1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜናዊ ናይጀርያ የሚታየዉ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነዉ።

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2009

በሰሜናዊ ናይጄርያ የሚገኙ ሕጻናት በአስቸኳይ ርዳታ ካላገኙ በሚቀጥለዉ ዓመት ለአስከፊ ረሃብ ይጋለጣሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት  ህፃናት መርጃ ድርጅት አስጠነቀቀ። እንደ ድርጅቱ መግለጫ በሚቀጥለዉ ዓመት ወደ 80 ሺህ የሚሆኑ ሕጻናት ቦኮ ሃራም አካባቢዉ ላይ በደቀነዉ ቀዉስ በችጋር ይሞታሉ ሲል አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/2UY0F
Nigeria Kind Unterernährung Ärzte ohne Grenzen
ምስል picture alliance/AP Photo/Sunday Alamba

UNICEF: 80, 000 children will starve to death in Nigeria - MP3-Stereo

በሰሜናዊ ናይጄርያ የሚታየዉ ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆን የገለፀዉ ድርጅቱ አካባቢዉ ላይ የሚገኙት ወደ  400 ሺህ የሚሆኑ ሕጻናት የአስቸኳይ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ ገልጾአል።    

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ባለፈዉ ሳምንት መጀመርያ ባወጣዉ መግለጫ በሰሜናዊ ናይጀርያ የሚታየዉ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነዉ። የተመጣጠነ ምግብ እጦቱ ችግር እና የሞት አደጋ የተጋረጠባቸው ሕፃናት ቁጥር መብዛት በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ እንዳባባሰዉ ድርጅቱ ገልጾአል። በሰሜናዊ ናይጀርያ የሚታየዉን አሳሳቢ የሕጻናት ሁኔታን በተመለከተ መረጃን ይፋ ያደረገዉ የሕፃናት አድን ድርጅት በበኩሉ ለቀዉሱ ምክንያት የከባቢ አየር ለዉጥና  በአየር መለዋወጥ የደረሰ ተፈጥርዋዊ ቀዉስ እንዲሁም አካባቢዉ ላይ የሚንቀሳቀሰዉ አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሃራም ምክንያት ሕዝብ ከመኖርያ ቀየዉ በመፈናቀሉ  ነዉ። የሕፃናት አድን ድርጅት ባልደረባ ፊዮና ሚሼይ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ባለሥልጣናት በሀገሪቱ ረሃብ አደጋ ሲደርስ በጊዜ ርዳታን መጠየቅ ይከብዳቸዋል፤ ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል።

Symbolbild Weltgesundheitstag Jedes vierte Baby nicht ausreichend geimpft
ምስል picture-alliance/dpa

«ችግሩን ለመቋቋም ከአቅማችን በላይ ነዉ ብለዉ ለመናገር ይከብዳቸዋል።  ሰዎች የዓለም አቀፍ ርዳታ ድጋፍ እንዲሰጥዋቸዉና ከጎናቸዉ እንዲቆሙ ፤ ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እንዲያደርጉ እየጣርን ነዉ። በሃገራት ዉስጥ መንግሥት ራሳቸዉ ድርቁን ለመቋቋም ጥረት እያደረጉ መሆናቸዉን እዉቅናን ባለማሳየታቸዉ ርዳታ ድርጅችም ብዙ ገንዘብን ለማፍሰስ መነሳሳት አያሳዩም ።»

ዩኒሴፍ ይፋ ባደረገዉ መረጃ በሰሜናዊ ናይጀርያ 400 ሺህ ሕጻናት የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል። የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ያለባቸው ሕፃናት የሚሞቱት እንደ ተቅማጥ ባሉ ተጓዳኝ ሕመሞች ቢሆንም አሁን ግን ሕጻናት በረሃብ ብቻ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑንም ተዘግቦአል። ዋና መቀመጫዉን ሮም ያደረገዉ የዓለሙ የእርሻ ድርጅት «FAO» ባልደረባ ኒል ማርሴል ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ድርታቸዉ በሃገራት የረሃብ አደጋ መኖሩን ማስጠንቀቅያ የሚሰጠዉ ዘግይቶ ነዉ የሚለዉን ትችት አይቀበሉም፤

Polio Nigeria
ምስል AFP/Getty Images

   

«ረሃብ ሲመጣ ብቻ ነዉ ማስጠንቀቅያ የሚሰጠዉ የሚባለዉ ነገር እዉነት አይደለም። ምክንያቱም የምንሰጠዉን ማስጠንቀቅያ በአግባቡ ካልተቀበሉት በኋላ ችግሩን ለመከላከል በጣም አስቸጋሪ ነዉ። ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል የቅድምያ ማስጠንቀቅያ የምንሰጠዉ በቻልነዉ መጠን በጣም  ቀደም ብለን ነዉ።»

በሰሜናዊ ናይጀርያ 4,7 ሚሊዮን ሕዝብ የረሃብ አደጋ ያሰጋዋል። ከነዚህ መካከል ደግሞ 400 ሺዉ ሕጻናት ሕክምናና እርዳታን ካላገኙ ከአምስት አንዱ ሕጻን እንደሚሞት የሕጻናት አድን ድርጅት አሳስብዋል። ቦኮሃራም የተባለዉ ጽንፈኛ ቡድን በሚንቀሳቀስባቸዉ አካባቢዎች የሰብዓዊ ርዳታን ጨርሶ ማድረስ ባለመቻሉ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ሕጻናት ጉዳይ እንዳሳሰበዉም ድርጅቱ አስታዉቋል።  ባለፉት ሰባት ዓመታት በጽንፈኛዉ በቦኮ ሃራም የተገደሉት ሰዎች ከ 20,000 እንደሚበልጥም ተዘግቦአል።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ