1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐረሪ ክልል ግብር ከፋዮች ቅሬታ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2011

የሐረሪ ክልል በያዝነው የበጀት ዓመት በወቅቱ ግብር አልከፈሉም ያላቸውን ነጋዴዎች ግብር ለማስከፈል እና ሌሎች ከግብር ስርዓቱ ውጭ ይንቀሳቀሳሉ ያላቸውን ደግሞ ወደ ግብር ከፋይነት ለማምጣት ይረዳል ያለውን ዘመቻ እያከናወነ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/3HMTE
Hyänen Äthiopien
ምስል Reuters/T.Negeri

ግብር ከፋዮች በሐረሪ ክልል ቅሬታ እያሰሙ ነው

የግብር ተመን እና የክፍያ ሁኔታ በኢትዮጵያ በከፋዩም በአስከፋዩም ዘንድ በየጊዜው ለንትርክ የሚዳርግ ጉዳይ ነው። ግብር ከፋዩ መንግሥት የሚጥለው ግብር አግባብነት የሌለው ነው እያሉ ሲያማርሩ፤ መንግሥት በበኩሉ በርካታ ነጋዴዎች ግብር የመክፈል ግዴታቸውን እየተወጡ አይደሉም ሲል ይወቅሳል። በወቀሳም ብቻ አያልፍም ርምጃ ሲወስድ ይስተዋላል። በሐረሪ ክልልም መንግሥት ግብር ለማስከፈል ዘመቻ ጀምሯል። ዘመቻው አንዳንድ ነጋዴዎች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል።

የሐረሪ ክልል በያዝነው የበጀት ዓመት በወቅቱ ግብር አልከፈሉም ያላቸውን ነጋዴዎች ግብር ለማስከፈል እና ሌሎች ከግብር ስርዓቱ ውጭ ይንቀሳቀሳሉ ያላቸውን ደግሞ ወደ ግብር ከፋይነት ለማምጣት ይረዳል ያለውን ዘመቻ እያከናወነ ነው፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግብር ከፋዮች ግን ባለሥልጣን መ/ቤቱ በሚጥለው የግብር መጠን እና አሠራር ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ በከተማው በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከሚገኙ ነጋዴዎች ለDW አስተያየት ከሰጡት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኃይሉ ካሳ የክልሉ ገቢዎች ባለሥልጣን የግብር አገማመቱ እና የአሰራር ተገቢነት ላይ ያለውን ቅሬታ ገልፀዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡት እኝህ በከተማው ሆቴል ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ሰሞኑን የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ባዘጋጀው መድረክ በምስጉን ግብር ከፋይነት የምስክር ወረቀት ሸልማቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በባለሥልጣን መ/ቤቱ አሰራር ላይ አድሎአዊነት ስለመኖሩ ይናገራሉ፡፡ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን የገቢ አሰባሰብና ክትትል ዋና ዳይሬክተር  አቶ አብዱልአዚዝ ሱፊያን ከገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልፀው ቅሬታ በየደረጃው የሚታይበት አሰራር መኖሩን አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል የሀረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ በወቅቱ ግብር አልከፈሉም ያላቸውን ነጋዴዎች ግብር ለማስከፈል እና ሌሎች ከግብር ስርዓቱ ውጭ ይንቀሳቀሳሉ ያላቸውን ደግሞ ወደ ግብር ከፋይነት ለማምጣት ይረዳል ያለውን ዘመቻ እያከናወነ ሲሆን በዚህም ከአንድ ሺህ ሶስት መቶ በላይ ያለፈቃድ ይሰሩ ነበር ባላቸው በየደረጃው ያሉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡ በንግድ ድርጅቶቹ ላይ ስለተወሰደው እርምጃ ያነጋገርናቸው አቶ አብዱልአዚዝ እርምጃው ህግን መሰረት አድርጎ የተካሄደ መሆኑንና በዚህም አብዛኞቹ ወደ ህጋዊነት መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

Markt Harar Äthiopien
ምስል Azeb Tadesse Hahn

በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ እየተከሰቱ ያሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን እያስተናገደች ባለችው ሀረር ለክልሉ ግብር መክፈል ከነበረባቸው ነጋዴዎች 38 በመቶ  ያህሉ ግብራቸውን መክፈል በነበረባቸው ግዜ ውስጥ አለመክፈላቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህንኑ በሚመለከት የባለስልጣኑ የገቢ አሰባሰብና ክትትል ዋና ዳይሬክተር  አቶ አብዱልአዚዝ ወቅታዊ ችግሮች በግብር ከፋዩም ሆን በተቋሙ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት በዘንድሮ ግብር አሰባሰብ ላይ የግብር ከፋዩን ወቅታዊ ሁኔታ በአግባቡ ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አሁንም የጀመረውን የግብር ገቢን የማሳደግ ስራ አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን እየተናገረ ባለባት ሀረር ህገወጥ ንግድና በህጋዊ ንግድም ቢሆን ህጋዊ ደረሰኝ ያለመስጠትና ያለመቀበል ችግሮች እንዳሉ ናቸው፡፡


መሳይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ