1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባና አንደምታው

ረቡዕ፣ ኅዳር 20 2010

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ረዘም ካለ ጊዜ አንስቶ ሲያኪያሄድ በቆየው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው የተወሰኑ የአመራር አባላትን ካሉበት ዝቅ በማድረግ፤ ማስጠንቀቂያ እና ጊዜያዊ እገዳ ማድረጉም ተዘግቧል። ለአንድ ወር ግድም የዘለቀው የሕወሓት ስብሰባ ውሳኔ አንደምታው ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/2oUXF
Äthiopien 40. Jahrestag TPLF
ምስል DW/T. Weldeyes

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት)በማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባው ሁለት የሥራ አስፈጻሚ አባላቱን ካሉበት ዝቅ አድርጎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መሥፍንን ላልተወሰነ ጊዜ ማገዱ ተገልጧል። ከሥራ አስፈጻሚነታቸው ዝቅ እንዲሉ ከተደረጉት መካከል ከሕወሓት ሊቀመንበርነታቸው መነሳታቸው የተነገረላቸው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ወልዱ እና አቶ በየነ ምክሩ ይገኙበታል። የቀድሞው የሕወሓት መስራችና  የአረና ትግራይ ፓርቲ አባል የነበሩት አቶ አሥገደ ገ/ሥላሴ የማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ «ፋይዳ ቢስ ነው» ብለዋል።

አክለው ሲናገሩም፦ «አሁን አባይ ወልዱ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ወረደ፤ ማን ሊተካ ነው? ያው እሱ ነው። እሱ የመለመለመው እታች የነበረው ሆዳም ነው የሚመጣው።  አዜብ መስፍን ታገደች ኋላስ ማን ሊመጣ ነው? ለምን በሙሉ ቢጠራረጉም ለእኔ ለውጥ አይመጣም። መሠረታዊ መፍትኄ ለማምጣት ከሆነ  ከኢሕአዴግ ውጪ የሆኑ ሰዎች  ያሉበት፤ ምሁራን፤ የሕግ ተመራማሪዎች፤ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች፤  ሌሎች የሳይንስ ተመራማሪዎች  ይሰብሰቡ። ይኼ ተገልሎ የቆየ አመለካከቱ ደስ አላለኝም፤ አበላልህ ደስ አላለኝም እየተባለ በየስደቱ የሚሄደው ገብቶ ስለሀገሩ መወያየት አለበት።»

ሕውሓትን ከመሰረቱት 11 ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ አስገደ ውሳኔው፦ «በኢትዮጵያ ለውጥ የመጣ ለማስመሰል» የተደረገ ነውም ይላሉ። የምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ተንታኝ እና ጸሐፊ አቶ ዩሱፍ ያሲን በበኩላቸው አሁን ብዙዎች «ጥገናዊ ለውጥ» የሚሉትን ውሳኔ ከመመልከት ይልቅ «ወሳኙ ወደፊት ያለው ነው» ባይ ናቸዉ። በተለይ ደግሞ የካቲት ወር ላይ የድርጅቱ ጉባኤ በሚደረግበት ጊዜ በውሳኔም ይሁን በሰው ቅያሬ የሚደረገው ለውጥ ይበልጥ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል። 
«ያ ድርጅት ወደ አንድ ድርጅት ማደግ እንዳልቻሉ፤ ይህ ድርጅት ደግሞ ከወታደራዊ ኃይልና ታጋይነት ወደ ፖለቲካዊ ሂደት ያልለወጠበት በአጠቃላይ በሀገሪቷ የሌሎቹ ሁሉ ተሳታፊነትና ዲሞክራሲያዊነት ሁኔታ ያልተፈጠረበት የዛ ሁሉ የተጠራቀመ ቀውስ ነው ዛሬ የሚመጣው። እና ያን ቀውስ በምን ያልፉታል ነው? አሁን ወታደር ጣልቃ ይገባል? ወታደር ጣልቃ ገብቶ ምንድን ነው የሚያደርገው? ምክንያቱም ወታደሩ ራሱ የችግሩ አካል ነው የሕወሓት ወታደር። ጄነራሎቹ ያው የሕወሓት ሰዎች ናቸው። እኔ ከዛ ሰፋ ያለ ነገር ካልመጣ [ጎታች ኃይሎቹ] ይበልጥ ወደ ቀውስ የሚወስዱን ይኾናሉ በጊዜ ካልተገቱ።»

Äthiopien Stadansicht Mek' ele
ምስል DW/Y. G. Egziabhare

አሁን ያለውን ኹኔታ «መገመት ከባድ ነው» ያሉት ደግሞ የቀድሞ የተቃዋሚ ብቸኛው የምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሠይፉ ናቸው። «እየሄድንበት ያለው መንገድ ልክ ነው ይል የነበረው ቡድን አሁን የተሸነፈ ይመስለኛል፤» ሲሉ የሕወሓትን ወቅታዊ አቋም የገለጡት አቶ ግርማ ይህንን በምሳሌ ያብራራሉ።

«ለምሳሌ እኛ ስለሌላው የክልል መንግሥቱ አያገባንም፤ በክልላችን ይህን እናደርጋለን ምናምን የሚለው የዓባይ ወልዱ ቡድን  አለማሸነፉ ያገባናል የሚለው ቡድን እያሸነፈ ነው። ግን ያገባናል የሚለው ቡድን በሁለት ነው የሚቀረው። ሁለቱ ያገባናል የሚሉት ቡድኖች  አያይ በጉልበት ነው አሁንም  የትግራይን የበላይነት አስጠብቀን ነው መቀጠል ያለብን ነው የሚሉት ወይንስ ደግሞ በእኩልነት መንፈስ ሁሉም [የራሱን ድርሻ] የሚያደርግበት ለውጥ ነው የሚሉት። ሁለቱ እንግዲህ ሌላ ግብ ግብ ላይ ያሉ ይመስለኛል።»አቶ ግርማ «እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደሰው፤ ለውጥ እፈልጋለው የሚለው ቡድን ቢያሸንፍ» እንደሚሻልም አክለው ጠቅሰዋል።

አቶ አስገደ ለሁሉም መፍትኄው «ቁርቁስ ቀርቶ እርቅ ነው» በማለት ያስረግጣሉ። «እርቀ ምሕረት ካልመጣ ሕወሓት በሙሉ ቢጠረጉ፤ ብአዴን ቢጠረግ፤ ኦህዴድ ቢጠረግ እኔ ትርጉም የሚያመጡ አይመስለኝም። አሁን ይኼ አርቲፊሻል ግለ-ሂስና ከሥልጣን መውረድ ብአዴንም  እንደዚህ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ። በኦህዴድም ሊቀጥል ነው፤ በሌሎች አጋሮችም ሊቀጥል ነው። ዋና ነገር የዚህ ሀገር ጠንቅ ሆኖ ያለው የሰብአዊ መብት ጉዳይ፤ የፍትኅ ጉዳይ፤ የሕግ የበላይነት ጉዳይ፤ የሀገሪቷ ሀብት የምዝበራ ጉዳይ ነው። ስለዚህ እነዚህ ይህን ያደረጉ ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው። እና በዚህ ለውጥ ይመጣል የሚል ግምት የለኝም።»

ለአንድ ወር ግድም ስብሰባ እና ግምገማ ላይ የሚገኘው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወደፊት ምን አይነት ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ እና እሱን ተከትሎም ምን ሊመጣ እንደሚችል በውል የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ግን አስተያየት ሰጪዎቹ ሁሉ ያሰመሩበት ጉዳይ ነዉ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ