት ጊዜ እጅግ ጥቂት ነው። ዛሬ በአፍሪቃ አንዳንዶቹ አብዛኛውን የልማት ዕርዳታ የሚቀበሉት አገሮች ለዴሞክራሲና ለበጎ አስተዳደር ባዕድ የሆኑ፤ ሰብዓዊ መብቶችን በመጣስ የሚወቀሱ መሆናቸው የተሰወረ ነገር አይደለም።

ሃቁ ይህ ሲሆን የልማት ዕርዳታው ፖሊሲ ለመብቶች መረጋገጥ በተግባር የቆመ፤ የሚፈሰው ገንዘብም በጥቂቶች ሳይመዘበር ለሕዝብ ማሕበራዊ ዕድገት ለመዋሉ ዋስትና የሚሰጥ ልሆን ይገባዋል። የልማት ዕርዳታው በተገቢ መልክ ሥራ ላይ ውሏል ሊባል የሚችለው ይህ ሲሆን ብቻ ነው። በሌላ በኩል ጀምስ ሺኩዋቲ እንደሚጠይቁት ዕርዳታውን ጨርሶ ማቆሙ ተገቢ መሆኑ በመጠኑም ቢሆን ያጠያይቃል።