1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአዲስ ዓመት መልእክት፣

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 23 2002

የጀርመን መራኂተ- መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል፣ አዲሱን 2010 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መንስዔ በማድረግ፣ ላገራቸው ዜጎች፣ ትናንት ማታ መልእክት አሰምተዋል።

https://p.dw.com/p/LIPZ

«(ክቡራትና ክቡራን)፣ ለእናንተና ለመላ ቤተሰባችሁ 2010 ፣ አዲሱ ዓመት፣ የጤናና የደስታ ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ!»።

ወሮ አንጌላ ሜርክል፣ በአዲስ ዓመት ዋዜማ መልእክት ለማሰማት የትናንት ማታው 5 ጊዜአቸው መሆኑን በመግለጽ፣ የትናንቱ የአዲስ ዓመት ዋዜማ፣ ከ 20 ዓመት በፊት በሃምበርግ ከተማ ፣ ከባላቸው ጋር ያሳለፉትን የማይረሳ ክብረ-በዓል እንደሚያስታውሳቸው ነው የጠቆሙት። እ ጎ አ ኅዳር 9 ቀን 1989 ዓ ም፣ የበርሊኑ ግንብ አጥር ፈረሰ። ታኅሳስ 31 ቀን ሐምበርግ ውስጥ ከምዕራብ ጀርመናውያኑ ዘመዶቻቸው ጋር የአዲሱን ዓመት ዋዜማና መባቻ ለማክበር የበቁት ሜርክል፣ የግንቡ አጥር ባይፈርስ ኖሮ የእርሳቸውና የያኔይቱ፣ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ(ምሥራቅ ጀርመን )ዜጎች በመላ፣ ዕጣ ፈንታቸው፣ ፍጹም የተለየ ሊሆነ ይችል እንደነበረ ሜርክል ያምናሉ።

«በምሥራቅ ጀርመን 35 ዓመታት ካሳለፍሁ በኋላ፣ የመጀመሪያውን የአዲስ ዓመት ዋዜማ ፣ በነጻነት ያሳለፍኩበት ሁኔታ ልዩ ሐሴት ለማድረግ ያበቃ ነበረ። እፁብ- ድንቅ ነበረ። ከዚያም፣ ከወራት በኋላ ጥቅምት 3 ቀን 1990 ዓ ም፣ አገራችን በነጻነት እንደገና ተዋኻደች። በዛሬው ምሽት ስለያኔው ሁኔታ መለስ ብዬ አስባለሁ።

እርግጥ ነው፣ በመልሶ ውኅደት ላጋጠሙ ችግሮች ሁሉ ገና መፍትኄዎቹን አላስገኘንም፣ የማይካደው ሐቅ ግን፣ የነጻነት ኃይል የበርሊኑን ግንብ አጥር የገረሠሠ መሆኑ ነው። ይኸው የነጻነት ኃይልም ነው፣ ዛሬ፣ በአዲሱ ዓመትና በመጪዎቹም ዐሠርተ-ዓመት፣ ብርታት ሊሰጠን የሚችለው! »

በውጭ ሀገራት በተለይ በአፍጋኒስታን የመልሶ ግንባታ ተግባር ለማከናወን የተሠማሩትን ሲብሎች፣ ሰላም ለማሥፈን የዘመቱትን ፖሊሶችና ወታደሮች አመሥግነው በአዲሱ ዓመትም ብዙ እንደሚጠበቅ የገለጡት ሜርክል፣ በሚመጡት ዓመታት ኀላፊነቱን ለአፍጋን ዜጎች ለማስረከብ ደረጃ በደረጃ ተቀዳሚ ግዴታዎች የሚሟሉበትን ሁኔታ በፖለቲካ ውሳኔዎች እልባት ማስያዝ ግድ እንደሚልም ነው ያስረዱት።

«በደል በተዛመተባት፣ የኃይል እርምጃ በተስፋፋባትና፣ ጦርነት ከአነአካቴው ሊወገድባት ባልቻለችው ዓለም፣ የሚመጡት 10 ዓመታት ፍትኅንና ሰብአዊነትን እንዴት መንከባከብ እንደምንችል፣ በጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ ታሪክም ታይቶ ያልታወቀውን የኤኮኖሚ ቀውስ እንዴት መቋቋም እንደምንችል፣ እንዲሁም፣ ለቀጣዩ ትውልድ ፋይናንሱን ለማስተካከል ወሳኞች ናቸው።»

በኮፐንሔገኑ የአየር ንብረት ጥበቃ ነክ ጉባዔ፣ ጀርመን በበጎ መንፈስ መላ ለመሻት ዝግጁ ሆና ብትቀርብና እተፈለገው ውሳኔ ላይ ባይደረስም፣ በአውሮፓ ፣ የተቃጠለ አየርን ልቀት በመመጠን ረገድ ጀርመን በትጋት እንደምትንቀሳቀስና እጅግ የደኸዩትን አገሮች ከመርዳት እንደማትቦዝንም ነው ሜርክል ያስረዱት።

ባዲሱ ዓመት፣ ከሚያስደስቱ ድርጊቶች፣ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ፣ የሩር አውራጃ፣ የ 2010 የአውሮፓ የባህል ከተማ ተብሎ በ ኤሰን የሚካሄድ ስብሰባ፣ እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያን ጉባዔ እንደሚገኙበት መራኂተ-መንግሥት ሜርክል ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የነጻነት ኃይል፣ የአብሮነቱ ተመክሮ፣ 60 ዓመት ጸንቶ የቆየው መሠረታዊው ህገ-መንግሥት፣ 20 ዓመት የሆነው ዳግም ሀገራዊ ውኅደት፣ እነዚህ ሁሉ ጀርመን የተለያዩ ፈተናዎችን መወጣት እንደምትችል የሚያመሥክሩ ናቸው።

« እናም ፣ 2010 ፣ ለአናንተ ለሁላችሁ፣ ከእነቤተሰባችሁ፣ ያሰባችሁት የሚሣካበት፣ ፍስሐን የምታገኙበትና የተባረከ ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።!»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ