1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ሰባት ሚሊዮን ሶማሌያውያን ዛሬም የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጥገኛ ናቸው

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 7 2010

ሶማሊያ ከ25 ዓመታት በላይ በየርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ ቆይታለች። መንግሥቱ ፈራርሶ ጠንካራዎቹ ጎሳዎች ሚናውን ነጥቀውታል። የተጣለበትን ኃላፊነት ባግባቡ የሚወጣ መንግሥት በመጥፋቱ ሶማሊያ አስከፊ ረሐብ ሲፈትናት ቆይቷል።  

https://p.dw.com/p/2m1y5
Somalia Mogadischu | unterernährtes Kind
ምስል DW/S. Petersmann

7 ሚሊዮን ገደማ ሶማሊያውያን የእርዳታ ጥገኛ ናቸው

በሞቅዲሹ ባናዲር ሆስፒታል ነርሶች የመነመነውን ሕጻን ልጅ እጆች በስስ ወረቀት ጠቀለሏቸው። አላማቸው ሕጻኑ አፍንጫው ላይ የተገጠመለትን የመመገቢያ ቀጭን ቱቦ እንዳይነቅል ለመግታት ነበር። "ምን እንደሆነ አላውቅም" ትላለች እናቱ ፋጡማ ስለ ልጇ ስትናገር። "ልመግበው ስሞክር ወዲያውኑ ያስመልሰዋል። በዚያ ላይ ተቅማጥ ይዞታል" ፋጡማ አከለች።

"ዝናቡን እንከተላለን"

ከሚቀጥለው ክፍል ካለው አልጋ ላይ ሐዋ የተባለች እናት ከኦቾሎኒ የተዘጋጀ የተመጣጠነ ምግብ ከትንሿ ሴት ልጇ አፍ ላይ ትጨምቃለች። ማታ ማታ ትኩሳቱ ተመልሶ ቢያገረሽባትም ባለፉት 12 ሳምንታት ግን ክብደት ጨምራለች። ትንሿ ሴት ልጅ አሁን የሚሰጣትን ምግብ በራሷ ጊዜ መዋጥ በመጀመሯ አፍንጫዋ ላይ ተገጥሞላት የነበረው የመመገቢያ ቀጭን ቱቦ ተወግዷል። "በቤታችን የሚላስ የሚቀመስ የለም። ልጆቻችን ከቀን ወደ ቀን እየደከሙ ነበር። ያኔ ጥለን ለመሔድ ወሰንን።" ትላለች ሐዋ። ከአሁን አሁን የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ያገኙናል ከሚል ሥጋታቸው ጋር እየታገሉ በጭለማ ውስጥ ለቀናት ተጉዘዋል። የእግር መንገዱ ስምንት ቀናት ፈጅቶባቸዋል።"የምንኖረው ከቀንድ ከብቶቻችን ጋር በገጠር ነው። በዚያ ሆስፒታልም ሆነ እርዳታ የለም።"

ሐዋ እና ፋጡማ አርብቶ-አደሮች ናቸው። ሁለቱም መደበኛ ትምህርት አልተከታተሉም። የለት ተለት ኑሯቸው ከቀንድ ከብቶቻቸው ውሎ ጋር የተሳሰረ ነው። በሶማሊያ በቅርቡ የተከሰተው ድርቅ አብዛኛዎቹን ፍየሎቻቸውን እና ግመሎቻቸውን ነጥቋቸዋል። ድርቁ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ቢያጠፋውም ሌላ ሕይወት ማለም ግን አይችሉም። መንግሥትም ሌላ አማራጭ አላቀረበላቸውም።

"ልጆቻችን እንዳገገሙ ተመልሰን ወደ መኖሪያ ቀያችን እንሔዳለን። ትኩረታችን በቀንድ ከብቶቻችን ላይ ነው። ዝናቡን እንከተላለን።" 

Somalia Mogadischu | unterernährtes Kind
ምስል DW/S. Petersmann

ይሁንና ዝናቡ እንደ ወትሮው እየጣለ አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው። የከባቢ አየር ለውጥ ተፅዕኖ በየቦታው ይታያል። ላለፉት አመታት እንደ ወትሮው ዝናባማ ወቅት የለም። የአፍሪቃ ቀንድ በረሐ ሆኗል። ሐዋ እና ፋጡማ በየርስ በርስ ጦርነት እና ተደጋጋሚ ድርቅ በገዛ አገራቸው ስደተኛ ከሆኑ አንድ ሚሊዮን ሶማሌያውያን ጋር እጣ ፈንታቸውን ይጋፈጣሉ።

በአገራቸው ከተሰደዱ መካከል ግማሽ ያክሉ ወደ ዋና ከተማዋ ሞቅዲሹ አቅንተዋል። የሐዋ እና የፋጡማ ልጆች የሚታከሙበት የባናዲር ሆስፒታል በአገሪቱ ከሚገኙት ትልቁ ነው። ለሆስፒታሉ ሰራተኞች ደሞዝ የሚከፍሉትም ሆነ አስፈላጊ የመድሐኒት ግብዓት የሚሸምቱት የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ናቸው።

አስቀድሞ መከላከል የሚቻል ሕመሞች

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) የሶማሊያ 28 የጤና ማዕከላትን ይደግፋል። የኮሚቴው የጤና አስተባባሪ ቢሻራ ሱሌይማን እንደሚሉት ሕሙማኑ የሚታከሙት ተመሳሳይ በሽታዎችን ነው።

"በአብዛኛው አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት ሕመም እና ተቅማጥ ነው የምናክመው። አብዛኞቹ ሕሙማን የሚኖሩት በቂ ምግብ እና ንፅህናው የተጠበቀ ውሐ በሌለበት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ነው።"

በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ከጥር እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እገዛ የሚደረግላቸው የጤና ማዕከላት ወደ 37,000 ገደማ ሕሙማንን አክመዋል። በዚሁ ተመሳሳይ ጊዜ በየወሩ 7,000 ሰዎች በአጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት ሕመም ተጠቅተዋል። አስቸጋሪው የአኗኗር ሁኔታ ተያያዥ ችግሮች አስከትሏል።

"የተመጣጠነ ምግብ እጦት የመከላከል አቅምን ያዳክማል" ሲሉ ያብራራሉ ቢሻራ ሱሌይማን። "የተመጣጠነምግብ እጦትን በራሱ መከላከል ይቻላል። ይሁንና የጤና ሥርዓቱ በመቃወሱ ምክንያት እጅጉን ተስፋፍቷል። በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት እና እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በተለይ የሳንባ ምች እና ኮሌራን ለመሰሉ ተላላፊ በሽታዎች  በቀላሉ ተጋላጭ ናቸው።"

የከፋ የምግብ እጥረት ተፈጥሯዊ እድገትን በመግታት ወይም በማዘግየት የሕጻናትን የረጅም ጊዜ እድገት ወደ ኋላ ይጎትታል።

Somalia Mogadischu | Flüchtlingsunterkunft
ምስል DW/S. Petersmann

ረሐብ በፖለቲካ ውድቀት ምክንያት

የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አምባገነኑ ዚያድ ባሬ በጎርጎሮሳዊው 1991 ዓ.ም. ከሥልጣን ከተባረሩ ጀምሮ ታጣቂ እና ተፎካካሪ የጎሳ መሪዎች እና ወንጀለኛ ቡድኖች የሶማሊያን ሥልጣን ለመቆጣጠር ሲፎካከሩ ቆይተዋል። አብዛኞቹ ፖለቲከኞችም በሕዝብ ደኅንነት ላይ ከማተኮር ይልቅ በጎሳ ፖለቲካ መሻኮትን መርጠዋል። የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ሐሳባዊ አገር ለመመሥረት የሽብርን መንገድ ይከተላሉ፤በረሐብ ለተጠቁ አካባቢዎች የሚላክ ሰብዓዊ እርዳትንም ይከለክላሉ። እጅግ ሰፊ ሙስናም አለ።

በሞቅዲሹ በሚገኘው ቪያ ሮማ ገበያ የዓለም የምግብ ድርጅት በእርዳታ ያቀረበው 50 ኪ.ግ. ሩዝ 23 ዶላር ይሸጣል። በብዛት ለሚገዛ ቅናሽ አለ። ከውጭ የሚገባውን እርዳታ እንዲህ ገበያ ላይ ሲሸጥ ማየት በሶማሊያ የተለመደ ነው። አንዳንድ ጊዜ እርዳታ ተቀባዮች የተሰጣቸውን ሩዝ እና ዘይት ለመሸጥ ይወስናሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ደላሎች እና የመንግሥት ሹማምንት ለእርዳታ የተላከውን ለግል ትርፋቸው ወደ ገበያ ስለሚልኩት ነው። የተባበሩት መንግሥትታ ድርጅት የሶማሊያ ልዩ ልዑክ ሚሻኤል ኬቲንግ በአገሪቱ የተንሰራፋው ረሐብ ዋንኛ ምክንያት የፖለቲካ ሥርዓቱ መፍረስ እንደሆነ ያምናሉ።

"ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ በሚወጡባቸው እና የመናገር ነፃነት በተከበረባቸው ማኅበረሰቦች ረሐብ ያን ያክል የለም። ረሐብ ሁልጊዜም ደሐ እና ደካማ በሆኑት የማኅበረሰቡ አባላት ላይ ይበረታል። የማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሒደት ውጤት ነው።"

አስቸጋሪው መልሶ መገንባት

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ ወደ ሰባት ሚሊዮን ገደማ ሶማሊያውያን በአሁኑ ወቅት በሰብዓዊ እርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው። ከአገሪቱ አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ግማሽ ያክሉ መሆኑ ነው። ካለፈው የካቲት ጀምሮ ሥልጣን የያዘው መንግሥት በዓለም አቀፍ እርዳታ ፌድራላዊ መንግሥት ማቆም ይፈልጋል። በሞቅዲሹ የሰፈነው መንፈስ ተስፋ ሰጪ ነው። የውጭ ዲፕሎማቶች እና ባለወረቶች ወደ አገሪቱ እየነጎዱ ነው። ከቀውስ ጥቅም ፈላጊዎችም ፈጠን ያለ ትርፍ ፍለጋ አብረው ብቅ ማለታቸው አልቀረም። የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒሥትር ኦማር ኦስማን ወደ ፊት ሊፈጠር የሚችል የረሐብ ቀውስን ለመግታት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በቀጥታ ወደ መንግሥታቸው ዓመታዊ በጀት እንዲሆን ይሻሉ።

"ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፍ አጋሮቻችን እምነት ላይ ጥገኞች ነን። መንግሥቱን መልሶ ለመገንባት ገንዘብ ካላገኘን በሙስና ልንከሰስ አንችልም። "

የሚኒሥትሩ ጥቆማ ዓለም አቀፉ እርዳታ ጭምር ከሙስና የጸዳ አይደለም የሚል ነው።

"በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያለው የገንዘብ ዝውውር ራሱ ሊፈተሽ ይገባል። ነገር ግን ሁልጊዜም ትኩረት የሚደረገው በሶማሊያ በኩል ያለው ሙስና ነው።"

ለውጥ ጊዜ ይሻል

በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. የተከሰተው የሶማሊያ የመጨረሻ ረሐብ 250,000  ሰዎች ገድሏል። በዚያን ጊዜ ዓለም ሶማሊያን ሙሉ በሙሉ ዘንግቷት ስለነበር እርዳታ የደረሰው እጅግ ዘግይቶ ነበር። በዚህ ዓመት ግዙፍ የእርዳታ ድርጅቶች በዚያ ይገኛሉ። የእርዳታ ሰራተኞቻቸው እና በዚያው በመገኘታቸው እና የመጠባበቂያ እርዳታ በማከማቸታቸው የባለፈው አይነት አስከፊ ቀውስ እንዳይከሰት መግታት ችለዋል። ፒተር ደ ክለርግ በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ናቸው።

Peter de Clercq, UN-Nothilfekoordinator für Somalia
ፒተር ደ ክለርግ በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ምስል UN Somalia

"2011 ጀምሮ ለሰብዓዊ እርዳታ 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርገናል። በእርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በስርዓቱ የሚሰራ መንግሥትን አይወክልም። 4 ቢሊዮን ዶላሩን ሶማሊያን መልሶ ለመገንባት አውለንው ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት ልንሆን እንደምንችል አስቡት። የሰብዓዊ እርዳታን ልናቆም ይገባል እያልኩ አይደለም። ነገር ግን በአስቸኳይ በልማት ላይ መስራት ይኖርብናል።"

ይሁንና ፒተር ደ ክለርግ የተጋነነ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ጠንቅቀው ያውቁታል። ሥልታዊ ትዕግሥት ከታጣ በሚቀጥሉት አስር አመታት በሶማሊያ የሚሰራው ሥራ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ያክላሉ።

ሳንዳራ ፒተርስማን/እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ