1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመምህራን ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ

ሰኞ፣ ግንቦት 19 2011

መኖሪያ ቤት ችግርን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነገቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ መምህራን ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ከሰላማዊ ሰልፈኞቹ የተወሰኑት ለግማሽ ቀን ያህል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው መፈታታቸውን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቀው የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር «የማውቀው ነገር የለም» ብሏል።

https://p.dw.com/p/3JEk3
Addis Abeba
ምስል picture alliance / landov

የመምህራን ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እንደሚሰጠን ቃል የገባልንን መኖሪያ ቤት ሊያስረክበን ባለመቻሉ እና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የፖለቲካ ወገንተኝነት ያለበት መብታችንን የማያስጠብቅና የማይወክለን ነው በሚል ትናንት ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል። 1200 የሚሆኑ መምህራን መስቀል አደባባይ በመውጣት ለሰዓታት ጥያቄያችንን ለማሰማት መሞከራቸውን አንድ የታሪክ አስተማሪ ተናግረዋል። አብዛኛው መምህር መዋከቡንና አላማውን ለማሳካት ሳይችል መመለሱን የተወሰኑ መምህራንም ለግማሽ ቀን ታስረው መፈታታቸውን ገልጸዋል። 

መምህራኑ ከደሞዝ በላይ የመኖሪያ ቤት አንገብጋቢ ችግር እንደሆነባቸውና ይህንንም በተደጋጋሚ ጠይቀው ምላሽ ማጣታቸውን ይልቁንም ለዘመናት በአፈና ፣ በአካዳሚክ ነጻነት እጦትና በኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ማሳለፋቸውን የሰልፉ ተሳታፊ አውስተዋል። 

በመላ ሃገሪቱ ከ508 ሺህ በላይ አባላቶች አሉኝ የሚለው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የመምህራን  የመኖሪያ ቤት ችግር እንዲፈታ ከ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ፓኬጅ ጸድቆ ተግባራዊ የሆነ ሲሆን በዚህም ከ 50 ሺህ በላይ መምህራን በዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራሁ ነው ብሏል።

በ2009 ዓ.ም. መምህራንን ያላካተተው የደሞዝ ጭማሪም መልስ እንዲያገኝ እየሰራሁ ነው ብሏል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ በንቲ መምህራኑ እያነሱ ያሉት ጥቄቃ ተገቢ ቢሆንም አካሄዱን ግን እኛ አናውቀውም የትላንቱ ሰልፍ ላይም ታሰሩ ስለተባሉ ሰዎች የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።

በትናንቱ የመስቀል አደባባይ ድምጽን የማሰማት እንቅስቃሴ ላይ ከተገኙት ይልቅ በፖሊስ ተከልክለው የቀሩት እንደሚልቁ የሰልፉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ሙከራ ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም።

ሰለሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ