1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመረጃና የመገናኛ ቴክኒክ መስፋፋት ለልማት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 22 1996

ማዕከላዊ መሥሪያቤቱ በዋሽንግተን የሚገኘው የዓለም ባንክ ከጥቂት ዓመታት በፊት የመሠረተው “ዲቬሎፕመንት ጌትዌ ፋውንዴሽን” የተሰኘው የልማት ማራመጃ ድርጅት ቦን አጠገብ ፔተርስበርክ በተባለው ኮረብታማ የከፍተኛ እንግዶች ማረፊያና መስተናገጃ ማዕከል ባለፈው ዓመት ያካሄደው ዓይነቱ የመረጃና የመገናኛ ሥነቴክኒክ መድረክ ዘንድሮም በዚያው ቦታ ተከፍቶ ጠበብትን አወያይቷል፣

https://p.dw.com/p/E0fX

እስካሁን ስለተገኙ ተሞክሮዎችም ዘገባዎችን አስደምጧል። ልክ እንደ ዓምናው፣ የዘንድሮውም መድረክ አዘጋጅ የጀርመን ክፍለሀገር ሮርት-ራይን-ቬስትፋለን እና ዶይቸ ቴሌኮም ነበሩ። “የልማት በር” ሊሰኝ የሚችለው “ዴቬሎፕመንት ጌትዌ” በዘመኑ የመረጃና የመገናኛ ሥነቴክኒክ አማካይነት በተለይ በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ የዕውቀትን አድማስ በማስፋት፣ በድህነት አንፃር የሚደረገውን ትግል ለማጠናከር ነው የሚሻው።

የዓለም ባንክ ግማድ የሆነው ድርጅት “ዲቬሎፕመንት ጌትዌ ፋውንዴሽን” ቦን አጠገብ ፔተርስበርክ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በከፈተው የውይይት መድረክ ላይ እንደተመለከተው፣ የዘመኑ “ዲጂታል” ሥነቴክኒክ የልማትን ትብብር ውጤታማነት ለማሻሻል፣ የመንግሥትን ዘርፍ ግልጽ አሠራር ለማጠናከርና የመንደር ልማት ማኅበራትን ለማነቃቃት፣ በዚህም አኳኋን ድህነትን በጥንካሬ ለመታገል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የሚታመንበት። ለልማት በር ከፈታ የቆመው ድርጅት እንደሚለው፣ በሐብታሙ ሰሜንና በድህው ደቡብ መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በውስጥና በአካባቢም ደረጃ ያለው የዕውቀት ክፍተት እንዲጠብ ለማድረግ ነው ትግል የሚደረገው። በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የዓለም ባንክ ሊቀመንበር ጄምስ ዎልፈንሰን እንዳስገነዘቡት፣ በድሃና በሐብታም መካከል ያለው የእውቀት ክፍተት ካልጠበበ በስተቀር፣ ሰላምና እርጋታ ሊኖር አይችልም፤ በያለበት የእውቀት ኅብረተሰብእ መፈጠር ያለበት መሆኑ ነው። “ዴቬሎፕመንት ጌትዌ” ለዓለም የልማት ኅብረተሰብእ የመረጃ ልውውጥ ማዕከል ለመሆን መብቃቱን በእርካታ ነው የሚያስረዳው። በዚህም መሠረት፣ ይኸው የልማት በር ከፋቹ ድርጅት ዓምና በፔተርስበርክ መጀመሪያውን መድረክ ባካሄደበት ወቅት ፶ሺ የነበሩት አባላቱ ዛሬ ከ፩፻ሺ መብለጣቸውን፣ ከእነዚሁ አባላቱ መካከል ከ፶ በመቶ የሚበልጡት ከሚደረጁት ሀገሮች የሚመጡ መሆናቸውን፣ በየወሩም ከ፫፻ሺ የሚበልጡ ጎብኝዎች እንዳሉት ነው የተመለከተው።

የዚሁኑ ድርጅት የመረጃና የመገናኛ ሥነቴክኒክ እውቀት ዘመቻ ከሚጠቀሙበት የአፍሪቃ ሀገሮች መካከል ዛሬ በጉልህ አንዷ የሆነችው ሩዋንዳ አሁን በዘረጋችው መርሐግብር ሥር፣ በሚቀጥሉት ፲፭ ዓመታት ውስጥ የኑሮን ጥራት ለማሻሻል፣ እንዲሁም ተበታትኖ የነበረውን የሕዝቡን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ትሥሥር ለማጠናከር ትበቃ ዘንድ፣ በመረጃው መረብና በሥነቴክኒኩ እመርታ ላይ የተመሠረተ፣ መካከለኛውን መደብ ያማከለ ኤኮኖሚ ለመፍጠር የተነሳሳች መሆኗ ነው በመድረኩ ላይ የተገለፀው። በሌላም አነጋገር፣ ሕዝቡ ከእጅ-ወደ አፍ ከሆነው ከኋላቀሩ ግብርና እየተላቀቀ፣ በመረጃው ሥነቴክኒክና እውቀት ላይ ወደተመሠረተው፣ ሥልጡን የሠራተኛ ኃይል ወደሚመራው ዘመናይ ኤኮኖሚ እንዲሸጋገር ለማስቻል ነው የሩዋንዳው መንግሥት ዕቅድ የዘረጋው። “ራእይ ፪ሺ፳” የተሰኘው የሩዋንዳ ልማት ግብ ተፋጥኖ ይነቃቃ ዘንድ፣ “ሩዋንዳ ዴቬሎፕመንት ጌትዌ ግሩፕ” በሚል መጠሪያ አዲስ የተመሠረተው ቡድን ቁልፉን ያሳዋቂነት ሚና እንደሚይዝ ነው የተገለፀው። ይኸው የመረጃና የመገናኛ ሥነቴክኒክ ማስፋፊያ ዘመቻ ዛሬ በአፍሪቃው ምሥራቅ ወደ ኡጋንዳም በመሸጋገር ላይ እንደሚገኝ ነው በመድረኩ ላይ የተነገረው።

በድህነት አንፃር በሚደረገው ትግል ረገድ የመረጃውና የመገናኛው ሥነቴክኒክ ምኑን ያህል ዓቢይ ሚና እንዳለው በተለይ እስያዊቱ ሀገር ባንግላዴሽ ናት አንድ ተጨባጭ ምሳሌ ሆና የምትጠቀሰው። ባንግላዴሽ ውስጥ በዝነኛው የገጠር ልማት ጠቢብ ፕሮፌሰር ሙሐመድ ዩኑስ የሚመራው “ግራሚን-ባንክ የመንደር ስልክ አገልግሎት”፣ ዘንድሮ “ዴቬሎፕመንት ጌትዌ ፋውንዴሽን” ለመጀመሪያ ጊዜ ለልማት ሙያ የሰጠውን የ፩፻ሺ ኦይሮ ሽልማት ለማግኘት በቅቷል። የባንግላዴሽ ግራሚን-ባንክ ከ፪፻፳ ተወዳዳሪዎች መካከል ተመርጦ ነው ሽልማቱን ያገኘው።

በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ተጀምሮ በመስፋፋት፣ ለድሆች(በተለይ ለድሆቹ የገጠር ሴቶች) ያለምንም ዋስትና ንኡስ ብድር የሚሰጠው ግራሚን ባንክ፣ ዛሬ ለሽልማቱ ያበቃው “የመንደር ስልክ” የተሰኘው ውጤታማ የገጠር ልማት ፕሮዤ ነው። በዚሁ የመንደር ስልክ ፕሮዤ ሥር ድሆቹ የገጠር ሴቶች በዚያው በገጠሩ አካባቢ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ዝግጁ በማድረግ፣ ራሳቸው ባለኩባንያ እንዲሆኑ ይደረጋል። በዚህ አኳኋን፣ ፕሮፌሰር ዩኑስ እንደሚያስረዱት፣ ግራሚን ባንክ የገጠርን ሴቶች ከድህነት ለማላቀቀ የሚያስችል የልማት ኃይል እየሆነ ነው የተገኘው። በ፴ሺ የባንግላዴሽ መንደሮች ውስጥ ቀድሞ ሊታሰብ እንኳ ያልቻለው ዘመናዊው የመረጃ አገልግሎት ዛሬ የገበሬዎችንና የሌሎችንም ገጠሬዎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ማስቻሉን የግራሚን ባንክ መሥራቹ ፕሮፌሰር ዩኑስ በከፍተኛ እርካታ ነው የሚናገሩት። ዛሬ ባንግላዴሽ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገጠሬዎች ናቸው በመንደር ስልኩ አገልግሎት የሚጠቀሙት። የንኡስ ብድሩ አገልግሎትና የመንደር ስልኩ ፕሮዤ ካሁን ቀደም ምንም ገቢ ያልነበራቸው የገጠር ሴቶች ዛሬ በወር እስከ ፭፻ ዶላር እንደሚያገኙ ያረጋገጡት ባለሙያው ሙሐመድ ዩኑስ ዛሬ “የስልክ ወይዘሮዎች” ወይም “ፎን ሌዲስ” የሚሰኙት ስልክ-ሻጮቹ ሴቶች፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ “የኢንተርኔት ወይዘሮዎች”--ኢንተርኔት ሌዲስ”--ሊባሉ እንደሚበቁም ነው ተሥፋ የሚያደርጉት።

የመረጃው ሥነቴክኒክ የዓለምን ድህነት ለመቅረፍ ምኑን ያህል አንቀሳቃሽ ኃይል እንዳለው የዓለም ኅብረተሰብእ ካሁን ወዲያ በይበልጥ ይገነዘበው ዘንድ፣ የባንግላዴሹ የገጠር ልማት ፕሮዤ ዓይነተኛ ምልክት ነው የሚሆነው። በፔተርስበርክ የተካሄደው ሁለተኛው የመረጃና የመገናኛ ሥነቴክኒክ መድረክ በዚሁ ግብ አኳያ ነው የሚታየው።