የሐዘን መግለጫ ስነ-ስርዓት ለሟች የበረራ ሰራተኞች
ሰኞ፣ መጋቢት 2 2011ማስታወቂያ
የኢትዮጵያ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር አባላት ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ሲበር በተከሰከሰው አውሮፕላን ህይወታቸውን ላጡ ባልደረቦቻቸው እና ተጓዦች ሃዘናቸውን ሲገልጹ ውለዋል፡፡ ሐዘን በተጫነው እና በርካቶች በታደሙበት በዚህ መርሐ ግብር የማህበሩ አባላት የበረራ ሰራተኞችን ሻማ በማብራት አስበዋቸዋል።
በጋራ ለሃዘን የተቀመጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ሁሉንም ሟች ባልደረቦቻቸውን እየጠቀሱ፣ ትጋታቸውን እና ስነምግባራቸውን እያስታወሱ፣ ጥቁር ለብሰው፣ በሃዘን እንባ ሲራጩ ውለዋል። አደጋው እጅግ እንዳሳዛናቸው የተናገሩት እነዚህ የስራ ባልደረቦች ህይወታቸውን ያጡት የበረራ ሰራተኞች "ታታሪዎችና ምስጉን ከመሆናቸው የተነሳ መልካም እና ጠንካራዎቹ ተሰባስበው ሄዱብን" እንዲሉም አድርጓቸዋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ካፒቴን የሽዋስ ጌታሁን በተለይ ዋና አብራሪ የነበረው ካፒቴን ያሬድ ጌታቸው የቅርብ ጓደኛቸው እንደነበሩ እና ዘወትር ማክሰኞና ሐሙስ አብረው ኳስ ይጫወቱ እንደነበር ለDW ተናግረዋል፡፡ አስደንጋጩ አደጋ ባይከሰት ለሀዘን ሳይሆን እንደወትሮው ለኳስ ነበር የምንገናኘው ብለዋል።
በሀዘን መግለጫ ስነ ስርዓቱ ላይ የታደመውን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ሰለሞን ሙጬን ዘገባ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ሰለሞን ሙጬ
ተስፋለም ወልደየስ
እሸቴ በቀለ