1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ አስራ አንዱ የሲዳማ ቀጠሮ  

ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 2011

የሲዳማ የለውጥ አራማጆች በመጪው ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የሲዳማ ክልል በይፋ እንዲመሰረት ቀን ቆርጠዋል። ክልሉ ሲቋቋም የሚመራበት ሕገ-መንግሥት እና አደረጃጀት በልሒቃን እና የዞኑ አስተዳደር ጥምረት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/3J3I0
Äthiopien, Demonstration in Hawassa
ምስል DW/S. Wegayehu

ክልሉ ጥናት እያካሔድኩ ነው ብሏል

ሲዳማ ክልል ይሆን ዘንድ የሚወተውቱ አራማጆች (አክቲቪስቶች) ሕዝበ-ውሳኔ ተካሒዶ የዞኑ ምክር ቤት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ያገኛል የሚል ተስፋቸው የተመናመነ ይመስላል። ከእነዚህ መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ሳሙኤል አለማየሁ ናቸው። 

አቶ ሳሙኤል "ሕዝቡ መንግሥት ሕዝበ-ውሳኔ አካሒዶ ክልሉን እናገኛለን የሚለው ተስፋ ተሟጧል። ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በአደባባይ መፈክር ይዞ በተደጋጋሚ እንደጠየቀ እናንተም ምስክር ናችሁ። መንግሥት ግን ይኸንን ታሪካዊ አጋጣሚ ሕገ-መንግሥቱ እስካልተቀየረ፣ እስካልተሻሻለ ድረስ፣ ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ ሆኖ ምን አልባት ባለው አንድ ወር ከምናምን የሚያስፈፅም ከሆነ ያ የመንግሥት አቋም ይሆናል። ሕዝቡ ግን ተስፋ የለውም። ሕዝቡ ተስፋው ራሱ ሕዝቡ ብቻ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ። 

Hawassa Äthiopien Frauen-Marsch
ምስል DW/S. Wegayehu

የሲዳማ አራማጆች የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መስተዳድር የሲዳማ ዞን ያቀረበውን የክልልነት ጥያቄ ለማስፈጸም "ቸልተኛ ሆኗል" ሲሉ ይተቻሉ። የሲዳማ ዞንን ጥያቄ የተቀበለው የክልሉ ምክር ቤት ግን ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሔድ የወሰነው ጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔደው መደበኛ ጉባኤው ነበር። ምክር ቤቱ ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤም ሕዝበ-ውሳኔው እንዲካሔድ በይፋ ጠይቋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔ ጥያቄ ለመስሪያ ቤታቸው መድረሱን አረጋግጠዋል። የሕዝበ ውሳኔው መካሄድ "የቦርዱን መሟላት የሚጠብቅ ጉዳይ ነው" ሲሉም ተናግረዋል። 

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ክልል የመሆን ጥያቄ ያቅርብ እንጂ እስካሁን በዞኑ አስተዳደር ደረጃ ሕዝበ-ውሳኔ ለማካሔድ ዝግጅት ስለመኖሩ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም። በሲዳማ ልሒቃን ዘንድ ግን ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ክልሉ በይፋ የሚመሰረትበት ቀጠሮ ሆኗል። በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና ተመራማሪው አቶ ፍላታ ጂግሶ እንደሚሉት በተመረጠው ቀን የሲዳማ ክልልን ለመመሥረት ሕጋዊ መሰረት አለ። አቶ ፍላታ "የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ይኸንን ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ ተቀብሎ ያስተናገደው ሐምሌ 10 ቀን 2010 ነበር። ሕገ-መንግሥቱ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ-ውሳኔ መካሔድ አለበት ነው የሚለው። ሕዝበ-ውሳኔ ካልተካሔደ ግን የመብት ጥያቄ እንደመሆኑ፤ ሕዝበ-ውሳኔ እንደ procedure ስለሚወሰድ እና መብቱን ለመገደብ ስለማይችል፤ ሲዳማ በ2010 ጥያቄውን ተቀብሎ በወሰነ ጊዜ ሕገ-መንግሥቱ ባስቀመጠው መሠረት እንዲቆይ ተደረገ እንጂ መብቱን ተግባራዊ አድርጓል። ስለዚህ ሕዝበ-ውሳኔ የማካሔድ ዕድላቸውን ካልተጠቀሙ፤ በተለይ የደቡብ ምክር ቤት በዚያ ጉዳይ ገብቶ መሔድ ካልቻለ፤ ያንን መብቱን መጠቀም እንዳልፈለገ ተቆጥሮ ሲዳማ በራሱ ክልል መሆኑን ያውጃል" ሲሉ ይገልጻሉ። 

የሲዳማ ባለስልጣናት ጭምር የሚገኙበት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት እና ክልሉን የሚያስተዳድረው ደኢሕዴን ክልል ለመሆን የቀረቡ የዞኖች ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥናት በማካሔድ ላይ ናቸው። ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ዛሬ ደቡብ ተብሎ የሚጠራውን እና የከረረ ተቃውሞ የቀረበበትን ክልል በአምስት አዳዲስ ክልሎች መልሶ የማዋቀር ሐሳብ መቅረቡን ይገልፃሉ። የደኢሕዴን እና የክልሉ መንግሥት ጥናት ተጠናቅቆ ሕዝበ ውሳኔ ተካሔደም አልተካሔደ የሲዳማ ልሒቃን የራሳቸውን ክልል ለመመስረት በዝግጅት ላይ ናቸው።

Neujahrsfest der Sidama
ምስል ARCCH

አቶ ፍላታ ጂግሶ "ዞኑ ወደ ክልል ካደገ በኋላ የሚኖረው አደረጃጀት ተሰርቶ አልቋል። ሕገ-መንግሥቱ ተሰርቶ አልቋል። ሕጎች በተለይ የሥራ አስፈፃሚ፤ ፍርድ ቤት እና እንደዚሁም የምክር ቤቱን ደንብ የሚመለከቱ ሕግጋትም እየተሰሩ ነው። ያ ጊዜ ከመድረሱ በፊት የሚያልቅ ነው የሚሆነው። ክልል ከተሆነ በኋላ በነጋታው መሰራት ያለበት ማኅበረ-ኤኮኖሚያዊ ሥራዎችም ጥናት ተደርገው ዛሬ [ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም.] ሪፖርት ተደርጓል። ሌላው ክልል ሲኮን የሚዲያ ሽግግር ያስፈልጋል በሚል የሚዲያው ዘርፍ ላይም ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ነበር። እሱም ዛሬ ሪፖርት ተደርጓል። ሥራዎች በሙሉ እየተጠናቀቁ ነው" ብለዋል። 

እስከ መጪው ሐምሌ 11 ቀን ድረስ በሲዳማ ዞን ምክር ቤት የተጠየቀው ሕዝበ-ውሳኔ ካልተካሔደ ምን ይፈጠራል? አቶ ፍላታ የኢትዮጵያ መንግሥት በዕለቱ "ውሳኔውን በይሁንታ ሊቀበል ይገባል" የሚል ሐሳብ አላቸው። አለበለዚያ ግን ሊፈጠር የሚችለው ነገር ያሰጋቸዋል።
"የመንግሥት ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል አናውቅም። ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ መሆን ያለበት ግን የሲዳማ ሕዝብ ሲያውጅ መቀበል ነው። ከዚህ አልፎ የሚሄድ ከሆነ የሚፈጠረው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው። ሰዉ መብቱን አትጠቀምም ሲባል እሺ ብሎ ወደ ቤት አይገባም። ያኔ የሚፈጠረው ነገር በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል" የሚሉት አቶ ፍላታ ናቸው። 
አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አሳይቷል የሚሉትን ቸልተኝነት እየጠቀሱ "ሲዳማ ክልል እንዲሆን አይፈልግም" ከሚል ድምዳሜ ደርሰዋል። የሲዳማ ሕዝብ ያቀረበው "የዳቦ ጥያቄ አይደለም" የሚሉት አቶ ሳሙኤል የሐምሌ አስራ አንዱ ቀጠሮ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል "ግብግብ" ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ይናገራሉ። 
አቶ ሳሙኤል "የማንነት ጥያቄ ስታውጅ ማወጅን የሚከላከል አካል ሊኖር ይችላል። ይኸንን በራስ መከላከል (Self-defense) የምትቋቋመው ይሆናል። አላስፈላጊ ውጥረቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። መንግሥት እስካሁን ድረስ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄውን በሕገ-መንግሥት መሰረት እንዳይመለስ ያጓተተው በራሱ ምክንያት ነው። ይኸ ማለት ሲዳማ ክልል እንዲሆን መንግሥት አይፈልግም ማለት ነው። ስለዚህ የዛኔ በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል። ይኸ ጥያቄም የማያስፈልገው ይሆናል። ከዚህ ውጪ አላስፈላጊ ግብግብ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል የሚፈጠር ይሆናል ማለት ነው" ብለዋል። 

Hawassa Äthiopien Frauen-Marsch
ምስል DW/S. Wegayehu

የክልሉ መንግሥት የሚያካሒደው ጥናት የሲዳማ እና የወላይታን ጨምሮ ክልል የመሆን ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖችን ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል። በጥናቱ መሠረት ተግባራዊ የሚሆነው አዲስ ክልላዊ አወቃቀር ተጨማሪ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ ጥያቄዎች እንደሚገጥሙት ይጠበቃል። 

እሸቴ በቀለ
ተስፋለም ወልደየስ