1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕጻናት ገዳይ በሽታዎች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2005

በዓለማችን የሕፃናትን ህይወት ስለሚቀጥፉ በሽታዎች ሲወሳ ብዙዎች ቶሎ የሚያስቧቸዉ HIV AIDS አለያም የወባ በሽታዎችን ነዉ። አንዳንድ ጥናቶች የተዘነጉት ችግሮች ይሏቸዋል ተቅማጥና የሳንባ ምችን፤ እነዚህ ሁለት በሽታዎች የሚያደርሱት ጉዳት አሁንም ባለመገታቱ የህጻናትን ህይወት ለመታደግ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻ እየተጠቀሰ ነዉ።

https://p.dw.com/p/194i6
ምስል AP

 በዓለማችን ከሚደርሰዉ የሕጻናት ሞት በሳንባ ምችና በተቅማጥ በሽታ የሚያልፉት ብዛት 29 በመቶዉን ይይዛል። የተቅማጥ በሽታ ብቻዉን በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የ760 ሺህ ሕፃናትን ህይወት እንደሚቀጥፍ መረጃዎች ያመለክታሉ። ግሎባል ሄልዝ ሪቪዉ እንደሚለዉ አብዛኞቹ የሶስተኛዉ ዓለም ሃገሮች በእነዚህ በሽታዎች ቢጠቁም በተለይ የድሃ ድሃ የሚባሉት እንደህንድ፣ ናይጀሪያ፤ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ ፓኪስታን እና ኢትዮጵያ ይበልጥ የተጎዱ ናቸዉ። ለችግሩ መስፋትና መባባስ ዋነኛዉ ምክንያትም የንፁህ ዉሃ አቅርቦት እጥረት እና ለበሽታ የሚያጋልጡ ተህዋሲያን ሲሆኑ፤ በቂ የህክምና አገልግሎት አለማግኘትና የተመጣጣኝ ምግብ እጥረትም ጉዳቱን እንደሚያባብሱ ተጠቅሷል። እንደዘገባዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2010ዓ,ም ኢትዮጵያ ዉስጥ 271 ሺህ እድሜያቸዉ አምስት ዓመት ያልሞላ ሕጻናት በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት ተቀጥፈዋል።

MDG Tadschikistan Müttersterblichkeit
ምስል DW


ምንም እንኳን አፍሪቃ ዉስጥ አምስት ዓመት ሳይሞላቸዉ የሚቀጩት ሕፃናት ቁጥር ካለፉት ዓመታት ወዲህ እየቀነሰ መጥቷል ቢባልም በተለይ የተቅማጥ በሽታ አሁንም ለብዙዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት መሆኑ እንደቀጠለ ነዉ የዓለም የጤና ድርጅት ዘንድሮዉም ያመለክተዉ። እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም መጨረሻ ድረስ በእነዚህ ሁለት በሽታዎች ምክንያት የሚያልፈዉን የሕጻናት ህይወት ለማትረፍ ታዲያ እነሱ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ታቅዷል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ በተከታታይ ለሶስት ጊዜያት በየአምስት ዓመቱ የጤና እና የህዝብ ቆጠራ መካሄዱን ያመለከቱት በአሜሪካን የልማት ተራድኦ ድርጅት የሚደገፈዉና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋ በጋራ የተቀረጸዉ የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና መርሃግብር ምክትል የቴክኒክ ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ቡልቶ  በተገኘዉ መረጃ መሠረት የሚሞቱ ሕጻናት ቁጥር መቀነሱን ያመለክታሉ፤
ዶክተር ተስፋዬ እንደሚሉት የተመ የአምዓቱን የልማት ግብ ለማሳካት ከሚወለዱት አንድ ሺህ ሕጻናት የሚሞቱት ቁጥር ወደ67 ዝቅ ማለት ይኖርበታል፤ ይህን ለማድርግ ደግሞ ኢትዮጵያ መስመሩን ይዛለች ባይ ናቸዉ።
የሕጻናትን ህይወት ለማትረፍ ከሚደረገዉ ጥረት ጎን ለጎን የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚከናወኑ ተግባራትም ይጠቀሳሉ። እናቶች በህክምና መስጫ ማዕከላት እንዲገላገሉ ማድረጉ ዓመት ሳይሞላቸዉ የሚቀጠፉትን ሕፃናትም ማትረፍ እንዳስቻለም ዶክተር ተስፋዬ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ የሕጻናቱን ህይወት ከሚቀጥፉት በሽታዎች በተለይ የሳንባ ምች ዋነኛዉ መሆኑን በመጥቀስም ለሕጻናቱ ከሚደረገዉ ህክምና በተጓዳኝ የመከላከል ጥረቱም ከሁለት ዓመት በፊት እንደተጀመረ ያመለክታሉ። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከብሽታዎቹ ጋ ተዳምሮ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ በማመልከትም ለእናቶች ትምህርት እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፤

የተጠቀሱት በሽታዎች የግልና የአካባቢን ንጽህና ከመጠበቅ ጋ እንደሚገኙ ነዉ ባለሙያዎች የሚያሳስቡት። ንፁህ ዉሃና ሳሙና በሽታዉ በየቤቱ ከመግባቱ በፊት ንፅህናን ለመጠበቂያ ከሚፈለጉት መካከል ዋነኞቹ ናቸዉ። የህመሙ ምልክቶች ሲታዩ ደግሞ ፈጥኖ ተገቢዉን ርዳታ እንዲያገኙ ወደሃኪም ቤት መዉሰዱ ህይወት ሊያተርፉ የሚያስችል ጥረት ነዉ። እንዲያም ሆኖ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች መድሃኒቱና አገልግሎቱ ባይጠፋም የሰዎች የንቃትና ግንዛቤ ጉድለት ሊድኑ የሚችሉ ሕፃናት እንዲሞቱ ምክንያት መሆኑ እየታየ ነዉ። ለምሳሌ ኬንያ ዉስጥ በአንዳንድ አካባቢ አንድ ሕፃናት የተቅማጥ በሽታ ቢታመም የእርግማን ወይም የክፉ መንፈስ ቁርኝት ተደርጎ እንደሚወሰድ ዶክተር አልፍሬድ ኦቾላ የፓዝ ኬንያ የህጻናት አድንና ልማት የቴክኒክ አማካሪ ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም ልጁ ወደላይ ወደታች ሲለዉ የሚመለከቱ ቤተሰቦቹ ያ ክፉ መንፈስ እየወጣለት ነዉ ብለዉ ስለሚያስቡ ህክምና የማያገኝበት አጋጣሚ መኖሩን ያመለክታሉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ይህን መሰሉ ኋላቀር አመለካከት እንዲቀር ጥረት ካልተደረገ በቀር የመድሃኒትና ህክምና ርዳታዉ ብቻዉን የሚፈይደዉ አይኖርም።
ዶክተር ተስፋዬ ቡልቶ የተቀናጀ የቤተሰብ የጤና መርሃግብር በሚንቀሳቀስባቸዉ በአማራ፤ ኦሮሚያ፤ ደቡብና ትግራይ ክልሎች የተመሩጡ ወደሶስት መቶ የሚደርሱ ወረዳዎች የመንግስት ተቋማትን በመደገፍ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዉልናል። የአካባቢን ንጽህና ከመጠበቅ አኳያም ዛሬ አልፎ ተርፎ ፉክክር የተያዘበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ። 

Zimbabwe Afrika Armut
ምስል AP

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ