1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕፃናት መብት ተሟጋች ቡድኖች ዘመቻ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 11 2008

በምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪቃ የሚገኙ በርካታ የመብት ተሟጋች ቡድኖች የሕፃናትን መብት ለማስከበር አንድ አዲስ ዘመቻ አነቃቁ።

https://p.dw.com/p/1H9mD
Sambia Energiekrise - Wasser
ምስል DW/J. Jeffrey

የሕፃናት መብት ተሟጋች ቡድኖች ዘመቻ

በዚህ ሳምንት በደቡብ አፍሪቃ የጆሀንስበርግ ከተማ «በሕፃናት ላይ የሚፈፀመውን በደል እና ብዝበዛ ማስቆም» የተሰኘውን ዘመቻ ያስተዋወቁት የመብት ተሟጋች ቡድኖቹ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን፣ መንግሥታትን ጭምር ህፃናትን ደህንነት እንዲከላከሉ እና የሕፃናቱን መብት በሚረግጡት አንፃር ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ የሚያደርጉትን ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ ግፊት ለማሳረፍ ወስነዋል።

ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ስቃይ በብዙ ሃገራት እየከፋ የሄደበት ድርጊት ለዘመቻው መጀመር ዋነኛ ምክንኢት መሆኑን ተሟጋች ቡድኖቹ አስታውቀዋል። ግርፊያ፣ የልጅነት ትዳር፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ሕፃናት ን በስራ ማሰማራት፣ ወዘተ፣ የመሳሰሉት በሕፃናቱ ላይ ከሚደርሱት በደሎች መካከል ይጠቀሳሉ። የመብት ተሟጋቾቹ ቡድኖች ባንዳንድ አፍሪቃውያት ሃገራት የወጡ አስደንጋጭ መዘርዝሮች በሕፃናቱ ላይ አካላዊ፣ ወሲባዊ እና ስነ አዕምሮአዊ በደል የሚደርስባቸው ሕፃናት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያሉ። በነዚህ መዘርዝሮች መሠረት፣ በዛምቢያ ከየአምስቱ ሴቶች አንዷ፣ ከየአስሩ ወንዶች አንዱ ፣ በማላዊ ከየአምስቱ ልጃገረዶች ሁለቱ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ፣ በታንዛንያ ደግሞ ከየአስሩ ሕፃናት ሰባቱ የኃይል ተግባር ሰለባ መሆናቸው ፣ በደቡብ አፍሪቃ ክብረ ንፅሕና ሰለባ ከሆኑት ሕፃናት መካከል 84 ከመቶው በዘመዶቻቸው ወይም በቤተሰቦቻቸው ወዳጆች መደፈራቸው ተጠቅሶዋል።

Angola Raby José aus dem Zentrum für obdachlose Kinder in Luanda
ምስል DW/M. Luamba

የመብት ተሟጋች ቡድኖች ይህ ዓይነቱን በደል አሁኑኑ ለማስቆም እንደሚፈልጉ በደቡብ አፍሪቃ የሶንኬ ፆታዊ ፍትሕ አፈላላጊ ድርጅት፣ የሕፃናት መብት ተመልካች ክፍል ኃላፊ ዌስል ፋንደንቤርግ አስታውቀዋል።

« ያካባቢው መንግሥታት በሕፃናት ላይ የሚፈፀመውን የኃይል ተግባር የማብቃት ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው ብለን እናምናለን። አንድ በተጨባጭ ሊያስቀምጠው የሚገባው ርምጃ ሕፃናትን መምታት ወይም መግረፍ በሕግ የሚከለክል ፖሊስሲ ማውጣት ነው። »

በስዋዚላንድ የተመ የህፃናት መርጃ ድርጅት፣ በምህፃሩ የ«ዩኒሴፍ» ተጠሪ ራሼል ኦዴዴ የሃገራት መሪዎች በተለያዩ ጊዜዎች በሚያካሂዱዋቸው ጉባዔዎች ላይ ከሕፃናት ጉዳይ ይበልጥ ለፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጡበት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

« የዓለም መሪዎች ስለ ንግድ ወይም ስለ ልማት በሚነጋገሩበትም ጊዜ ስለ ሕፃናትን ጉዳይ መዘንጋት አይችሉም። ሕፃናትን ከኃይል ተግባር ፣ ከበሽታ፣ ከበደል ማን ነው የሚከላከላቸው? ስለዚህ መሪዎች ለሕፃናቱ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ሊወያዩበት ይገባል። »

Mosambik Mopeia Luis Va
ምስል DW

«Child Pipeline international Africa » በተባለው ድርጅት ዘገባ መሰረት፣ ድርጅቱ ከሚደርሱት የርዳታ ጥሪዎች መካከል ብዙው የኃይል ተግባር ሰለባ የሆኑ ሕፃናት መሆኑ ተገልጾዋል።

የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ የህፃናት ጉዳይ ተመልካች ጽሕፈት ቤት ባልደረባ ዶሚሲል እናላ የሕፃናትን ደህንነት ለመከላከል አስፈላጊው ሁሉ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

« ሕፃናት የወደፊቱ መሆናቸውን ተገንዝበነዋል። ስለዚህ ለነሱ ደህንነት ገንዘብ ማውጣት አለብን። መንግሥታት፣ የንግድ ተቋማት ፣ ሲብል ማህበረሰብም በሕፃናት ላይ የሚፈፀመው የኃይል ተግባር ማስቆም የሚቻልበትን መፍትሔ ለማፈላለግ ተባብረው ሊሰሩ ይገባል። »

በዚሁ ሰሞኑን በተነቃቃው ዘመቻ ላይ ከሚሳተፉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድርጅቶች መካከል « የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን የማህበራዊ ጉዳይ ተመልካች ክፍል፣ «ፕላን ኢንተርናሽናል» እና « ሴቭ ዘ ችልድረን» ይጠቀሳሉ።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ