1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት ዕቅድና ወጣቶች የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ የወጣቶች ገንዘብ ዕቅድ

ዓርብ፣ ጥቅምት 18 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት የወጣቶችን ቁልፍ ጥያቄዎች ይፈታል ያለውን የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ የወጣቶች ገንዘብ ዕቅድ ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡ እቅዱ ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ ያስገኛል ቢባልለትም ወጣቶች ግን ከቀደመ ተሞክሯቸው በመነሳት ችግር ፈቺነቱን ተጠራጥረዋል፡፡ መንግሥት ሌሎች የቤት ሥራዎቹንም ይስራ ባይ ናቸው፡፡ 

https://p.dw.com/p/2RrGJ
Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

የመንግሥት እቅድና ወጣቶች

እንደ ትምህርት ቤቶች እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁሉ የኢትዮጵያ የሕግ አውጪ እና መወሰኛ ምክር ቤቶች ክረምቱን ለእረፍት ይዘጋሉ፡፡ መስከረም ሲጠባ ወደሥራ የሚመለሱት ሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባቸውን አሀዱ የሚሉት በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት በዓመቱ ሊከውናቸው ያቀዳቸውን ተግባራት ፍንጭ የሚሰጥበት ነው፡፡ የዚህ ዓመት የፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ንግግርም መሰል ጥቆማ ይዟል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አንድ ሰዓት በፈጀ ንግግራቸው ደጋግመው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የወጣቶች ነገር ነው፡፡ በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ወጣቱ “ዋነኛ ተዋናይ” እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ ወጣቶቹ “የሚገኙበትን ሁኔታ በትክክል መገንዘብና ለችግራቸውና ለጥያቄያቸው የሚመጥን መሠረታዊ መፍትሄ ማቅረብ «አጣዳፊ» እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡ በዚሁ ንግግራቸዉ  “ለየት ያለ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሥራዎች” በሚል ከዘረዘሯቸው ውስጥ የወጣቶቹ ጉዳይ ቀዳሚ ነው፡፡

እንደ መንግሥት እምነት ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት ዕድል የሚሰጠው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ማስፈጸሚያ የሚሆን የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ገንዘብ እንደሚቋቋም በፕሬዝዳንቱ አማካኝነት ይፋ ተደርጓል፡፡

“በያዝነው ዓመት በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል  የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል፡፡ ለዚህም ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ የአሥር ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ የፈንዱን አስተዳደርና አጠቃቀም በተመለከተ በሚወጣው የህግ ማዕቀፍ መሠረት የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ሙላቱ እቅዱን ተናግረዋል፡፡  

“መንግስት የወጣቶች ፈንድ አጠቃቀምና የኘሮጀክቶች ትግበራ መሰረተ ሃሳቦችን ከሚመለከታቸው የአመራር አካላትና ከወጣቶች ጋር በመመካከርና ተፈላጊውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ በመስጠት የሚያስፈፅም ሲሆን፣ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀየሰው ኘሮግራም በየጊዜው እየተገመገመ አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድበት እንዲሆን ይደረጋል” ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ መንግሥት የወጣቶችን ችግር ለመፍታት በሚል የተለየ መፍትሄ አዘጋጅቼያለሁ ሲል የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ቀርጾ፤ ለገጠር እና ለከተማ ወጣቶች በሚል የከፋፈለውን “የወጣቶች ማዕቀፍ» ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም እንደታለመዉ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒሰትሩን አቶ ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት የወጣቶችን ችግር ይፈታል በሚል የተቀረጹት ማዕቀፎች ከወቅቱ ጋር ሊሄዱ እንዳልቻሉ ሲገልጹ ታይተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሙላቱም በንግግራቸው ከዚህ ቀደም የተዘጋጁት መፍትሄዎች “እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥር እና ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን” እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ መቶ ሚሊዮን ከሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ከ30 ዓመት በታች ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለእነዚህ ወጣቶች ታስበው የተቀረጹ መርሃግብሮች «በመንግሥት በኩል በሚታዩ ድክመቶች በተለይ ደግሞ በአድሏዊ እና ብልሹ አሰራሮች ምክንያት ሲደነቃቀፉ የወጣቱ ትውልድ ቅሬታ እንደሚባባስ ታይቷል» ይላሉ ፕሬዝዳንት ሙላቱ፡፡

እርሳቸው ጭምር የዘረዘሯቸው ችግሮች ባሉበት ሁኔታ በአዲስ ያቀረቡት “የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ገንዘብ” ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ የዛሬ ዓመት ግድም የፈነዳው ተቃውሞ ዋነኛ ማዕከል የነበረው የኦሮሚያ ክልል 2.4 በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ ሥራ አጥነትን እዋጋለሁ ካለ ገና መንፈቅ መቆጠሩ ነው፡፡ ባለፈው የካቲት ይፋ የተደረገው የክልሉ ዕቅድ ለ832‚000 ወጣቶች የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ያለመ ነበር፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ በዴሳ ነዋሪ የሆነ ወጣት በክልሉ የተገባውን ቃል በኦሮሚያ የመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ ሰምቷል፡፡ ከዚያ በኋላ በአካባቢቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ተከታትሏል ነገር ግን “ቃል እና ተግባር” አልተገናኙለትም፡፡ 

Äthiopien Mulatu Teshome ist neuer Präsident
ምስል Elias Asmare/AFP/Getty Images

“ምንም የተለየ ነገር የለም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በማይክሮ ኢንትርፕራይዝ እናደራጃች ኋላን ብለው በወሬ ደረጃ እና በወረቀት ደረጃ ተጽፎ የመጣ አለ፡፡ ይሄ ለይስሙላ የመጣ ወረቀት ነው፡፡ እስከዛሬ ግን የመጣ ብር የለም፡፡ ይሄ ወጣቶቹን ወደ ስራ ለማስገባት አይደለም ስለወጣቶቹ ጉዳይ ራሱ የሚያወራ ሰው አታገኝም” ይላል፡፡

መንግሥት ይህን እቅድ ይፋ ያደረገው ወጣቶችን “በእጁ ለማሰገባት” እንጂ በትክክልም ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ አስቦ እንዳይደለም የበዴሳው ወጣት ይከራከራል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሲያደርገው የነበረውንም ጥረት “የይስሙላ” ይለዋል፡፡ ለዚህም በአካባቢያቸው ሰኔ ወር ላይ የተጠራን ስብሰባ በምሳሌነት ያነሳል፡፡ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ለወጡ ሥራ አጥ ወጣቶች በተጠራ ስብሰባ ላይ ሁለተኛ ደረጃ እንኳ ያልደረሱ ሰዎችን በማሳተፍ መንግሥት የሚፈልገውን እንዲናገሩ ከተደረጉ በኋላ ያዉ ተቀርጾ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን መተላለፉንም ያስታውሳል፡፡

“ወጣቶች የመንግሥትን እጅ ሳይጠብቁ ሥራ ፈጣሪ መሆን አለባቸው” በሚለው የመንግሥትን የዘወትር ውትወታም የበዴሳው ወጣት ራሱ በተግባር መፈተሹን እንዲህ ያስረዳል፡፡  

“ለራሴ መንግስት ቤት እሰራ ነበር፡፡ ከመንግስት ቤት ጥዬ ወጣሁ፡፡ ስራ ትቼ ማለት ነው፡፡ ከዚያ የራሴን የግል ስራ ጀመርሁ፡፡ የግል ስራ እንኳ በራስህ ብትሰራ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርተህ ለማደግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምንድነው? ስትሰራ ከምትሰራው ነገር የመትከፍለው ብዙ ነው፡፡ እዚህ ጋር መጥቶ ይህን ትከፍላለህ ይለሃል፡፡ በዚያ ላይ ግብር ብለው በዓመት ላይ ትከፍላለህ፡፡ የስራ እና የሙያ ፍቃድ ብለው ለዚህም ትከፍላለህ፡፡ ለስንት ነገር ነው ክፍያ የምትከፍለው?” በምሬት ይጠይቃል፡፡

“ይህንን ሁሉ ችግር ውስጥ አልፈን፣ ሰርተን፣ ነገ እናድጋለን ብለው በመንግስት ላይ ሙሉ ለሙሉ እምነት የላቸውም፡፡” 

ከምሥራቅ ኢትዮጵያ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠን፣ ወደ ሰሜን ተጉዘን፣ ደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ ብንገኝ የምንዳምጠውም እሮሮ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው የሐይቁ ወጣት በዞናቸው በከተማም በገጠርም ያሉ ወጣቶች በሥራ እጦት ባህር እያቋረጡ መሰደድ ዕጣ ፈንታቸው እንደሆነ ያገልጻል፡፡

“ከመጠን በላይ ስራ አጥ ወጣቶች በከተማም በገጠርም ያለው፡፡ በባህር እየተሻገሩ በየመን እና በጅቡቲ በረሃ ላይ እየቀለጡ የቀሩ ብዙ አሉ፡፡ በዋትስ አፕ ‘አፋልጉን፤ መንገድ ገብቶ ጠፋ፣ መንገድ ገብታ ጠፋች፤ እባካችሁ የወደቁበትን አሳዩን’ እያሉ ብዙዎች ይልኩልናል፡፡ እኛ አካባቢ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያለው፤ በጣም ይዘገንናል” ይላል፡፡  

ከደቡብ ወሎ የሚነሱ በርካታ ወጣቶች በሶማሌ ክልል አቋርጠው እና የጅቡቲን መስመር ይዘው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ሥራ ፍለጋ እንደሚሰደዱ የሐይቁ ወጣት ይናገራል፡፡ እስከ አስር ሺህ ብር የሚያስወጣው ይህ ጉዞ የመን በረሃ ዉስጥ በአጋቾች መያዝን ከጨመረ እስከ 50 ሺህ እና 60 ሺህ ብር ሊወስድ እንደሚችል ያብራራል፡፡ ለጉዞ የሚያወጡትን ገንዘብ በሀገር ቤት ለምን እንደማይጠቀሙ ለተጠየቀው ሲመልስ የራሳቸውን ሥራ የጀመሩ እንኳ በግብር ክፍያ እንደሚማረሩ እና ከውጭ ገንዘብ ተልኮላቸው የሚሠሩትም “በፅንፈኛ ድርጅቶች ትደጎማላችሁ” እየተባሉ መሸማቀቅ እንደሚደርስባቸው ይናገራል፡፡   

በሐይቅም ሆነ በበዴሳ የሚኖሩት ወጣቶች በፕሬዝዳንቱ የቀረበውን የ10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች የገንዘብ ተቋም እቅድን ቢያደምጡም ጥርጣሬ አላቸው፡፡ የሐይቁ ወጣት “የተስፋ ዳቦ” ሲል ሰይሞታል፡፡ የበዴሳው ደግሞ “ወጣቶችን ማባበያ” ይለዋል፡፡

የሐይቁ ወጣት መንግሥት ይህን እቅድ ይዞ የመጣው የደረሰበትን ተቃውሞ ለማብረድ ነው የሚል እምነት አለው፡፡

“ይህ እንግዲህ ምናልባት መቄጥን የሚያመላክት ነው፡፡ በስርዓቱ ተወልደው ያደጉ ናቸው እነዚህ ወጣት የሚባሉት በአሁኑ ሰዓት፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ከመሸንገል እንዲሁ ቀርቦ እና አቅርቦ ማወያየቱ እና ማነጋገሩ የተሻለ ነገር ነበር፡፡ እንጂ እንደዚህ እነርሱን በተሻለ ተስፋ እየሸነገሉ የሚረጋጉበትን መንገድ ለመፈለግ ያደረጉት ስልት ይመስለኛል” ሲል አስተያየቱን ያጋራል፡፡    

ሁለቱም ወጣቶች የወጣቱ ችግር ሥራ ማጣት ብቻ ሳይሆን የመብቶቹ አለመከበር እና በአግባቡ አለመሰማቱ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡ የበዴሳው ወጣት ህዝቡ “በስርዓቱ ላይ እምነት አጥቷል” ባይ ነዉ፡፡ ስርዓቱ እስካልተቀየረ ድረስ እንዲህ አይነት እቅዶች መፍትሄ አይሆኑም ሲልም ይሟገታል፡፡

“የስርዓቱ መቀይር ብቻ ነው መፍትሄ መሆን የሚችለው፡፡ እንጂ የፈለጉትን ያህል ብር ቢመድቡ፤ ብርም አይደለም ወርቅ ቢመድቡ መፍትሄ ሊሆን አይችልም” ሲል ለችግሩ መድኃኒት የሚለውን ይጠቁማል፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ