1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕወሓት ውሳኔና ባርነት በሊቢያ

ዓርብ፣ ኅዳር 22 2010

ሊቢያ ውስጥ አፍሪቃውያን ስደተኞች ለባርነት እየተሸጡ መሆኑን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ከታየ ወዲህ በበርካቶች ዘንድ ቁጣው አይሏል። ሕዝባዊ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በተራዘመ ስብሰባና ግምገማው ማብቂያ ላይ የተወሰኑ የአመራር ለውጦችን ማድረጉም ተገልጧል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/2ocpG
Migranten aus Westafrika Symbolbild Menschenhandel
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

በሊቢያ በረሀ የአፍሪቃውያኑ ስደተኞች ሰቆቃ አሁንም ያስተጋባል። ሊታመን በማይችል መልኩ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪቃውያኑ በአፍሪቃ ምድር ይሸጣሉ፣ ይለወጣሉ፣ ይመዘበራሉ፣ ይደፈራሉ፣ ይገረፋሉ፤ ብሎም ይገደላሉ። ነገሩ አዲስ ባይሆንም፦ አፍሪቃውያኑ ሊቢያ ውስጥ ለባርነት በገንዘብ ሲሸጡ የሚያሳየው ቪዲዮ ከተሰራጨ ወዲህ ግን ቁጣው ከጥግ እስከ ጥግ አስተጋብቷል። የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት መሰናዶዋችን ትኩረት ነው። ሕዝባዊ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) በተራዘመ ስብሰባውና ግምገማው ማብቂያ ዶ/ር ደብረ ጽዮንን ሊቀመንበሩ፤ የተወሰኑትን ከፍተኛ አመራሩንም ከፍ እና ዝቅ አድርጎ ተጠናቋል። 

ሊቢያ፤ የሰቆቃ ምድር። የሰው ልጅ ገላው የሚተለተልበት፤ በባርነት የሚሸጥበት፤ ብሎም እንደዘበት ሕይወቱ የሚቀጠፍባት ሀገር። ዛሬ ይህ ጉድ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መውጣቱ ይበልጥ ትኩረት ሳበ እንጂ ሰቆቃው ለዓመታት የዘለቀ መሆኑን የኖሩበት ይናገራሉ። ሊቢያ ውስጥ በባርነት ተሽጦ ጀርመን እንደመጣ የገለጠልን አድማጫችን በሊቢያ ስለተመለከተው ግፍ በድምፁ እያብራራ በዋትስአፕ የቀርጸውን መልእክት ልኮልናል።
 
ከሊኮ ስማርት በሊቢያ የሚከሰተውን እንግልት አስመልክቶ በፌስቡክ ገጹ ስጋቱን እንዲህ ገልጧል። «እህ!!!! ሊቢያ…የአፍሪቃዊያን እዳ… ባርነት የባሪያ ንግድ ስርዓት በሊቢያ ተጀምሯል። በዛ በኩል መሄድ አሁን ከምን ጊዜውም የበለጠ እሳት ላይ መጣድ ነው።»

ዜድ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ ያቀረበው ጽሑፍ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ «የአፍሪቃ የመጀመሪያው ቦይንግ 787-9 አውሮፕላን ኮናክሬ፤ ጊኒ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት» ሲል ይነበባል። የአየር መንገዱ ከበረራ ሠራተኞቹ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚታይበት ፎቶግራፍም ተያይዞ ተለጥፏል። የዜድ መልእክት እንዲህ ይነበባል። «አስጠላችሁኝ፤ እስቲ ኤርላይንስ እራሱ ሊቢያ የሚገኙ ወገኖችን ይመልስ። በሳሙኤል ኤቶ ይህን ያኽል ሲመለስ እንዴት አንድ መንግሥት ህዝቡን መታደግ ያቅተዋል? ተዋጉ ካላቹሁንም እንዋጋ አይደለም ሊቢያ ሌላም እንገባለን እኛ ኢትዮጵያውያን።» ብሏል። 

አፍሪቃዊው የእግር ኳስ ፈርጥ ሳሙኤል ኤቶ ከሊቢያ ካሜሩናውያን ስደተኞችን አስወጣ የሚል መልእክት ቀደም ሲል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲንሸራሸር ቆይቶ ነበር። ሳሙኤል ኤቶ ከስደት ለተመለሱ 250 ካሜሩናውያን 1,5 ሚሊዮን ፍራንክ ለግሷል የሚል መልእክትም በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭቷል።  

Tschad  Migranten auf Trucks
ምስል picture alliance/dpa/D. v. Trotha

የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን፤ የቸልሲ፣ የኢንተር ሚላን እና የባርሴሎና አጥቂ የነበረው ሳሙኤል ኤቶ ማኅበራዊ መገናኛዎቹ ለስደት ተመላሾቹ ገንዘብ ሰጠ ሲሉ የሚያወሩት ስህተት መሆኑን በፌስቡክ ገጹ ተናግሯል። ለአንድም ከስደት ተመላሽ የአውሮፕላን ቲኬት እንዳልከፈለም በገጹ ላይ ገልጧል። ይልቁንም «ባልተጨበጡ ወሬዎች» ተጠምዶ ጊዜን ከማባከን «ሌሎች ወንድሞቻችን ክብራቸውን አጥተው መዋረዳቸውን እናስቁም» ሲል መረጃዉን ያሰራጩትን ድረ-ገጾች ተማጽኗል። 

ሳሙኤል ኤቶ ካሜሩናውያኑን ከሊቢያ አስወጣ በሚል በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨው ፎቶግራፍ ጥቁር ስደተኞች አውሮፕላን ውስጥ ተቀምጠው ይታዩበታል። ሆኖም ይህ ፎቶግራፍ ከ21 ወራት በፊት የቡርኪና ፋሶ ስደተኞች ከሊቢያ ሲመለሱ የተነሱት መሆኑን ቢቢሲ በድረገጹ ምንጩን ጠቅሶ ዘግቧል። የተጠቀሰው ምንጭ በእርግጥም ፎቶግራፉ ራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ያቀረበው ዘገባ ውስጥ የተካተተ ሲሆን፤  ኢንተርኔት ላይ ከሰፈረም አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት አስቆጥሯል።

ስለ ሊቢያ የአፍሪቃውያኑ የባርነት ሰቆቃ «አፍሪቃ ኢዝ ኤ ከንትሪ» በሚል የትዊተር አድራሻ የቀረበው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ፦ «ኧረ ለመሆኑ ሰዎች ሊቢያ ውስጥ ዘረኝነት ስለመኖሩ ድንገት አሁን እንዴት ተከሰተላቸው?» ሲል ዘርዘር ያለ ጽሑፍ አስፍሯል። ከመልእክቱ ጋር በማገናኛ የተያያዘው ዝርዝር ጽሑፍ በሊቢያ የአፍሪቃውያኑ እንግልት የጀመረው ከቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ መወገድ አንስቶ መሆኑን ያትታል። 

ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በአገዛዝ ዘመናቸው የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለማፈን ከተጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል የምዕራብ አፍሪቃ ጥቁር ቅጥረኛ ወታደሮችን ማሰማራት ነበር። ኮሎኔሉ ከተሸሸጉበት ጉድባ ውስጥ ተጎትተው ከወጡና ከተገደሉ በኋላ በጥቁሮች ላይ ጥላቻ እና በቀሉ እየተስፋፋ መምጣቱንም ጽሑፉ ያብራራል።

አብዱርሀማን ሑሴን በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «ለዚህ ሁሉ መንስዔው ጋዳፊን ከሥልጣን ያወረዱ አገሮች ናቸው። ለሊቢያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሰርአት አናመጣለን ብለው አሁን አንደምናየው ባርነትን አመጡ። ሰለዚህ በዋናነት የሚጠየቁት አሜሪካ እና ተባባሪዎቿ ናቸው።» ብሏል።

አምሶን ሐጋን በተባለ ጸሐፊ የቀረበና ፌስቡክ ላይ የሰፈረ ጽሑፍ ደግሞ የጥቁሮች ጥላቻ በሊቢያ ብቻ አይደለም ይላል። እንደ ሊቢያው ብዙም ባይነገርለትም አልጀሪያ የሚገኙ የሰሜን አፍሪቃ ዓረቦችም ጥቁር አፍሪቃውያን ላይ ጥላቻና ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ጠቅሷል። 

Libyen Flüchtlinge in Sabratha
ምስል Reuters/H. Amara

ጽሑፉ «የአልጀሪያ የቀይ ጨረቃ ፕሬዚዳንት ሳይዳ ቤንሃቢለስ መጤ ጠል ቅስቀሳ በአንድ የአልጄሪያ ጋዜጣ ተናግረዋል።» ሲል አስነብቧል። አልጄሪያዊቷ ወይዘሮ በጋዜጣው  «የአፍሪቃውያኑ ፈላሲያን እና ስደተኞች በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች መንሰራፋታቸው ለአልጄሪያውያን ችግር ያመጣል። ግልጽ የሆነው ችግር ደግሞ ኤድስና ሌሎች ተዛማች በሽታዎች ናቸው። በሀገራችን ከባድ ጥፋት ከመድረሱ በፊት የአልጄሪያ ባለሥልጣናት እነዚህ ስደተኞች ወደመጡበት ሊያባርሩልን ይገባል።» ብለዉ ቅስቀሳ አድርገዋል ሲልም ይጠቅሳል። ይባስ ብሎም ጥቁሮችን ከአልጀሪያ ለማባረር በማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፉ ትዊተር ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ተከፍቶ ነበር። በሀሽታግ የሚንደረደረው ቅስቀሳ «አልጀሪያ ለጥቁሮች  እምቢ ትበል።» ይላል። መሰል ቅስቀሳዎች ባባሱት ጥላቻ አልጀሪያ ውስጥ በርካታ ጥቁር አፍሪቃውያን በቁጣ በተሰባሰቡ አልጀሪያውያን መገደላቸውና መቁሰላቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል። 

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ረቡዕ ዕለት ማምሻውን ሲጠናቀቅ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤልን ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ፤ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔርን ምክትል ሊቀመንበር ማድረጉ ተገልጧል። ሌሎች አራት ሰዎች ወደ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት መግባታቸውም ተጠቅሷል።  

ባራኪ ዮሐንስ በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፦ ሕወሓት ፖሊት ቢሮ ላይ ያደረገው ለውጥ በዋናነት አንድ አካባቢ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል። ባራኪ ዘጠኝ የፖሊት ቢሮ አባላት የመጡበት አካባቢን በእንግሊዝኛ በመዘርዘር «የአድዋ የበላይነት» መስፈኑን ጠቅሷል። ማኅሌት በላቸው ደግሞ በትዊተር ጽሑፏ፦ «ህወሀት፣ 'ለተከሰተው ችግር ኃላፊነቱን እንወስዳለን ...'ብሎ በቃ ዝም... ኃላፊነት የወሰደ እኮ ሥልጣን ይለቃል፤ ይባረራል፤ ይታሰራል ... ይቀጣል ...» ብላለች።

«የህወሃት እርስ በርስ መፋተግ ሊትዮጵያ ህዝብ የሚያመጣው ነገር የለም! ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት መሰረታዊ ለውጥ ነው።» የሚል አጠር ያለ አስተያየት የሰጠው ደግሞ ራቢያ ሮባ ጃርሶ ነው፤ በፌስቡክ። «መጀመሪያውም መጨረሻውም አምባገነንነት እኛ ከሌለን ሁሉም አይኖርም ወይም ሁሉም መኖር የለበትም ፖለቲክስ» የሳሃ ዓለሙ የፌስቡክ አስተያየት ነው። 

አብዱርሃማን ደጉ ደግሞ፦ «እኔ እደሚመስለኝ የሰው መቀያየር ምንም ዋጋ የለውም፤ ዋናው መቀየር ያለበት የድርጅቱ አላማ ነው ስለአንዲት ኢትዯጵያ ቢያስቡ ጥሩ ነው» ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። 
ዘርይሁን‏ በትዊተር ባሰፈረው ጽሑፉ፦ ሕወሓት «በኢትዮጵያ እና በትግራይ ደረጃ ሥልጣን እና ፖለቲካው ላይ ከመደራደር» ይልቅ ውሳኔው «ከተጠያቂነት እና የምር ለውጥ» ከመሻት ውጪ መኾኑን ጠቅሷል። ኤዶም ካሣዬ፦«ንቅዘት በሕወሓት ውስጥ ተባብሷል» ስትል «ኢትዮጵያ» የሚለውን ቃል በሀሽታግ እና በጥያቄ አያይዛ ትዊተር ላይ ጽፋለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ