1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐማስ-እስራኤል ፍጥጫና መካከለኛዉ ምስራቅ

ዓርብ፣ ጥር 15 2001

የእስራኤል ዛቻ ማየል፥ የሐማስ ደባ መቀጠል እምነት ተስፋዉን መና እንዳያስቀረዉ ያሰጋል

https://p.dw.com/p/Gezg
እሳቱ-ለዘላቂዉ ይጠፋ ይሆን?ምስል picture alliance / landov

እስራኤልና ሐማስ ካለፈዉ እሁድ ጀምሮ በየፊናቸዉ ያደረጉት የተኩስ አቁም ጋዛን መልሶ ለመገንባትና የግዛቲቱን ሕዝብ ስቃይ ለማቃለል እንደሚረዳ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ሰላም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ ማስታወቃቸዉ ደግሞ ተኩስ አቁሙ ወደ ዘላቂ ሰላም ይቀየራል የሚል ተስፋ ማጫሩ አልቀረም።የእስራኤል ዛቻ ማየል፥ የሐማስ ደባ መቀጠል እምነት ተስፋዉን መና እንዳያስቀረዉ ያሰጋል።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።


ጋዛን ያወደመዉ ድብደባ ከቆመበት ካለፈዉ እሁድ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥የአዉሮጳ ሕብረት፥የአረብ ሊግና የሌሎችም ጥሪ፥ጥያቄና የዲፕሎማሲ ዉጣ ዉረድ ተኩስ አቁሙ ዳር ባይዘልቅ እንዲፀና ለማድረግ ነዉ።

ተኩስ አቁሙ ፋይዳ የጋዛ ነዋሪዎችን ከመገደል፥ ከመቁሰል፥ ከመሸበር ከማዳን ባለፍ መድሐኒት፥ እሕል ዉሐ እንዲረዱ፥ የጠፋ-መኖሪያ መስሪያቸዉን ለመጠገን መሰረት መሆኑም ጭምር ነዉ።አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድራቸዉ በመካከለኛዉ መስራቅ ሠላም ለማዉረድ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ትናንት ማስታወቃቸዉ ደግሞ ለንቋሳዉ ተኩስ አቁም ሕይወትን ከማትረፍ ባለፍ ለዛላቂ ሰላም የሩቅ ተስፋ ሆኗል።
ድምፅ

«በየዋሕ እስራኤላዉያን ላይ ያነጣጠረዉ የአሸባሪዎች የሮኬት ጥቃት ሊታገሱት የማይገባ የመሆኑን ያሕል፥ፍልስጤሞችን ተስፋ የሌለዉ መፃኤ ሕወትን እንዲገፉ ማድረግም አይቻልም።»


የኦባማ መልዕክት የሚኖረዉ ተቀባይነት ወደፊት የሚታይ ነዉ።የኒዮርክ፥ የብራስልስ፥ የካይሮዉ ፖለቲከኛ-ዲፕሎማቶች ተኩስ ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ያደረጉት ጥያቄ-ጥሪ ግን እስራኤል የዘጋችዉን የጋዛ ሰርጥ መተለላለፊያዎች ሙሉ በሙሉ እንድትከፍት ሊያሳምናት አልቻለም።የእስራኤል ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሐማስ በድብቅ የጦር መሳሪያ ላለማስገባቱ ማረጋገጪያ ካለገኙ በስተቀር ከና ወደጋዛ ሸቀጥና ሰዎች መግባት መዉጣት አይችሉም።

በዚሕም ምክንያት በቦምብ-አረር ከማረር ተንፈስ ያለዉ የጋዛ ነዋሪ ከዉጪ ከሚሰፈርለት እርዳታ ሌላ-የሚፈለገዉን ሸቀጥ-ጉርሱን ለማግኘት በምድር ዉስጥ-መተላለፊያዎችን መጠቀም ግድ እየሆነበት ነዉ።

የእስራኤል ጦር ከሰማይ፥ ከምድር፥ ከባሕር ለሃያ-ሁለት ቀናት ባወረደዉ እሳት ካጠፋዉ ሕይወት አካል ሌላ ቤት-ሕንፃዎችን፥ መሳጂዶችን፥ ትምሕርት ቤቶችን አጋይቷል።ግብፅን ከጋዛ ጋር የሚያገናኙትን የዋሻ-መንገዶች ያክል የቀጠቀጠ ግን አልነበረም።ዋሾቹ ድብደባዉ በቆመ በዕለታት ልዩነት እንደገና አገልግሎት መስጠት መጀመራቸዉ ነዉ-ጉዱ።ከዋሻዎቹ ሰራተኞች አንዱ።
ድምፅ

«ሌላ ሥራ የለም።ሌላ አማራጭ የለንም።እነሱ ድንበሩን አይከፍቱትም።ሰዎች በዚሕ ዋሻ እንዲደሩ የሚገደዱት በድንበሩ መዘጋት ምክንያት ይሕ ነዉ።»

ዋሻዉ-የሩቁ ከሚያስበዉ በላይ ጠንካራ-ብዙም ነዉ።ከራፋ ተነስቶ ግብፅ የሚወጣዉ አንዱ-ከምድር በታች አስራ-አምስት ሚትር ጥልቅ ነዉ።ብዙ መቶ ሜትሮች ይረዝማል።አንዳድ ስፍራ በጠንካራ-ጣዉላ ተለብጧል።አንዳዱን የእስራኤል ጦር ያወረደዉ ቦምብ አልደፈረዉም።በነዚሕ ዋሾች ነዉ-ከምግብ፥ አልባሳት እስከ ከብቶች፥ ከሞተር ብስክሌት፥ እስከ ጦር መሳሪያ ወደ ጋዛ የሚንቆረቆረዉ።

በእስራኤል ጥቃት የተጎዳዉን ሕዝብ ለመርዳት የቆረጡ አንድ ጀርመናዊ ሐኪም ወደ ጋዛ ሾልከዉ የገቡትም ከነዚሕ ዋሾች ባንደኛዉ ነበር።የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን ዋሻዎቹ-የእግዳዉ ዉጤት መሆናቸዉን እየቀበሉም።ተቃራናዊን እንጂ። ቃል አቀባይ ማርክ ኤጌቭ እንደሚሉት መተላለፊያ ዋሻዎቹ ሐማስ ለጦር መሳሪያ ማስረጊያነት የሰራቸዉ-ናቸዉ።

«ሐማስ የተኩስ አቁሙን እንደሚያደናቅፍ ከመጀመሪያዉ እለት ጀምሮ የታወቀ ነበር።ግልፅና የተለየ ነገር ቢኖር አለም አቀፉ ማሕበረሰብ፥ ዩናይትድ ስቴትስ፥ አዉሮጳ እና የአረብ መንግሥታት በሙሉ የጦር መሳሪያዎች፥ ሚሳዬሎች ከኢራን ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዳይገቡና ሐማስ እንዳይታጠቃቸዉ ለመከላከል መቁረጣቸዉ ነዉ።»

ኢራንም ሆነች ሐማስ ዉንጀላዉን አይቀበሉትም።የእስራኤል ሐማስን እንደገና ለመደብደብ መዛትዋንም አላቆመችም።

Negash Mohammed

Quellen: DW,Reuters,ZPR (Ö-töne)