1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዝብ አመፅ በትያትር መድረክ

ሐሙስ፣ ሰኔ 25 2007

በቀድሞው የራድዮ ጣብያችን መቀመጫ በኮሎኝ ከተማ ለአስር ቀናት የአፍሪቃ ትያትር ፊልም እና ሙዚቃ ትርኢት ተካሂዶአል። ባለፈዉ ሳምንት መጠናቀቅያ ላይ ባበቃዉ በዚህ ትርኢት የአፍሪቃ ሃገራት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚያንፀባርቁ አጫጭር ቲያትሮችና የሙዚቃ ድግስ ለታዳሚዉ ቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/1FrMp
Africologne Durchwachte Nacht in Ouagadougou
ምስል Africologne


በነዚህ ኪነ-ጥበባዊ የመድረክ ላይ ሥራዎች አፍሪቃዉያኑ ሃገራት ማኅበረሰቡ የሚተገብራቸዉ እለታዊ ክንዉኖችና ፖለቲካዊ ለዉጦች ተንጸፀባርቀዋል። ለምሳሌ በመድረክ ከቀረቡ ትያትሮች መካከል በቡርኪናፋሶ ለዘመናት የፕሬዚዳንት መንበሩን ተቆናጠዉ ይዘዉ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኮምፓዎሪ የቡርኪናፋሶ ሕዝብ ስልጣኑን ለቀዉ እንዲነሱ እንዴት ጫና እንዳሳደረ የሚገልፅ ትያትር በመድረኩ ቀርቦ ነበር። የዶቼ ቬለ የፈረንሳይ ቋንቋ ስርጭት ክፍል ባልደረባ አዉደ ጀንስቢትል በስፍራዉ ላይ ተገኝታ ዘገባ አጠናቅራለች በእለቱ ዝግጅታችን አፍሪኮለኝ ስለተባለዉ በኮለን ከተማ ስለተካሄደዊ የአፍሪቃ የኪነ-ጥበብ ድግስ እንቃኛለን ።
« አሁን ተቆጣጥረን እንይዛለን፤ የህዝብን አመፅና ቁጣ ይገልፃል። ጩኸት ትግል ይታያል። ለረጅም ጊዜ አደባባይ ቆሞ የነበረዉ የባለሥልጣኑን ገፅ የሚያሳየዉ ሃዉልትም ተገረሰሰ። በሌላ ወገን ወላጆች በዚህ ብጥብጥ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩዋቸዉን የልጆቻቸዉን አስክሬን ከወደቀበት መሬት ሲያነሱም ይታያል።» ይህ ሁሉ ባለፈዉ ዓመት በቡርኪና ፋሶ ጎዳናዎች ላይ ይታይ የነበረ ነባራዊ ሁኔታ ነዉ። ዛሬ ደግሞ ይህ በትያትር መልክ መድረክ ላይ «እንቅልፍ አልባዉ ለሊት በዋጋዱጉ» ተብሎ ቀርቦአል።»
« እንቅልፍ አልባዉ ለሊት በዋጋዱጉ » በተሰኘ የቡርኪናፋሶ ተወላጆች ባለፈዉ ሳምንት በተጠቃለዉ አፍሪኮለኝ የኪነ-ጥበብ ትርዚት ላይ ላይ መድረክ ላይ የቀረበ አጠር ያለ ተዉኔታዊ ሙዚቃ ነበር። በራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ በስሞስኪ ሙዚቃ አፍሪቃዉያኑ ዉዝዋዜ ዳንሳቸዉን ለተመልካች አሳይተዋል። ሙዚቀኛ ስሞስኪ በሚያቀነቅናቸዉ ሙዚቃዎቹ በተለይ ሙስናና ማኅበረሰባዊ ችግሮች መፍትሄ እንዲገኝላቸዉ ያዜማል፤ ከእንቅልፋችን መንቃት አለብን ሲልም ጥሪዉን አሰምቶአል። ሙዚቀኛ ስሞስኪ ባለፈዉ ዓመት ፕሬዚዳንት ኮምፖኦሬ ከስልጣን እንዲወርዱ ከፍተኛ ተቃዉሞ በተደረገ ጊዜ በተቃዉሞዉ እንቅስቃሴና ተሳትፎን በማድረግ ቀደምትና ማዕከላዊዉን ቦታ በመያዝ እዉቅናን ያገኘ ከያኒ ነዉ።
የዛሬ ዓመት ቡርኪና ፋሶ ዋጋዱጉ መዲና ላይ ተቃዋሚዎች «ይበቃል።» ሲሉ ነበር አደባባይ በመዉጣት ተቃዉሞአቸዉን የገለፁት። ሕገ መንግሥቱን ቀይረዉ በስልጣን ለመቆየት የፈለጉት ኮምፖኦሬ ህዝባቸዉ የተመኙትን አላሟላላቸዉም። እድል ስላላገኙም ነዉ ከስልጣን ለመዉረድ የበቁት። የ64 ዓመቱ የቀድሞ የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓኦሬ እንደ ጎርጎረሰዊዉ አቆጣጠር በ1987 ዓ, ም በመፈንቅለ መንግሥት ነበር ስልጣንን ለመጀመሪያ ጊዜ የጨበጡት። ከ4 ዓመታት በኋላ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ምርጫ ተካሄደ፤ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ኮምፓኦሬ ሁሌም ምርጫ እንዳሸነፉ ቀጠሉ። በጎርጎረሳዊዉ 2000 ዓ,ም ኮምፖኦሬ ሕገ መንግሥቱን ቀይረው ሁለት ጊዜ የስልጣን ጊዜያቸውን ማራዘማቸዉ ይታወቃል። ኮምፓዎሪ መጨረሻ ላይ ይዘዉት የመጡት እቅዳቸዉ ግን አልተሳካም። ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓኦሬ በጎርጎረሰዊዉ 2014 ዓ,ም ከስልጣን ተወገዱ።
« በጎርጎረሰዊዉ 2014 እስከ 2015 ዓ,ም ሃገራችን አንድ የእድል እጣ ፈንታዉ ጥያቄ ዉስጥ የገባበትና እንጥልጥል ላይ የደረሰበት ነበር። ፕሬዚዳንቱ ስልጣናቸዉን ያስረክቡ አያስረክቡ የሚታወቅ ነገርም አልነበረም። በምናቤ በአንድ ምሽት የሃገሪቱ እድል እጣ ሁሉ በአንድ ጊዜ የሚቀለበስበት ሁኔታን ፈልጌ ነበር »
ሰርጌ ኤሜ በጎርጎረሰዊዉ 2014 ጥቅምት 25 በቡርኪና ፋሶ የደረሰዉን ትያትር በመድረክ አቀረበ። ሰርጌ ትያትሩን ማሳየት በጀመረ በስድስተኛዉ ቀን፤ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓኦሬ ከስልጣን እንዲነሱ የሚጠይቀዉ ተቃዉሞ እየጋመ እየተቀጣጠለ መጣ። ከወጣቱ ጋር የሚሰራዉ የትያትር ሥራ ባለሞያዉ ሰርጌ ትያትሩን ከሙዚቃና ከዳንስ ጋር በማቀናጀት ማኅበረሰቡ ጋር ለማድረግ ጥረቱን ጀመረ።
«እንደማስበዉ በብዙ የአፍሪቃ ሃገራት የማኅበረሰብ መሪዎችን የሚተቹና የሚነቅፍ ብዙ ትያትሮች ያልዋቸዉ ይመስለኛል። በትያትር አቀናባሪዎችና በጻሐፍት ዘንድ በርካታ ትችታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎችም አሉ። ከዚህ ሌላ እንደ ሙዚቀኛ ስሞስኪም አይነት የማኅበረሰቡን ጉድለት በማንፀባረቅ በሙዚቃ የሚያቀነቅን ከያኒም አለ። ግን እስከዛሬ ትችቶችና በማኅበሰብ ዉስጥ የሚታዩ ጉድፈቶች በዳንስ ተቀናብሮ ለተመልካች ሲቀርብ አልታየም። እኔ በዳንስ እንዲህ አይነቱን ነገር ከመፍጠሪ በፊት አብዛኛዉን ዳንስ አይነት የመዝናኛ ብቻ ነበር። በአገራችንም ዳንስ ከማኅበረሰቡ ዕለታዊ ሕይወት ጋር የተቆራኘ አይደለም።»
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓኦሬ፤ በአሁኑ ጊዜ በሃገራቸዉ ፖለቲካዉ ዘርፍ በመሳተፍ ላይ መሆናቸዉ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
በዚሁ የአፍሪኮለኝ የኪነ-ጥበብ ድግስ ላይ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ተወላጆች በመድረክ ላይ ለታዳሚ የቀረበዉ የአፍሪቃዉያኑ ትያትር መድረክ የማኅበረሰቡን የየዕለት ኑሮ የሚያመላክት በዴሞክራቲክ ኮንጎ የትያትር መድረክ የቀረበ መሆኑ ተነግሮለታል። በኮንጎ ተወላጁ ሲልቪ ዴክሎ ፖመስ የተደረሰዉ «ብሉ ኮማ ፤ » የተሰኘዉ ይህ ትያትር፤
«አነስታዚያ የምትባል አንዲት የአስራ ስድስት ዓመት ወጣት ፕሬዚዳንቱ መኖርያ ቅጽር ጊቢ አጠገብ ምንጣፍ ዘርግታ መኖርያዋን እዝያ አድርጋለች። ምክንያትዋ ደግሞ፤ ከሞት የተረፈችበት ከባድ ፍንዳታ ባስከተለዉ ቃጠሎ እጅግ ብዙ ህጻናት አልቀዋል፤ ህጻናቱ ፍትህ ያግኙ ነዉ። ፍንዳታዉ በጎርጎረሰዊዉ አቆጣጠር በ2012 ዓ,ም መጋቢት 4 ቀን መዲና ብራዛቪል ዴሞክራቲክ ኮንጎ ዉስጥ የጦር መሳርያ ቁሳቁስ ማስቀመጫ መጋዘን ጋይቶ ነዉ። በፍንዳታዉ እጅግ በርካታ ሰዎች አልቀዋል፤ በርካታ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸዉ ተቃጥሎ ፤ መኖርያ ቤትና ንብራተችዉን አጥተዋል። የትያትር ሥራ ባለሞያዋ ሲልቪ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ መንግሥት ላይ በግልፅ ቅሪታዉን ያሰማል፤
«ከጎርጎረሰዊዉ 2012 ዓ,ም መጋቢት 4 ጀምሮ ስለዚህ ጉዳይ ያነሳ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ዉሎ ይታሰራል። ሰዎች ፍፁም ስለዚህ ጉዳይ አያወሩም። ኮንጎ ዉስጥ ይህን ጉዳይ የሚተርከዉ ትያትር ለተመልካች ከቀረበ በኃላ ፤ ስለ ቃጠሎዉ ጉዳይ የሚያነሳ ባለመኖሩ፤ ስለዚህ ጉዳይ የሚያነሳ ነገር መጣ ብሎ ነዋሪዉ እጅግ ነዉ የተደሰተዉ። እኔ በነሱ ስም ሆኜ ተናግሪአለሁ። ይህን ማድረግ ይኖርብናል። በርግጥ እጅግ አደገኛ ሁኔታን ወደጎን ትቼ ፤ ለራሴ ሳላስብ ነዉ ያደረኩት ። ግን ይህን ነገር በይፋ ተናገርክ ተብዬ ብታሰር፤ መታሰሬ በራሱ በሃገሪቱ ምንም አይነት ዲሞክራሲ አለመኖሩን የሚያሳይ ጥሩ መረጃ ይሆናል»
በበርካታ አፍሪቃ ሃገራት በነበሩ ጦርነቶችና ግጭቶች፤ የስነ-ልቦና ችግር ያገኛቸዉ የጦርነቱ ተጎጂዎች ጥቂት አይደሉም። ይህን ችግር የገጠማቸዉ ተጎጂዎች አሁንም ምንም ዓይነት የስነ አዕምሮ ሕክምናንን አላገኙም። ከኮንጎ ተወላጁ የትያትር ሥራ ባለሞያ ሃርቪ ማሳምባ ይህን ችግር በትያትር መልክ ወደ መድርክ ይዞት ቀርቦአል።
« አንድ ምስጢር ልንገርህ ። በዚህ ጦርነት ለምን እንደተዋጋሁ ረስቸዋለሁ» ይላሉ በቀጥታ ትርጉሙ «የጦርነት ዘፈን» በተሰኘዉ ትያትር ላይ አንድ የአባት። ።ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ በተጠቃለለዉ በአፍሪኮለኙ ትርኢት ማጠቃለያለት የቀረበና እጅግ የተወደደ ትያትር እንደነበር ተነግሮለታል። በዚህ ትያትር አንድ አባት በጦርነት ላይ በአንድ አነስተኛ ገጠር መንደር ዉስጥ ስለፈፀመዉ ዘግናኝ ድርጊቶች ይተርካል። በዚሁ ትረካ ይህ ሰዉ ግድያና ፤ ሴቶችን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ እና በርካታ ዉድመትን ፈፅሞአል።
ጦርነቱ አልፎ ከብዙ ጊዜ በኃላ ይህ አሰቃቂ ድርጊትና ስቃይ አልፎ አልፎ በሕሊናዉ ድቅን እያለ ይመጣል። ችግሩን ለመፍታት ስለጉዳዩ ማዉራት ይኖርበታል። በካናዳዊዉ የተፃፈዉ ድርሰት በአንድ ቦታ ላይ ስለተፈፀመ አንድ የታወቀ ጦርነት አይደለም። ትያትሩ በጎሳ ግጭት ጥላቻ ኃይል የቀላቀለ ጥቃት የሚከተለዉን መሰረታዊ ነገር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ። ኤንሪ ማሲንባም ይህን መልክት ነበር መስማት ማየት የሚፈልገዉ፤
« በትያትር ድርሰቱ ዉስጥ ይህን ሳነብ ፤ ወድያዉ ነዉ ልቤ የተነካዉ፤ ስሜቴም የተረበሸዉ። ምክንያቱም ታሪኩ እኛ ጋር የተፈፀመ እና የሚታይ የነበረ ነገር በመሆኑ ነዉ። በአገራችን በተካሄደዉ የጦርነት ዓመታት ሁሉ፤ ጉዳት ለደረሰባቸዉ ነዋሪዎች የመንፈስ ጥንካሪና ማበረታቻ እንዲሆናቸዉ ምንም አይነት የስነ-ልቦና ሕክምና አልተካሄደም። በርካታ ሕዝብ በደረሰበት ጉዳት የስነ-ልቦና ችግር ደርሶበታል። እነዚህ ተጎጂ ሰዎች አሁን ወላጆች ሆነዋል፤ ችግራቸዉንም በቀጣይ ለልጆቻቸዉ እያስተላለፉ ይገኛሉ።» ሲል የኮንጎ ተወላጁ ማሲንባ ይገልጻል።
በኖርዝ ራይ ዊስፋልያ ግዛት አፍሪኮለኝ የቀረበዉ የአፍሪቃዉያኑ ሙዚቃ ትያትርና ዳንስ በእዉነታ ላይ የተመረኮዘና የማኅበረሰቡን ጥያቄ የሚያመላክት መሆኑ ተነግሮለታል።
ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ በጀርመን በኖርዝ ራይን ዊስትፋልያ ግዛት የተካሄደዉ አፍሪኮለኝ ትርኢት በተለይ በአፍሪቃ የሚታዩትን የሕዝብ አመጽ በትያትር መልክ በመድረክ ላይ ያንጨባረቀ ነበር። ሙሉዉን ቅንብር የድምጽማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

Theaterstück Cantate de guerre von Larry Tremblay inszeniert vom Theaterregisseur Harvey Massamba
ምስል DW/A. Gensbittel
Theaterstück Cantate de guerre von Larry Tremblay inszeniert vom Theaterregisseur Harvey Massamba
ምስል DW/A. Gensbittel
Theaterstück Cantate de guerre von Larry Tremblay inszeniert vom Theaterregisseur Harvey Massamba
ምስል DW/A. Gensbittel
Africologne Dialog Forum
ምስል DW/A. Gensbittel
Africologne Durchwachte Nacht in Ouagadougou
ምስል Africologne