1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዳሴ ግድብና የሶስትዮሹ ስብሰባ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 22 2006

ሚንስትሩ ግብፅ ኮሚቴዉ እንዲስየም ተስማማች ማለት «የግድቡን ግንባታ በይፋ ተቀበለች ማለት አይደለም» በማለት አጠቃላይ ዉዝግቡን ለማስወገድ ሰወስቱ ሀገራት አሁንም ብዙ መራቃቸዉን አልሸሸጉም።

https://p.dw.com/p/1D3JW
Nil Dammbau in Äthiopien
ምስል DW/G. T. Hailegiorgis

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምታሥገነባዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ሐይል ማመጫ ግድብ በዉሐዉ ፍሰት ላይ የሚያደርሰዉ ተፅዕኖ እንዲጠና «የሰወስትዮሽ» የተባለዉ የሚንስትሮች ስብሰባ ተስማማ።ካርቱም ላይ ተሠብስበዉ የነበሩት የኢትዮጵያ፤የሱዳንና የግብፅ የዉሐ ሚንስትሮች ባወጡት የጋራ መገለጫ እንዳስታወቁት ከሰወስቱ ሐገራት የተዉጣጣ አጥኚ ኮሚቴ እንዲመሠረት ተስማምተዋል።በሥምምነቱ መሠረት ዓለም ዓቀፍ ባለሙያዎች የግድቡ ግንባታ የሚያደርሰዉን ተፅዕኖ ያጠናሉ፤የሰወስቱ ሐገራት የጋራ ኮሚቴ ጥናቱን ይከታተላል።ነጋሽ መሐመድ የኢትዮጵያ የዉሐ፤የመስኖና የሐይል ሚንስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑን አነጋግሮ የሚከተለዉን ዘገባ አጠናቅሯል።

የሠወስቱ ሐገራት የዉሐ ጉዳይ ሚንስትሮች፤ በግብፅ እንቢተኝነት ለበርካታ ወራት አቋርጠዉት የነበረዉን ዉይይት ሰኞ ለመቀጠል መስማማታቸዉ እንደተነገረ ዉይይቱ ሲከፋ-እንደከዚሕ ቀደሙ ይቋረጣል-ሲያግባባ ደግሞ ሌላ ጊዜ ይቀጠራል-የሚል መላምት አስከትሎ ነበር።ሚንስትሮቹ ስብሰባቸዉን ሲያጠናቅቁ እንዳሉት ግን የዉይይታቸዉ ሒደት ብዙዎች ከጠበቁት ብዙ ያግባባ ነበር።

የስብሰባዉ አስተናጋጅ የሱዳኑ የዉሐ ሐብትና የኤልክትሪክ ሚንስትር ሙአታዝ ሙሳ አብደላሕ ሳሊም እንዳሉት ሥብሰባቸዉ ሰወስቱ ሐገራት መፍትሔ ለማግኘት ለሁለት ዓመታት ያደረጉና የሚያደርጉት ጥረት ከግብ ለማድረስ ያለመ ነበር።ሒደቱም፤ በሚንስትሩ አገላለፅ ሐቀኝነት፤ግልፅነትና እና መተማመን የሠፈነበት ነበር።

Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ የዉሐ፤የመስኖና የኃይል ሚንስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑም የሱዳን አቻቸዉን አስተያየት ይጋራሉ።የሥብሰባዉን ሒደት፤የተደረሰበት ስምምነት መስካሪ ነዉ-በማለት።

ሥምምነቱ ኢትዮጵያ የምታስገነባዉ ግድብ በዉሐዉ ፍሰት ላይ የሚያደርሰዉን ተፅዕኖ የሚያስጠና የጋራ ኮሚቴ እንዲመሠረት ነዉ።ኮሚቴዉ አቶ ዓለማየሁ እንዳሉት ከሰወስቱ ሐገራት የሚወከሉ እኩል አባላት ይኖሩታል።ዓለም ዓቀፍ ተቀጣሪ ባለሙያዎች የሚደርጉትን ጥናት ይከታተላል፤ጥናቱ ደግሞ ሁለት ዓይነት ነዉ።

«ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን» የተሠኘዉ ሥብስብ ከዚሕ ቀደም ያደረገዉ ጥናት እያለ አሁን አዲስ ጥናት እንዲደረገ ሚንስትሮቹ መስማማታቸዉ ድርብ ጥናት ግራ-አጋቢም ብጤ ነዉ።ሚንስትር ዓለመያሁ ግን ከእንግዲሕ የሚደረገዉ ጥናት እንዲደረግ የመከረዉ የቀድሞዉን ጥናት ያደረገዉ ቡድን ራሱ ነዉ ባይ ናቸዉ።

Karte Nil Verlauf und Renaissance-Staudamm

የግብፁ የዉሐና የመስኖ ሚንስትር ሁሴይን መሐመድ አል ሙጋዚ ዓለም አቀፉ አጥኚ ቡድን የጠቆመዉን ሐሳብ «ለካይሮ ጠቃሚ»፤ ሲሉት ከሁለቱ አቻዎቻቸዉ ጋር ያደረጉትን ሥምነትም «አግባቢ» በማለት አወድሰዉታል።ይሁንና ሚንስትሩ ግብፅ ኮሚቴዉ እንዲስየም ተስማማች ማለት «የግድቡን ግንባታ በይፋ ተቀበለች ማለት አይደለም» በማለት አጠቃላይ ዉዝግቡን ለማስወገድ ሰወስቱ ሐገራት አሁንም ብዙ መራቃቸዉን አልሸሸጉም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ